2023-06-09 07:45:22
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
"በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፤ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን"
ቆላስይስ 1፥10-11
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
✥••┈••●◉ ✞ ◉●••┈••✥
ዲያብሎስን ድል የምንነሣው እንዴት ነው
✥••┈••●◉ ✞ ◉●••┈••✥
➯ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ እንዳስተማረን ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት ፣ ምንም ዓይነት ረሀብና ቸነፈር ቢወርድብንም እግዚአብሔር እኛን መመገብ እንደሚቻለው በማመን ፣ በእጃችን ባለው ሀብት ንብረት ሳይኾን በእግዚአብሔር ስንመካ ፣ በሰው ሳይኾን በእግዚአብሔር ስንታመን ፣ ከእኛ ዓቅም በላይ ሳንጨነቅና የሚያስጨንቀንን ኹሉ ለመድኃኔዓለም አሳልፈን ስንሰጥ ዲያብሎስን ድል ማድረግ ይቻለናል፤ ስግብግብነትና የድኻውንና የምስኪኑን ማኅበረ ሰብዕ ንብረት መሻት በእኛ ላይ ሲሰለጥን ግን ዲያብሎስ ድል ያደርገናል፡፡
➯ ልጆቼ ! ሰይጣን አሁንም በሰዎች አድሮ ጌታችንን እንደፈተነው ይፈትነናል " እጅ ብትነሣልኝ ይህንና ይህን አደርግልሃለሁ " ይለናል፤ ጌታችን ዲያብልስን ድል በነሣው ጊዜ መጽሐፍ ሲናገር፤ ይኸውም ከዚያ በኋላ በሰዎች አድሮ ፈተነው እንጂ እርሱ ራሱ በቁሙ ሊፈትነው አልመጣም ሲል ነው፡፡
" እስከ ጊዜው ድረስ ተወው " ይላል፡፡
ሉቃ 4፥13
➯ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስን ድል ባደረገው ጊዜ "መላእክት መጥተው አገለገሉት" ይላል መላእክቱን ከዚያ በፊት እንዲመጡ አላደረጋቸውም፤ ይኸውም ሰይጣን "ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገኝ መላእክት ረድተውት ነው" ብሎ ምክንያት እንዳያመጣ ነው፡፡
➯ አንድም 'ዲያብሎስን እንዲህ ድል ስታደርጉ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ያገለግሏችኋል' ሲለን ነው፤ ይኸውም አልዓዛር ድህነቱን፣ በሽታውን፣ አጽናኝ ማጣቱን ፣ በአጠቃላይ የደረሰበትን ችግር ሁሉ ድል ሲያደርግ መላእክት መጥተው ወደ አብርሃም ዕቅፍ እንደወሰዱት ማለት ነው።
ሉቃ 16
➯ ልጆቼ ! ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለው፤ ዲያብሎስ የሚፈትነው በየገዳማቱ ፣ በየዋሻውና በየገደሉ ያሉትን ብቻ አይደለም፤ ዲያብሎስ በከተማ ላለነውም እንዲኹ ይፈትነናል፤ በገበያው ቦታ ይፈትነናል፤ በየወኅኒው ቤቱ ይፈትነናል፤ በቁሙ ራሱ ላይመጣ ይችላል፤ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ ፣ በራሳችን ምኞት አድሮም ይፈትነናል እንጂ፡፡
➯ ታዲያ ምን እናድርግ ? ፈጽመን አንመነው፤ ጆሯችንን አንስጠው አመስጋኝ መስሎ ቢመጣም ፈጽመን እንጥላው፤ አብዝቶ "ይህን ላድርግልህ" ቢለንም እኛም አብዝተን እንራቀው፤ ምክንያቱም በቀዳማይቱ ሔዋን ያደረገውን ስንመለከት አስቀድሞ ልቧ ከንቱ በኾነ ተስፋ እንዲሞላ አደረገ፤ ቆይቶ ግን በዚሁ "ተስፋ" ጣላት ፣ ታላቅ በደልም እንድትፈጽም አድርጓታልና፡፡
➯ ልጆቼ ! ዲያብሎስ እጅግ አረመኔ የኾነ ጠላት ነው፤ የተሰጠንን ጸጋ እስክንጥል ድረስ እኛን እንዲህ ባሉ ጦርነቶች አብዝቶ ይዋጋናል፤ ስለዚህ እንራቀው፤ በቃል ብቻ ግን አይደለም፤ በገቢርም እንጂ በሕሊና ብቻ አይደለም፤ በስራም ጭምር እንጂ፤ እርሱ የሚወደውን ሥራ ከመሥራት ፈጽመን እንከልከል፤ መከልከል ብቻ ግን በቂ አይደለም ፤ እግዚአብሔር የሚወደውንም ጭምር እናድርግ እንጂ፡፡
➯ ዲያብሎስ መጠነ ብዙ ተስፋ ሊሰጠን ይችላል፤ ኾኖም ይህን የሚያደርገው እኛን ለመውሰድ እንጂ ለመስጠት አይደለም፤ ከባባድ የስርቆት ወንጀሎችን ሠርተን ባለጸጋ እንድንኾን ይጋብዘናል፤ በዚህ ምድር ፍሬ ብቻ እንድንቀማጠል አግዝፎ ያሳየናል፤ ኾኖም ይህን የሚያደርገው ጽድቅ ከእኛ እንድትርቅ ፣ ደግሞም ሰማያዊውን ሀብት እንድናጣ ፈልጎ ነው፤ እዚህ ምድር ላይ ባለ ጸጋ ኾነን በላይኛው ቤታችን ለምነን እንኳን የማናገኝ ድኾች ሊያደርገን ሽቶ ነው፡፡
"የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል"
ምሳ 1፥33
" #ወአንቢበክሙ አንትሙ #ለዘኢያንበበ አይድኡ
➘ #እናንተ_አንብባችሁ_ላላነበበው_ንገሩ"
ምንጭ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ በድካሜ ብዛት ሳይገባኝና ሳይገባኝ በምጽፈው ድርሳንወ ገድላት መጽሐፍት ላይ የቃላት (የፊደል) ሕፀፅ ቢገኝ በጎደለው እየሞላችሁ በጠመመው እያቃናችሁ አንብቡ በረከት ተካፈሉ እላለሁ ከምንም ጊዜ በላይ ለሀገራችንና ለዓለም ሰላም እንዲሁም ለደካማው ወንድማችሁ እንድበረታ (የተጣልሁ) እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ
"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
───────────
Channel
https://telegram.me/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
───────────
1.1K views✞ ባሮክ ✞, 04:45