Get Mystery Box with random crypto!

ትንኝን በምግብ የሚያስብ እግዚአብሔር አሰበኝ 'ለክብሩ ቀንተህ ስትጣል  ምግብ አብስሎ እንደ እና | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

ትንኝን በምግብ የሚያስብ እግዚአብሔር አሰበኝ

"ለክብሩ ቀንተህ ስትጣል  ምግብ አብስሎ እንደ እናት÷ገስጾ እና መክሮ እንደ አባት  የሚያኖርህ እግዚአብሔር ለችግሮችህ መፍትሔ የሚሆኑ ሰዎችን ይልክለሀል።"

ዳንኤል በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ እና ተግቶ በመኖሩ የነገሥታቱን ድለላና ዛቻ ጥሎ ፈቃደ እግዚአብሔርን በመጠበቁ በባቢሎን ምድር በግበ አናብስት (በአናብስት ጉድጓድ) ተጥሎ ነበር። በዛው ወራት ዕንባቆብ ደግሞ ለአጫዶች ሁሉ ምግብ አብስሎ ምሳ ይዞ ሲሔድ የእግዚብሔር መልአክ ተገልጦ "ይህን አብስለህ የያዝከውን ምሳ በአናብስት ጉድጓድ ተጥሎ ላለው ለዳንኤል ውሰደለት እርሱ አሁን ባቢሎን ይገኛል የሚል መልእክት ነገረው"። ዕንባቆብም መልሶ "ወለባቢሎንኒ ኢይአምራ" ባቢሎንን አላቃትም ቢል መልአኩ  በጸጉሩ ይዞ አድርሶታል። ከዛም እንደ ደረሰ ያበሰለውን ምግብ በተዘጋ ግንብ ገብቶ ለዳንኤለ ሰጥቶ በተዘጋ ግንብ ወጥቷል። ዳንኤልም ይህን ሲመለከት "ትንኝን በምግብ የሚያስብ እግዚአብሔር አሰበኝ" ብሎ አመሰገነ።

እግዚአብሔር በእኛ የጀመረውን ዓላማ እስኪጨርስ ድረስ ለሚገጥሙን ስብራቶች ጠጋኞችን÷ለሚፈጠሩብን ጉድጓዶች ድልድይ የሚሆኑንን ይልክልናል። እንደ ዳንኤል ለእውነት ብለህ ስትቸገር ለሌላ የታሰበውን ሲሳይ ይዘውልህ የሚመጡ ድንገተኛ ዕንባቆቦችን ያዘጋጅለሀል። እውነት የሆነ ክርስቶስን ሰቅለው ቁማር ሲጫወቱ እንዳመሹት ሳይሆን የመስቀሉን እውነት አስበው መከራ ከሚቀበሉት ወገን ለመቆጠር ቁርጠኛ ለመሆን ከተጋህ ሰዎች በማይደርሱበት ዱር ላይ ብትሆን እንኳን መፍትሔ ሊሆንህ የሚችል መውጫን ያዘጋጅልሀል።

ዳንኤል በምድር ገዢዎች ፊት ጥፋተኛ የሰማይና የምድር ገዢ በሆነው በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እውነተኛ ሆኖ በመገኘቱ በመከራው ጊዜ ይተወው ዘንድ አልወደድም። በእግዚአብሔር  ዘንድ ትክክለኛ መሆንህን ሳታውቅ በሰዎች ዘንድ ትክክለኝነትህን ለማረጋገጥ ስትጥር የእድሜህ ማገባደጃ ላይ ትደርሳለህ። ብዙ ሰዎችን የገዛ ሐሳብ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ዋጋ አልባ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ቀላሉ መፍትሔ በእግዚአብሔር ሕግጋት ውስጥ ተመላልሰህ በእርሱ ፊት ትክክለኛ ለመሆን መድከም ነው። ያኔ ለሚደርሰብሕ መከራ መውጫውንም ያዘጋጅለሀል። መውጫውን ባያበጅልህ እንኳን ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት አክሊልን ያቀዳጅሀል።

በናታን በኩል ዳዊትን ከኃጢአት የመለሰ እግዚአብሔር በኃጢአት ማዕበል እንዳንወሰድ የሚመልሱን ደጋጎቹን እንደሚልክ በዕንባቆብም በኩል የዳንኤልን ረኅብ እንዳስታገሰ ለሥጋዊ ሕይወታችን ረብ የሚሆኑትን ይልካል።

እግዚአብሔር ለሥጋችንም ለነፍሳችንም ያስባል።

ዲ/ን ሞገስ አብረሃም


https://t.me/akanim1wasen2