2022-09-22 19:05:27
የዛሬ 40 ዓመት ጥርስ የሚነቀልበት ሂደት ብዙም ሳይለወጥ ጥርስ የማስነቂያ ዋጋ አሁን ላይ እጅግ ውድ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የ1980ዎቹ ክትፎ ከዘንድሮው ክትፎ ምንም ለውጥ ሳይጨመርበት በዋጋ ረገድ ውድ የሆነበት ምክንያት ምን ይመስላቸኋል? በትምህርት ጥራት እየቀነሱ ነገር ግን በዋጋ ውድ እየሆኑ ያሉ ኮሌጅ እና ዩኒቨርስቲዎች ምክንያታቸው ምን ይመስላችኋል?
ከ1970ዎቹ እስከ 2014 ድረስ ተመሳሳይ ዘፈን በየመድረኩ የዘፈነ ዘፋኝ ተመሳሳይ ስራ እየሰራ የሚከፈለው ክፍያ ለምን የጨመረ ይመስላችኋል? የዛሬ 25 ዓመት በተመሳሳይ የሰርግ ዘፈን የዳረ ዘፋኝ ዘንድሮ ያንኑ ዘፍኖ በብዙ እጥፍ ክፈሉኝ ለምን የሚል ይመስላችኋል? የዛሬ 20 ዓመት የነበሩ የግል ትምህርት ቤቶች የማስተማሪያ ዘዲያቸው ብዙም ሳይለውጡ እና ነባር አስተማሪዎቻቸው እየተጠቀሙ የዛሬ 20 ዓመት ከሚጠይቁት ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ ያስወደዱት ለምን ይመስላችኋል?
በጥራትም ሆነ በአዋጪነት ደካማ መሆናቸው እየታወቀ ለትምህርት ሴክተር፤ ለጤናው ሴክተር፤ ለደህንንት ተቋማት፤ ወዘተ ለምን ከፍተኛውን የመንግስታትን በጀት ድርሻ የሚወስዱ ይመስላችኋል?
ከላይ በዘመናት መካከል የአገልግሎት ዋጋዎች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ የመጡበትን ምክንያት እኔም እናንተ ልትገምቱ ከምትችሉት የዘለለ ምክንያት አላቸው ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን የአሜሪካዊውን ኢኮኖሚስት William Baumol ወሳኝ አርቲክል ማለትም #Cost_Disease (Baumol effect) የሚለውን ሳነብ በቀጣይ የአለም የኢኮኖሚ አካሄድ ባህሪ ልብ ሳይባል እየተለወጠ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡
William Baumol በ1960ዎቹ የሚሰሩ ሙዚቀኞች የተለየ ፈጠራን ሳይጨምሩ (Low productivity) ተመሳሳይ ስራዎች በመስራት የሚያገኙት ገቢ ግን በፍጥነት እያደገ መሄዱን አየ! ከዛ የ100 ዓመት መረጃዎችን (1865 እስከ 1965) ሲያጠና ተጨማሪ ፈጠራ ሳይኖራቸው ዘፋኞች በየመድረኩ የሚያስከፍሉት ክፍያ እየጨመረ ነበር፡፡
ስለዚህ "ሁለት አይነት ሴክተር በኢኮኖሚ ውስጥ አለ" አለ! በጣም የቴክኖሎጂ ፈጠራቸው እያደግ ያሉ እና በተጨማሪ የማምረት አቅም (Productivity) የደረጁት የአምራች/Manufacture ክፍሉ እና ብዙም የተለየ ፈጠራ እና የማምረት አቅማቸው እያደገ ያልሆኑት (Stagnant productivity) የአገልግሎት/Service ክፍል ናቸው ይላል፡፡
#ለምሳሌ፡- ከደርግ ዘመን ጀምሮ የቆዳ ጫማ የምርት ስርዓት ለማደግ የለፋውን ያህል ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በተመሳሳይ ጣባ የሚቀርበው ክትፎን ማወዳደር ማለት ነው (ከያኔው አንጻር አሁን ላይ የቂቤው ጥራት ቀንሶ ሊሆንም ይችላል!) ስለዚህ የአንድ ጫማ ዋጋ ጫማውን ለማምረት በየዘመኑ የተፈጠሩ የጫማ ቴክኖሎጂ እና ማሽኖችን መሰረት በማድረግ ውስን የዋጋ ጭማሪ ሊኖረው ቢችልም ምንም የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የአመራረት ሂደት የሌለው ክትፎ በየሬስቶራንቱ የሚጠየቅበት ዋጋ ከያኔው አንጻር ከፍተኛ ነው፡፡
ከታች ያለውን ግራፍ ተመልከቱት በአሜሪካ የ20ዓመት መረጃ ተወስዶ የአምራች ክፍሉ ዋጋ እና የአገልግሎት ክፍሉ ዋጋ ያላቸው ልዩነት ከፍተኛ ነው! የጫማ ዋጋ ከሚጨምረው በላይ የትምህርት ቤት ክፍያ ያድጋል፤ የአዳዲስ ዘመናዊ መኪኖች ዋጋ ከሚጨምረው በላይ ለህክምና የሚጠየቀው ዋጋ ውድ ነው፤ በየዘመኑ ለመጡ ለፈርኒቸር ውጤቶች ከሚጠየቀው ዋጋ በላይ ልጅ ለማስተማር የሚጠየቀው ዋጋ ውድ ነው፤ ወዘተ፡፡
በአምራች ክፍሉ ያለው ምርታማነት ማደግ ሰዎች ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኙ ስለሚያደርግ የመክፈል አቅም አላቸው (This is because the economy's constantly growing productivity simultaneously increases the community's overall purchasing power) የሚለው እሳቤ ለአገልግሎት የሚቀርቡ ሰዎችን ዋጋ እያናረው መጥቷል እንዲሁም ሰዎች በተቻለ መጠን ወደ አምራች ክፍሉ የስራ ዘርፍ ሊኖራቸው የሚችልን መዛወር ለመቋቋም በአገልግሎቱ ሴክተር ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን እዳይለቁ ለማባበል ሲባል የሚከፈላቸው ክፍያ እያደገ ሲሄድ ለአገልግሎቱ የሚያስከፍሉት እንዲያድግ ይደረጋል፡፡
በሀገራችን ከሆቴል ማናጀር ወይም ዋና ሼፍ እና ከጫማ ፋብሪካ ማናጀር በደሞዝ የሚሻለው ማን ነው?
William Baumol የመኪና አምራች ክፍሉ በጣም ዘመናዊ መኪኖችን እያመረተ ነው! ስለዚህ ፈጠራው ጨምሮ በሹፍርና ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች በራሱ መንቀሳቀስ የሚችል (Automated) መኪና ሲፈጠር ስራቸውን ያጣሉ! ነገር ግን ምንም ዘመናዊነት ቢያድግ ሰዎች ሃኪም፤ አስተማሪ እና ጸጉር ቆራጮችን በማሽን ሊተኳቸው አልያም እነዚህ የአገልግሎት ሴክተር ሰራተኞች ስራችንን ልናጣ እንችላለን ስለማይሉ የአገልግሎት ሴክተሩ ተሳትፎ እያደገ ይሄዳል ይላል፡፡
ረቦቶች/ማሽኖች እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እያደጉ መምጣታቸውን ተከትሎ በማምረቻ ተቋማት ያለው የሰራተኛ ቁጥር የመጨመር ሳይሆን የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ ነገር ግን በአገልግሎት ሴክተሩ ያለው ሰራተኛ በእጅጉ እያደገ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? በቀጣይ የዓለም ኢኮኖሚ ከአምራች ወደ አገልግሎት ሴክተር እየተዛወረ መሄዱ ጤነኛ የሚባል አይሆንም ይላል ምክንያቱም በአገልግሎት ሴክተሩ የሚከፈለው ከፍተኛ ክፍያ በአምራች ዘርፉ ያሉ ሰራተኞችን ማስኮብለሉ አይቀርም ነው፡፡
የመንግስታት የጤና እና የትምህርት ወጪ/በጀት እያደገ ሲሄድ ለሴክተሩ በተሰጠ ትኩረት ብቻ ይመስላቸዋል! ነገር ግን ሴክተሩ የሚጠይቀው ዋጋ እና ወጪ በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡
ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው የአምራች ክፍሎች/ፋብሪካዎች የሚጠቀሟቸው ማሽኖች የምርትን ጠቅላላ ወጪ ስለቀነሱት የምርቶች ዋጋ መቀነስ እያሳየ ነው ነገር ግን ከፍተኛ የማምረት አቅም የማይስተዋልበት የአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ ፈላጊ በመያዝ የአገልግሎት ወጪውም ክፍያውም ውድ እየሆነ ነው፡፡
#ለምሳሌ፡- ደሞዝ በማይከፈላቸው ረቦቶች የሚያመርት ካምፓኒ የማምረቻ ወጪው በሂደት እየቀነሰለት ነው የሚሄደው ስለዚህ የምርቱ ዋጋ እየቀነሰ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ቀጥታ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሴክተር (labor-intensive services) ውድ መሆናቸው ቀጥለዋል፡፡
ነገር ግን በሀገራችን ሁኔታው ይህንን ባህሪ ይይዛል ለማለት ከባድ ነው፡፡ የማምረቻ ዘርፉ የምርታማነት መጠን በሚፈለገው ልክ ሳያድግ/ኢኮኖሚው በአብዛኛው ለፍጆታው የሚያስፈልገውን የኢንዱስትሪ ውጤቶች ከውጪ ሸምቶ አስገቢ ሆኖ/ የግል ሴክተሩ ለትምህርት፤ ለጤና፤ ወዘተ የሚጠየቀው ክፍያ William Baumol በሚለው በተመሳሳዩ እያደገ ነው! ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ጠንካራ መሆን የሚገባው በአምራች እና በአገልግሎት ሴክተሩ መካከል ሊኖር የሚገባው እሽቅድድም ጤነኛ ሲያረግ ነው፡፡
የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንዲወደድ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት አለማለቁ ነው! ሁሌም ከሁኔታዎች አንጻር አመክንዮዎቹ ይቀነሳሉ! ይጨመራሉ! ዛሬ ላቀርብላችሁ የሞከርኩት ሃሳብ ትንሽ ግር የሚል ቢመስልም ዓለም ምርጥ የሚለው የኢኮኖሚክስ ሃሳብ ነው! በጽሁፍ ለመግለጽ የማያመቹ ቢሆኑም የተወሰነ ሞክሪያለሁ ተጨማሪ በማንበብ በደንብ መረዳት አልያም ማዳበር የምትፈልጉ ሰዎች ልትጨምሩበት ትችላላችሁ፡፡
3.0K viewsWasyhun Belay, 16:05