2023-05-01 12:50:20
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል እንጂ በዚኽ የለም"
ሉቃ 24፥5
"በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥
ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን"
ቆላስይስ 1፥10-11
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
ክፍል ፫
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ስለ ጋብቻ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ጋብቻና በብሉይ ኪዳን ዘመናት የነበረው እድገቱ
➯ በአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን የጋብቻ ትልቁ ዓላማ ኾኖ የምናየው ልጅ መውለድን ነው፤ በተለይ አርእስተ አበው በነበሩበት ዘመን ልጅ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነበር፤ ከሦስቱ አርእስተ አበው መካከል በአብርሃምና በያዕቆብ የምናየው ይህንን ነው፤ የታሪክ መጻሕፍቱ ላይ ግን ምንም እንኳን በዘመኑ የነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ ባይችሉትም ጋብቻ በአበው ከነበረው ደረጃ ጥቂት ከፍ ብሎ በአንድ ባልና በአንዲት ሚስት መካከል ብቻ እንዲከናወን ይፈለግ ነበር፡፡
➯ በጥበብ መጻሕፍት ደግሞ ልጆችን ከመውለድና ብዙ ሚስቶችን ካለማግባት በተጨማሪ አሁንም ከፍ ብሎ ልጆችን በአግባቡ ማሳደግ የጋብቻ ዓላማ ኾኖ መጥቷል፡፡
➯ ጋብቻ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ዘሥጋ መካከል ላለው ፍቅር ትእምርት መኾኑ በግልፅ ማስተማር የተጀመረው በነቢያት ዘመን ነው፤ በዚህ ዘመን ጋብቻ
“ልጆችን ወለድሁ፤ አሳደግሁም” ከሚለውና ልጆችን ከመውለድና በአግባቡ ከማሳደግ በተጨማሪ እግዚአብሔር እንደ ሙሽራ እስራኤልም እንደ ሙሽሪት ኾነው ቀርበዋል፡፡
ኢሳ 1፥2
➯ ከዚህ ኹሉ ማጠቃለል የምንችለው፥ የመዋትያን ጋብቻ ራሱ ምን ያህል (እስከ ሰዶማዊነት ድረስ) እየወደቀ እንደ ኼደ፣ እስራኤላውያን ትርጕሙንና ለምን እንደ ተሰጣቸው እንዲያውቁት ብዙ ክፍላተ ዘመናት እንደ ወሰደባቸው ነው፤ በርግጥ ይህ የኾነበት ዋና ምክንያት ምን እንደ ኾነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሮሜ መልእክትን በተረጎመበት ዓሥራ አንደኛው ድርሳኑ ላይ እንዲህ ያስረዳናል
“ከክርስቶስ መምጣት በፊት ሰውነታችን ኃጢአት በቀላሉ የሚያጠቃው ነበር፤ በሰው ልጆች ላይ ሞት ከተፈረደ በኋላ ቊጥር የሌላቸው ፍትወታትም አብረው ወደ ባሕርዩ ዘልቀው ገብተዋልና፤ ከዚህ የተነሣም ምግባር ትሩፋትን ለመያዝ መፋጠን ቀላል አልነበረም የሚረዳ መንፈስ ቅዱስ ወይም ኃይል የምትኾን ጥምቀት ገና አልነበሩምና፤ በታሰረለት ልጓም መሠረት የማይጓዝ ፈረስ እንዲሁ ወደ መራው እንደሚኼድና ደጋግሞ እንዲወድቅ ምን መሥራት እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሌለባቸው ይነግራቸው ዘንድ የተሰጠው ሕግም በቃላት ደረጃ ምክር ከመስጠት የዘለለ ኃይል አልሰጣቸውም ነበር”
የጋብቻ እድገት በሐዲስ ኪዳን
➯ በብሉይ ኪዳኑ እድገት ላይ እንዳየነው ጋብቻ በዘመናት ኺደት እያደገ መጥቷል፤ ሐዲስ ኪዳን ሲቃረብ ደግሞ የበለጠ እጅግ ከፍ አለ፤ የሐዲስ ኪዳን ምልክት ኾነው የመጡት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና መጥምቁ ዮሐንስ ደናግል ናቸውና፡፡
➯ ጌታችን ኃይለ ጥምቀትን ከሰጠ በኋላ ደግሞ ፍጹም ተለወጠ፤ ቀድሞ በብሉይ ኪዳን ኃይለ ጥምቀት ስላልነበረች በአንዲት ሚስት መጽናት ያቅት የነበረው አሁን ግን አንዲት ሚስትም መተው ወደሚቻልበት ዓቅም አደገ እስኪ በዘመናት ከፋፍለን እንየው
፩) በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን
➯ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር መጀመሪያ የኼደው ወደ ገዳም ነበር፤ በሌላ አገላለፅ የመጀመሪያው የቅድስና መንገድ አድርጎ ያሳየን ድንግልና (ምንኵስና) ነበረ ዳግማዊ አዳም እንደ መኾኑም፥ ቀዳማዊ አዳም ሊኖረው ይገባው የነበረውን ሕይወት ኖረ፡፡
ማቴ 4፥1
➯ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከቆየ በኋላም አገለግሎቱን የጀመረው በሰርግ ቤት ነው፤ በዚህም የድንግልና ሕይወትን መኖር ለማንችል ሰዎች የጋብቻ ሕይወትን ሲባርክልን ነው፤ መባረክ ብቻ ሳይኾን ሲያስተምርም እነ ረቢ ሒለልና ረቢ ሻማይ የተለያዩበትን ትርጓሜ ለጠየቁት ፈሪሳውያን አማናዊ ትርጕሙን ሰጣቸው፡፡
ዮሐ 2፥1-11
➯ ሰዎች በጋብቻ ላይ የነበራቸው እምነት እየተስተካከለ እንዲኼድና እግዚአብሔር ጋብቻን ለሰዎች የሰጠበት ዋና ዓላማ ዓላማቸውን አድርገው እንዲኖሩበት አስተማራቸው፤ እንዲህ በማለት
“ሙሴ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም”
ማቴ 19፥8
➯ “ስለ ልባችሁ ጥንከሬ” ማለትም ስለ በደላችሁ ስለ ኃጢአታችሁ ከዚሁ የተነሣም ስለ መድከማችሁ ሲል ነው፤ ባል ሚስቱን ሲጠላት ልቧን እያሸ የሚገድላት ስለ ኾነ ሴቲቱም ባሏን ስትጠላው መርዝ አጠጥታ ሥራይ አብልታ የምትገድለው ስለ ኾነች፥ ከሚገዳደሉ እንዲለያዩ ፈቀደላቸው፤ አሁን ግን ይህ ተከለከለ ፍቺ፣ ዝሙት ፈጽሞ የማይቻል ኾነ፡፡
➯ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታትን በተለይም የቆሮንቶስንና የኤፌሶን መልእክትን ስናያቸው ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ቢቻል ቢቻል ሰው ኹሉ እንደ እርሱ ድንግል እንዲኾን አስተማረ፤ ራሱን መግዛት የማይችል፣ የዝሙት ጠንቅ ያለበት ግን እንዲያገባ ፈቀደለት፤ ይህ ያገባ ሰውም ግን ቢያገባም አንድ ሰው ሳይርበው እንደማይበላ፣ ሳይጠማው እንደማይጠጣ፣ እንቅልፉ ሳይመጣ እንደማይተኛው ባለ ትዳርም ምንም እንኳን የሚያርፍበት አስተማማኝ ቦታ ያለው ቢኾንም፥ ፈቃዱ ሳያስቸግረው እንዲሁ እንዳገኘው ሩካቤ እንዳይፈጽም አስተማረው፤ ለጸሎት ሲተጉ፣ ሲጾሙ ይህን እንዳያደርጉ በስምምነት እንዲከላከሉ አዘዛቸው፤ ጸሎት የሌለበት ጊዜ ስለሌለም በተዘዋዋሪ ቢቻል ቢቻል አግብተውም ቢኾን ወደ ድንግልናዊ ሕይወት እንዲያድጉ መከራቸው፤ ሚስት ያለችው ሚስት እንደሌለቺው ይኹን አለ፤ ዝሙትንና ፍቺንም እጅግ አጥብቆ ተጸየፋቸው፡፡
፪) ከ2ኛው-5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን
➯ በዚህ ዘመን ውስጥ ጋብቻ እጅግ ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደገበት ነው፤ ከኹለተኛው ሦስተኛው ከሦስተኛውም አራተኛው መ.ክ.ዘ. ጋብቻ እጅግ ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደገበት ነው፤ ድንግልናና ጋብቻና ኹለቱ የቅድስና መንገዶች በቅዱስ አትናቴዎስ አጠራርም “ኹለቱም ጸጋዎች” በተለይም በአራተኛው መ.ክ.ዘ. እጅግ የተመነደጉበት ነው፡፡
➯ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ጥንቱንም የነበረ ቢኾንም በቀጰዶቅያ አባቶች ይበልጥ እንደ ተብራራ ኹሉ፥ የድንግልናና የጋብቻ ትምህርትም ይበልጥ የተብራራው በዚህ ጊዜ ነው፤ የድንግልና ሕይወት ወደ ምንኵስና ያደገው በዚህ ጊዜ ነው፤ የድንግልና ሕይወት መምራት ያልቻለው ደግሞ የጋብቻ ሕይወቱን ትንሽዋ ቤተ ክርስቲያን በማለት በትንሽዋ ቤተ ክርስቲያን በሚያደርጋቸው አገልግሎቶች ድኅነቱን እንዲፈጽም የተደረገው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
➯ ለዚህ ዋና ምክንያት ተብሎ የሚጠቀሰውም ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ስለ አባ እንጦንስ የጻፈው ገድል ነው፤ ገድሉ በጊዜው ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጐሙም ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
654 views✞ ባሮክ ✞, edited 09:50