2022-09-08 19:53:11
በ2014 ጠቅላላ የውጪ ንግድ (Export and Import) ሪፖርት
የውጪ ንግድ (Export)፡- የኢትዮጲያ የውጪ ንግድ 4.1 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከባለፈው አመት የ600 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ አለው፡፡ የውጪ ንግድ ግኝት 20 % ያድጋል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም በ14 % ጭማሪ ያለው ግኝት ተገኝቷል፡፡
ወደ ውጪ የተላኩ ቁሳቁሶች የደረሱበት ሀገር ድርሻ ሲታይ ሲዊዘርላንድ 13%፤ ኔዘርላንድ 9%፤ አሜሪካ 9% ድርሻ፤ ሶማሊያ 8%፤ ሳውዲ አረቢያ 7% እና ጀርመን 7% በመሸመት ቀዳሚ ሲሆኑ በጠቅላላ ኢትዮጲያ ከ30 በላይ ለሆኑ የዓለም ሀገራት ምርቶቿን ልካለች፡፡
ከ2013 የውጪ ንግድ አንጻር በ2014 የተገኘው የ600 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ ምክንያት የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የጫት ፍላጎት ማደግ (27%)፤ ጀርመን ለቡና ያላት ፍላት ማደግ (24%) እና ኔዘርላንድ ለአበባ የነበራት ፍላጎት ማደግ (19%) የፈጠረው ነው (እነዚህ ሶስት ሀገራት ያላቸው ፍላጎት ማደግ 70% የኢትዮጲያ የውጪ ንግድ እንዲያድግ አግዟል)፡፡
ወደ ውጪ የተላኩ ምርቶች ዝርዝር ሲታይ ቡና (1.4 ቢሊየን ዶላር)፤ ወርቅ (546 ሚሊየን ዶላር) እና አበባ (544 ሚሊየን ዶላር) ድርሻ አላቸው በድምሩ ሶስቱ ምርቶች ብቻ ከጠቅላላው ግኝት የ60% ድርሻ አላቸው፡፡
ወደ ውጪ የተላኩ ምርቶች መጠን ሲታይ ወደ ውጪ ከተላኩት መካከል ቡና በ57%፤ ስጋ በ45% ፤ ፍራፍሬ በ27% እና ጨርቃጨርቅ በ19% ወደ ውጪ የተላከው ከ2013 አንጻር እድገት ሲኖራቸው በተቃራኒው የቅባት እህል እና ጥራጥሬ በ26%፤ ወርቅ በ16% እና የቆዳ ውጤቶች በ9% ከ2013 አንጻር የቀነሰ ምርት ወደ ውጪ ተልኳል፡፡ ለውጪ ገበያ ከሚቀርቡ 18 ምርቶች መካከል 10 የሚሆኑ ምርቶች ጠቅላላ አቅርቦት በ2014 ዝቅተኛ ሆኗል፡፡
ይህ የሚያሳየው የውጪ ምንዛሬ ግኝት እድገቱ የተገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት በመላክ ሳይሆን በዓለም ገበያ የመሸጫ ዋጋዎች በመጨመራቸው ነው፡፡ #ለምሳሌ፡- የቡና መሸጫ ዋጋ በዓለም ገበያ በ30% አድጓል፡፡ የውጪ ንግድ አፈጻጸም መለኪያ ዋነኛው በየዓመቱ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች መጠን እየጨመረ መሄዱ ቢሆብም ወደ ውጪ የሚላከው መጠን ቀንሶ የዓለም ገበያ ዋጋ በመጨመር የሚገኝ የትርፍ እድገት ውስን ድክመት አለበት፡፡
ቡና በከፍተኛ ሁኔታ በዓለም ገበያ ዋጋው በመጨመሩ የውጪ ግኝቱ ሲያድግ ጨርቃጨርቅ፤ አበባ እና ስጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጠናቸው በመጨመሩ የውጪ ምንዛሬ ግኝቱ እንዲያድግ ሆኗል፡፡
#ለምሳሌ፡- የAGOA ክልከላ የጨርቃጨርቅ ምርትን ለጥቂት ወር የቀነሰው ቢሆንም ቀድሞ የነበሩ ትዛዞችን በመሸጥ፤ ከነታሪፉ በአሜሪካ ገበያ ማቅረብ የቻሉ አምራቾች መኖር እንዲሁም የጨርቃጨርቅ አምራቾች በአማራጭ የቻይና፤ የካናዳ እና የቱርክ ገበያዎች ላይ ሽያጭ መጀመራቸው መጠኑ እንዲያንሰራራ አድርጓል)፡፡
#ለምሳሌ፡- የአበባ ምርቶች ላይ አዳዲስ ማሳዎች መዘጋጀት እና ነባር የአበባ አምራቾች የማስፋፊያ ቦታ ማዘጋጀት (የአበባ ማሳዎች ስፋት በ12% ጨምሯል)፤ የማጓጓዣ ስርዓት መስተካከል እና የቀጠለ የአውሮፓ ሀገራት የአበባ ፍላጎት መኖር፤ ከአውሮፓ ውጪ ያሉ ሀገራት እንደ መካከለኛው ምስራቅ፤ እስያ እና አፍሪካዊያን የኢትዮጲያን አበባ ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት በ19 % ማደጉ የአበባ ምርት መጠን በ2014 እንዲጨምር አድርጓል፡፡
#ለምሳሌ፡- የስጋ ምርት በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራ ያለው ፍላጎት ካለፈው ሁለት ዓመታት ወዲህ በማደጉ 67 ሚሊየን ዶላር ይገኝበት የነበረው መጠን በ2014 ወደ 100 ሚሊየን ዶላር ግኝቱ አድጓል፡፡
በ2014 ጠቅላላ 22.7 ቢሊየን ዶላር ከተለያዩ ምንጮች የውጪ ምንዛሬ የተገኘ ሲሆን የቁሳቁስ ሽያጭ 4.1 ቢሊየን ዶላር፤ የአገልግሎት ሽያጭ 6.2 ቢሊየን ዶላር፤ ሬሚታንስ 5.3 ቢሊየን ዶላር፤ FDI 3.2 ቢሊየን ዶላር፤ ብድር 1.1 ቢሊየን ዶላር (ብድሩ በመንግስት እና በመንግስት የልማት ድርጅቶች በጋራ የተወሰደ ነው) እና እርዳታ 1 ቢሊየን ዶላር ነው፡፡
ከ2013 አንጻር ለውጪ ምንዛሬ ግኝቱ መጨመር የቁሳቁስ ሽያጭ በ13% የአገልግሎት ሽያጭ በ21% እና ሬሚታንስ በ2% እድገት የነበራቸው ቢሆንም የመንግስት ብድር በ100 ሚሊየን፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር በ900 ሚሊየን ዶላር እና እርዳታ በ300 ሚሊየን ዶላር ከ2013 አንጻር በ2014 ቀንሷል፡፡
በ2014 ጠቅላላ የተገኘ የውጪ ምንዛሬ 22 ቢሊየን ዶላር ቢሆንም ከውጪ የተሸመተው የ18 ቢሊየን ዶላር ወጪ ልዩነት 4 ቢሊየን ዶላር ያለፈ ሲሆን የ Balance of Payment ልዩነቱ በ2014ዓ.ም 2 ቢሊየን ዶላር ደርሷል፡፡ በ2013 ከነበረው የ2.9 ቢሊየን ዶላር ልዩነት አንጻር መሻሻል ያለው ሲሆን ክፍተቱን ለመሙላት የብሄራዊ ባንክ እና ከባንኮች ከነበረው ከጠቅላላ የውጪ ምንዛሬ ክምችት ተሸፍኗል፡፡
2014 ዓ.ም ሲጀምር የመንግስት የውጪ ምንዛሬ ግኝት እቅድ 5.4 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ቢሆንም የተሳካው 4.1 ቢሊየን ዶላር ነው፡፡ ይህም ግኝት የተገኘው የቡና እና የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ስለጨመረ (#ለምሳሌ፡- የኢትዮጲያ ቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ከ2013 አንጻር በ25% ጨምሯል) አንዲሁም የአበባ እና የፍራፍሬ ምርት መጠን መጨመር ለግኝቱ አስተዋጾ አድርጓል፡፡ #ለምሳሌ፡- የጫት አቅርቦት በ21% ቢቀንስም በዓለም አቀፍ ገበያ (ጅቡቲ) ያለው የጫት ዋጋ በ23% በመጨመሩ የመቻቻል አይነት አዝማሚያ አለው ማለት ነው፡፡
የውጪ ንግድ (Import)፡- በ2014 ኢትዮጲያ ከፍተኛ ሸቀጦች ከውጪ ሀገራት ሸምታለች፡፡ በ2013 ከነበረው 14.2 ቢሊየን ዶላር በ2014 ወደ 18.1 ቢሊየን ዶላር የደረሰ ሸመታ አድርጋለች ይህም ላለፉት 10 ዓመታት ከነበረው የእድገት ትሬንድ አንጻር በ27% ጨምሯል፡፡
ኢትዮጲያ የሸመተችባቸው ሀገራት ስብጥር ስንመለከት፡ ቻይና 18% ድርሻ እና ህንድ 15% ድርሻ ይዘው ቀዳሚዎች ላኪ ሀገራት ሲሆኑ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፤ ሳውዲ፤ ኪዌት፤ ቱርክ እና አሜሪካ እያንዳንዳቸው ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ቁሳቁስ ወደ ኢትዮጲያ ልከዋል፡፡
ኢትዮጰያ ከውጪ ላስገባቻቸው ቁሳቁሶች ወጪ መጨመር አንዱ ምክንያት ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ዋጋ መናር ነው፡፡ #ለምሳሌ፡- የነዳጅ ዋጋ በ83%፤ የእህል ዋጋ በ63% እና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በ98% ዋጋቸው ንሯል፡፡ ዋና ዋና ወጪዎች ሲታዩ ነዳጅ 3.3 ቢሊየን ዶላር ወጪ፤ እህል 2.2 ቢሊየን ዶላር ወጪ እና የአፈር ማዳበሪያ 1.4 ቢሊየን ዶላር ግዢ ተከናውኗል፡፡ እነዚህ ግዢዎች በሙሉ የተከናወኑት በመንግስት ነው፡፡
የግል ሴክተሩ ሸመታዎች በአብዛኛው በ2014 ቀንሰዋል፡፡ #ለምሳሌ፡- የማምረቻ ግብዓት ግዢ በ22%፤ መኪኖች በ17% እና የግል መጠቀሚያዎች በ1% ከ2013 አንጻር ቀንሰዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሸመታዎች ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ ያለባቸው የ Capital goods ላይ ሳይሆን ወደ ሌሎች ቁሶች ላይ ያዘነበለ ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ለግል ሴክተሩ የቀረበው የውጪ ምንዛሬ አናሳ በመሆኑ በግል ሴክተሩ የተደረገ ሸመታ ድርሻ ቀንሷል፡፡ #ለምሳሌ፡- የግብርና እና የማኒፋክቸር ተቋማት የማምረቻ ግብዓቶች (Capital goods) ሸመታ ከ2013 አንጻር በ1 ቢሊየን ዶላር ያህል ቅናሽ አላቸው፡፡ በርግጥ የውጪ ሸመታ መጠን ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት አንጻር ሲታይ ከነበረበት 13% ወደ 16% አድጓል፡፡
5.6K viewsWasyhun Belay, 16:53