2022-09-16 19:38:29
የውጪ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ በመግባታቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ያጣሉ?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጪ ባንኮች ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መታሰቡን ተከትሎ ብዙ ሰዎች የሀገር ውስጥ ባንኮች ህልውና አሉታዊ ተጽኖ እንደሚደርስበት ያስባሉ! የሀገር ውስጥ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ሊያጡ ስለሚችሉ ይጎዳሉ የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ!
በመጪው ጊዚያት ውስን የሀገር ውስጥ ባንኮች ሊጎዱ ይችላሉ! ነገር ግን የሚጎዱት የውጪ ባንኮች ስለሚገቡ ወይም መሰረታዊ ደንበኞቻቸውን ስለሚያጡ ነው ብዬ አላስብም!
ለዚህ ውይይት እንዲረዳን የፋይናንስ ገበያውን ባህል እንመልከት! የቆጣቢው ህዝብ ብዛት፤ ሰዎች የሚቆጥቡበት/የባንክ ደብተር የሚከፍቱበት ምክንያት እና አማካይ ሰዎች በየባንክ አካውንታቸው እየቆጠቡ ያሉት የቁጠባ መጠን፤ ወዘተ፡፡
በተመሳሳይ የውጪ ባንኮች መሰረታዊ ትኩረት ቁጠባን በማሰባሰብ ለብድር ማቅረብ ሳይሆን ከተከማቸ ካፒታል ብድር በማቅረብ ከከፍተኛ የብድር ወለድ ትርፍ መሰብሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የሀገር ውስጥ ባንኮች ሰፊ የቁጠባ ስርዓት ላይ መሳተፋቸውን ከቀጠሉ ለብድር ሊያቀርቡት የሚችሉት ካፒታል ተቀማጭ ገንዘብ ሳያጡ በገበያው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
#ለምሳሌ፡- የውጪ ባንኮች በሀገር ውስጥ የማህበራዊ ተሳትፏቸው ደካማ ነው! እንዲሁም ዋና መስሪያ ቤት ላይገነቡም ይችላሉ! ምን ማለት ነው በተዘዋዋሪ በተደረገላቸው ጥበቃ ወይም ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በከፍተኛ ሁኔታ ወጪ በማውጣት የሚሳተፉ የሀገር ውስጥ ባንኮች በተወሰነ መልኩ ከተሳትፏቸው ሊቀንሱ ይችላሉ! ነገር ግን ከጠቅላላ ኢኮኖሚው ፋይዳ አንጻር የሚቻቻል ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ልብ በሉ አሁንም የውጪ ባንክ ሳይገባም የባንክ ሴክተሩን ፉክክር መቋቋም ያቃታቸው የሀገር ወስጥ ባንኮች አሉ! በተመሳሳይ ከ5 ዓመት በኋላ (ለአዳዲስ ባንኮች እስከ 7 ዓመት) መሟላት የሚገባው የ5 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ካፒታል ለሟሟላት ብዙ የሚቀራቸው ባንኮች ብዙ ናቸው፡፡
በርካታ ሃብቶቻቸውን ዋስትና በማስያዝ በቢሊየን እና በመቶ ሚሊየን ብድር ውስጥ ያሉ ደንበኞች እስከ 30 ዓመት የሚቆይ የእዳ ዋስትና ውስጥ በመሆናቸው በቀላሉ ከነባር የሀገር ውስጥ ባንኮች በመላቀቅ ከውጪ ባንኮች ዋስትና አስይዘው ብድር ለመውሰድ የሚያስችል አቅም ሊኖራቸው ስለማይችል የሀገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ተበዳሪ ደንበኞቻቸው እንደያዙ በገበያው ትርፋማነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
የውጪ ባንኮች መግባት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ለማቅረብ ድፍረት ወይም አሰራር ሊኖራቸው ስለማይችል ወደ ተለያዩ ታዳጊ ሀገራት ገበያ ሲገቡ ዝቅተኛ ብድሮች ላይ የመሳተፍ ልምድ ስላላቸው የሀገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ የብድር ጥያቄዎችን በማስተናገድ በገበያው ሊፎካከሩ መቻላቸው አይቀርም፡፡
ባንኮች ያለባቸው አደጋ የውጪ ባንኮች ከመግባታቸው በፊትም ለረጅም ዓመታት ለባለሃብቶች/ድርጅቶች ያቀረቡትን ብድር ወለድ እንጂ ዋናውን በመሰብሰብ የተመዘገበ ትርፋቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የመጪው ጊዜ ስጋታቸው ከውጪ ባንኮች ጋር ከመፎካከር በላይ እስካሁን ሲያቀርቡ የኖሩትን ዋናውን/Principal ብድር ማስመለስ ላይ ነው (ሁሉም ብድር በበቂ ዋስትና የቀረበ ነው ብሎ ማሰብ ጤነኛ አይደለም)፡፡
በባንኮች የቁጠባ ታሪክ ውስጥ ብዙ የባንክ ደብተር የሚከፍቱ ሰዎች እና በምክንያት ሳይሆን በሰዎች ጉትጎታ ብዙ አካውንት የሚከፍቱ ሰዎች በአካውንቶቻቸው የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ከፍተኛ ባለመሆኑ አዳዲስ የውጪ ባንኮች በገቡበት ቅስፈት ብዙ ሰዎች ተጨማሪ አካውንት ከውጪ ባንኮች ቢያወጡ ከፍተኛ ቁጠባ ወደ ውጪ ባንኮች የሚዛወር እና ከፍተኛ ቁጠባ ከሃገር ውስጥ ባንኮች የሚወጣ ሊሆን ይችላል ብዬ አላስብም፡፡
#ለምሳሌ፡- የሰዎች ልምድ በመሆኑ የመጀመሪያ ወራቶች ላይ የውጪ ባንክ አካውንት የሚኖራቸው ሰዎች ቁጥር እንደወረት መጨመሩ አይቀርም! በተመሳሳይ የሳፋሪኮም 07 መነሻ ሲም ካርድ የሚያወጣ ሰው ቁጥር ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡
መደበኛ የሀገር ውስጥ ባንኮች ገጠሩን ሲነኩ ስላልኖሩ እና የገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ የፋይናንስ አቅርቦት እየተሸፈነ ያለው በመደበኛ የዋስትና ማስያዣ ባለመሆኑ አደጋ በመጋራት የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ህልውና የውጪ ባንኮች በመግባታቸው ይበልጥ የሚፈተን ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን የገጠሩ ማህበረሰብ ንቃተ ህሊና እና ለአዳዲስ አሰራሮች የሚኖራቸው ተሳትፎ ፈጣን ባለመሆኑ ከተለመደው የብድር እና ቁጠባ የደንበኝነት መዝገቦቻቸው ወደ አዳዲሶቹ የውጪ ባንኮች ደንበኛ ለመሆን ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ ለማለት እንደሚያስቸግር ይሰማኛል፡፡
#ለምሳሌ፡- አዳዲስ የግብርና አሰራር (ምርጥ ዘር፤ መስኖ/ውሃ ማቆር፤ ኩታ ገጠም፤ የመኖ ዝርያ፤ ወዘተ) ለማስተዋወቅ በጣም ከፍተኛ ተግዳሮት የሚኖረው ከተለመደው የወጡ ልምዶችን ቶሎ ያለመቀበል ባህሪ በብዛት ስላል ነው)፡፡
የውጪ ባንኮች ባይመጡም ወደፊት ሁሉም የሀገር ውስጥ ባንኮች የተለመደውን ትርፋቸውን ይዘው ሊቀጥሉ አይችሉም! ውስን ባንኮች አሁንም በተሻሉ ባንኮች እየተዋጡ ነው፡፡ የስራ ማስኬጃ ወጪያቸውን እስከሸፈኑ ድረስ እንዳልወደቁ የሚያስቡ እንዲሁም ለባለአክሲዮን የትርፍ ክፍፍል መስጠት ተቸግረው/ዝቅተኛ መጠን የትርፍ ክፍፍል በተደጋጋሚ እያቀረቡ ያሉ ባንኮችን ታዘቡ፡፡
#ለምሳሌ፡- አንድ ባንክ በበቂ ሁኔታ ከፍተኛ ደሞዝ ለሃላፊዎቹ፤ ለሰራተኞቹ እና አበል ለቦርዶቹ እስከከፈለ እና የስራ ማስኬጃ ወጪውን እስከሸፈነ ድረስ አክሲዬን የገዙ ደንበኞች ምንም ትርፍ አላገኙም በሚል የሚጨነቅበት ደረጃ ምን ያህል ነው? በተመሳሳይ የባንከ ባለአክሲዮኖች ባንካችን የትርፍ ክፍፍል እየሰጠን አይደለም ስለዚህ ይቅርብን ቢሉ! ለሶስተኛ ወገን ከስረው ካላስተላለፉ በቀር አሰራሩ ቀላል ነው?
የውጪ ባንኮች ቢገቡም ባይገቡም ወደ ፊት የካፒታል ገበያው ሲከፈት አሁን ካለው በተሻለ የነባር/ውጤታማ ባንኮች አክሲሆን ለገበያ በሰፊው ሊዘዋወር ስለሚችል ባለአክሲዮኖቻቸውን እያጡ የሚመጡ ባንኮች እንዲሁም አዳዲስ ባንኮች ለመክፈት ለገበያ ለሚቀርብ አክሲዬን ለመግዛት ፍላጎቶቻቸው የሚቀንስ ትርፍ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሚመጣ አሁን ላይ ደካማ ባንኮች እስከ ጥምረት የደረሰ ስትራቴጂ ማሰብ መጀመር አለባቸው (ጠቅላላ ጉባዬ ላይ ባለአክሲዬኖች ይህንን የመፍትሄ ሃሳብ ቢያነሱ ስህተት ነው?)፡፡
በተቃራኒው የውጪ ባንኮች መግባትን እንደ እድል በመቁጠር በቴክኖሎጂ፤ በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ሃይል፤ በቀልጣፋ አሰራር፤ በደህንነት አመራር፤ በጥምረት ብድር የማቅረብ አሰራር፤ ወዘተ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ በጋራ ለማደግ ቀዳዳዎችን መፍጠር የሚችሉ የሀገር ውስጥ ባንኮች ለውጡን በብዙ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
6.7K viewsWasyhun Belay, 16:38