Get Mystery Box with random crypto!

ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

የቴሌግራም ቻናል አርማ ortodoxmezmur — ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit
የቴሌግራም ቻናል አርማ ortodoxmezmur — ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit
የሰርጥ አድራሻ: @ortodoxmezmur
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 136.15K
የሰርጥ መግለጫ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ አሜን።
. ዝማሬ ዳዊት
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተምህሮና ስርዓትን የጠበቁ ትምህርቶች, መዝሙራት እና ወረባትን ከነዜማቸው ለማግኘት ቻናላችንን ይጎብኙ።
ለማንኛውም ሀሣብ, ጥቆማ, አስተያየት
@zmaredawit_messengerbot ላይ
ቢያስቀምጡልን ይደርሰናል

Ratings & Reviews

3.67

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

2

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 4

2024-03-09 21:02:35 ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ መጽሐፏ እንደምታስተምረን፣ ኃጢአትና ዲያብሎስ የአንድ ሳንቲም _ ሁለት ገጽታዎች ናቸው፤ ይህም ማለት ዲያብሎስ ባለበት ኃጢአት አለ ፤ ኃጢአት ባለበትም ዲያብሎስ አለ ማለት ነው፤ እነዚህ ሁለቱ የሚለያዩ አይደሉም፤ የመጨረሻ ግባቸው ደግሞ ሰውን መጣል ነው፡፡ዲያብሎስ የሰውን ደካማ ዝንባሌ ወይም በሆነ ነገር መጐምጀትን በሰው ሲመለከት ያንኑ የጐመጀበትን ክፉ ምኞት እንዲፈጽም፣ በረቂቅ የሰው ኅሊና ውስጥ ገብቶ በከፍተኛ ደረጃ ይገፋፋል፤ ሰውም በራሱ የመጐምጀት ዝንባሌና በዲያብሎስ ግፊት ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ጐጂ የሆነውን ድርጊት ይፈጽማል ፤ ቀጥሎም ድርጊቱ በእግዚአብሔር ፊት በደል ይሆንና ከእግዚአብሔር ይለየዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትንና ክብርን ጨምሮ ብዙ መልካም ነገርን ያጣል፤ ኃጢአት የሚባለውም ይህ ነው፤ በቀደሙት አባትና እናት ማለትም በአዳምና ሔዋን የተከሠተው ነገርም ይኸው ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ኃጢአትን በጽድቅ፣ ዲያብሎስን በጾም በማሸነፍ የአሸናፊነትን መንገድ ሊያሳየን የመጣው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳምና በሔዋን የተፈጸመው ውድቀት እንዴት እንደሚቀለበስ በዚህ ጾም አስተምሮናል፡፡ ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ፤ ዲያብሎስም መራቡን አይቶ ይጐመጅልኛል ብሎ በምግብ ፈተነው፡፡ የጌታችን መልስ ግን ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ የሚል ነበረ፣ በተመሳሳይም በፍቅረ ንዋይና በአምልኮ ባዕድ ፈተነው የጌታ መልስ ግን በተቃራኒው ነበረ፡፡

ዲያብሎስ በሦስቱም የማስጐምጃ ፈተናዎች ጌታ ሊሸነፍለት ካለመቻሉም በላይ "አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ" ብሎ ሲገሥጸው ተሸንፎ ትቶት ሂዶአል፡ በአሸናፊነቱ የተደሰቱ መላእክትም ወዲያውኑ መጥተው በክብረ አምልኮ አገለገሉት፤ በዚህ ድርጊት የምንመለከተው እውነታ ቀዳማይ አዳምን ባሸነፈበት ስልት ዳግማይ አዳም ክርስቶስን ለመጣል ዲያብሎስ የሄደበትን ርቀት በአንድ በኩል ስናይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የቀዳማይ አዳም ተሸናፊነትና ውድቀት ለመቀልበስ ያሳየውን ጥብዓት እናያለን፡፡

በዚህም የቀደመው ውድቀት በኋለኛው አሸናፊነት ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ፣ ዲያብሎስ ጓዙን ጠቅልሎና ተስፋ ተስፋ ቆርጦ መሄዱን እናስተውላለን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ጌታችን የአሸናፊነትን መንገድ በቃልና በተግባር አስተምሮናል፤ አሳይቶናልም፤ ይህንም ያደረገው እሱ አሸንፎልናል እያልን ለመኵራራት ሳይሆን፣ በእሱ ኃይል እየታገዝንና እሱ ባሸነፈበት ስልት እየተጠቀምን እንድናሸንፈው ነው፡፡ ሰይጣን የሚሸነፍበት ስልት በሌላ ሳይሆን፤ ሥጋዊ መጐምጀትን ከአእምሮአችን አውጥተን በመወርወር ነው፡፡

ሥጋችን በፍቅረ ንዋይ፣ በሥልጣን፣ በዝሙት እንደዚሁም በተለያዩ ሥጋዊ ምኞቶች ሊጐመጅ ይችላል፤ ያን ጊዜ ሰይጣን እነሱን እንድንፈጽም ሊገፋፋን ከበኋላችን እንደቆመ እናስብና "አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሃድ” እንበለው፡፡ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ያስጐመጁን ነገሮችን ከኅሊናችን አውጥተን በመጣል እሱን ማሸነፍ አለብን፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ይሸሻል፤ መላእክትም ወደኛ መጥተው ይረዱናል፣ ይጠብቁናል፤ ያግዙናል፣ ያድኑናል፡፡ ዲያብሎስ የሰዎችን የመጐምጀት ዝንባሌን ተከትሎ በመገፋፋት ዛሬም ዓለማችንን ለከፋ ውድቀት እየዳረጋት ነው፣ ሀገራችንን ጨምሮ በየአካባቢው የሚቀሰቀሱት አለመግባባቶችና ግጭቶች መንሥኤያቸው ከመጐምጀት ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ግማሹ በሥልጣን፣ ግማሹ በሀብት፥ ግማሹ በራስ ወዳድነት፣ ግማሹ ደግሞ የበላይ ለመሆን በሚል እሳቤ የሰው ኅሊና በክፉ ምኞት ይጐመጅና በዲያብሎስ ገፋፊነት ወደ ተግባራዊ ጥፋት ይገባል፡ በውጤቱም ሰው ይጎዳል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ጾም ማለት እህልንና የእንስሳት ውጤቶችን ከመመገብ መከልከል ብቻ አይደለም፣ የእንስሳት ውጤት የሆኑትን ላለመመገብ ከምንወስነው በላይ እኩያት ፍትወታትንና ኃጣውእን ላለማስተናገድ በቁርጥ መወሰን ይጠበቅብናል፡፡ ስንጾም መገዳደልን፤ መጣላትን መለያየትን፤ መገፋፋትን በሆነ ነገር መጐምጀትን እርም ብለን በመተው ዲያብሎስን የምናሸንፍበት የአሸናፊነት ኅሊና መላበስ አለብን፣ ከክፉ ኅሊና እና ተግባር የተለየን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጎ ነገርን ለመስራት በእጅጉ መበርታት ይጠበቅብናል፡፡

ዲያብሎስ ተስፋ ቆርጦ የሚሸሸው ይቅር ይቅር ስንባባል፤ ለሰላምና ለአንድነት፣ ለፍቅርና ለስምምነት ስንቆም ነው! ከዚህም ጋር በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ጸያፍ የሆነው ግብረ ኃጢአት በዚህች ምድር እንዳይፈጸም ማኅበረ ሰባችን በተጠንቀቅ ሲቆም ነው፤ እንደዚሁም ደም መፋሰስ፣ አለመተማመንና በሴት ልጆቻችን የሚደርስው አካላዊ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ ጥቃት ሲቆም ነው፡፡ ጾማችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ መኖር ሲችሉ፣ የተራቡት ሲደገፉ፣ ፍትሕ ያጡት ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡

ይህ ዓይነት መልካም ሥነ ምግባር በእያንዳንዱ የማኅበረሰብ አእምሮ ቦታ አግኝቶ ሲተገበር ትክክለኛውን ጾም ጾምን ማለት እንችላለን፣ ዲያብሎስም በእርግጠኝነት በዚህ ይሸነፋል፤ የሰው ጣዕመ ሕይወትም በዚህ ይለመልማል! ምድሪቱም በእግዚአብሔር በረከት ትሞላለች፡፡ ይህን ቅዱስ ተግባር በወርኃ ጾሙ በደንብ እንድንተገብረው ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለኦርቶዶክሳዊው ማኅበረሰብ መንፈሳዊና አባታዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም

በሀገራችን ረሃብ የሚያጠቃቸው ወገኖች በበዙበት በአሁኑ ወቅት፤ ሳንመጸውት ጾምን ጾምን ማለት ማጣፈጫ ወጥ የሌለው ምግብ መመገብ ማለት ስለሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የቁርስ በጀቱን ለተራቡ ወገኖች በመለገስ ወገኖቹን በረሃብ ከመሞት እንዲታደግ ወቅታዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የጾም ወቅት ያድርግልን! እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ !! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
15.5K views18:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-09 21:02:34
"ጾማችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ መኖር ሲችሉ፣ የተራቡት ሲደገፉ፣ ፍትሕ ያጡት ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡"
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ 2016 ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ሁሉ የምትገኙ ምእመናንና ምእመናት ልጆቻችን በሙሉ!

እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

“ወእምዝ ኃደጎ ዲያብሎስ ወናሁ መጽኡ መላእክት ይትለአክዎ፡- ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ እነሆም ያገለግሉት ዘንድ መላእክት መጡ›› (ማቴ ፬፲፩)፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተመሥጦ የምንጾመው ጾም፣ ጾመ ኢየሱስ ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ጾም በጥንት ጊዜ ሰው በኃጢአት የወደቀበትን ምክንያት፣ እንደዚሁም ሰው ኃጢአትንና ዲያብሎስን እንዴት እንደሚያሸንፍ ጌታችን እኛን ያስተማረበት ጾም ነው፡፡
13.1K views18:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-09 19:42:41 ​​​​ዐቢይ ጾም

ጾም ማለት ሰውን ከምግብ መከልከል ነው፡፡ (ፍትሃ ነገስት አንቀፅ.15) “ጾምሰ ተከልኦተ ብዕሊ ዕምመብልዕ በጊዜ እውቅ” ጾም ማለት በታወቀው ዕለት በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡

መብል መጠጥ የኀጢአት መሠረት ነው በመብል ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ላይ መጣ “ይችን ዕፀ በለስ ብትበሉ ሞትን ትሞታላችሁ” ዘፍ.2፥17 ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው። መብል መጠጥ ከልክ ሲያልፍ ከተዘወተረም ከእግዚአብሔር ይለያል፤ “ያዕቆብ በላ ጠገበ ወፈረ ገዘፈ ደነደነ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ” ዘዳ.32፥15-17 “የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም” ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 “ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና ማቴ.5፥6 ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ “ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት መዝ.68፥10

ጾም በነቢያት የተመሠረተ በክርስቶስ የጸና በሐዋርያትም የተሰበከና የተረጋገጠ ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረን ይህን ጾም ከምግብ ለመከልከል ጋር ጸሎትን፥ ስግደትን፥ ምጽዋትንና የንስሐ ዕንባን ጨምረን እንጹመው፡፡ ጌታችንና ነቢያት፣ ሐዋርያት የተውልን መንፈሳዊ መሣሪያ ነውና፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርዓያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴ.6-16፡፡ ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን፡፡

የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች የሚከተሉት ናቻው ፡-

ዐቢይ ጾም
ባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል፡፡

ጾመ ሁዳዴ
በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡

የካሳ ጾም
አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ካሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ፡፡

የድል ጾም
አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴ. 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡

የመሸጋገሪያ ጾም
ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡

ጾመ አስተምህሮ
ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2

የቀድሶተ ገዳም ጾም
ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ /በገዳመ ቆሮንጦስ/ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡

የመዘጋጃ ጾም
ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡

የሥራ መጀመሪያ ጾም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በምድር ሳለ ስብከት፣ ተዓምራት ከመጀመሩ በፊት የጾመው ጾም ነውና የሥራ መጀመሪያ ጾም ይባላል።

ሼር
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
16.8K views16:42
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-08 21:47:53 ሰላም ውድ የዝማሬ ዳዊት ቻናል ተከታታዮች በእግዚአብሔር ፍፁም ሰላምታ እንደምን ሰነበታቹ? አሜን! የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!

እንደሚታወቀው ፊታችን ታላቁ የዐቢይ የጾም ወቅት ነው በመሆኑም
ስለ ዐቢይ ጾም ምንነት
እያንዳንዱን ሳምንታት ስም፣ ምንነት እና ትርጉም
እንዲሁም የጾም፣ የበገና መዝሙራትን ወደናንተ ለማድረስ ዝግጅቱን ጨርሷል

ይህን መልዕክት ለሁሉም ሰው #ሼር በማድረግ እንዲዳረስ የማድረግ ሃላፊነት የናንተ ነው።

@ortodoxmezmur
16.1K views18:47
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-06 22:34:33 ​​አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ!

አንድን የሥጋ ቁስል ለመፈወስ ለእያንዳንዱ ሰው ከባድ ነው፤ የነፍስን ቁስል መፈወስ ግን ለኹሉም ቀላል ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ለመፈወስ መድኃኒት ብሎም ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነፍስን ለመፈወስ ግን ቀላል ብሎም ወጪን የማይጠይቅ ነው፡፡ ሥጋን ከዚያ ከሚያሰቃይ ቁስሉ ለመፈወስ አድካሚ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀዶ ጥገና ምላጭ መቀደድ አለበት፤ መራራ መድኃኒቶችም ሊጨመሩበት ይገባል፡፡

ነፍስን ለመፈወስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አያስፈልግም፡፡ ፈቃደኛ መኾን ብቻ በቂ ነው፤ ፍላጎቱ ካለ ኹሉንም ነገር ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የእግዚአብሔር መግቦቱም እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው፡፡ ሥጋ ቢቆስል ያን ያህል ከባድ ጉዳትን አያመጣብንም፤ ምክንያቱም ምንም ባንታመምም እንኳን ሞት መጥቶ ይህን ሥጋችን ያፈርሷል፤ ያበሰብሷልምና፡፡ ነፍሳችን ብትታመም ግን ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር የነፍስን ሕመም ለመፈወስ መድኃኒቱ ቀላል፣ ምንም ወጪና ስቃይ የሌለበት ያደረገውም ስለዚሁ ነው፡፡

ታዲያ ምንም እንኳን በሕመሙ ምክንያት የሚያገኘን ጉዳት ያን ያህል ብዙ ባይኾንም የገንዘብ ወጪን የሚጠይቀው፣ ሐኪም የሚያስፈልገው፣ ብዙ ስቃይ ያለበት ሥጋችን ሲታመም እርሱን ለማከም እጅግ የምንደክም ኾነን ሳለ፥ እጅግ ብዙ ጉዳት የሚያመጣውን፣ እርሱን ለመፈወስ ወጪ የማይጠይቀውን ፣ ለማስታመም ሌሎች ሰዎች የማያስቸግረውን፣ እንደ ምላጩና እንደ መራራ መድኃኒቱ ስቃይ የሌለበትን ይልቁንም ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ሳይፈልግ በእኛ ኃይል ባሉ ምርጫና ፈቃድ ብቻ መዳን የሚችለውን፣ ይህን ማድረግ ሳንችል ስንቀርም ከባድ ፍርድና ቅጣት ስቃይም እንደሚያገኘን በእርግጥ እያወቅን የነፍሳችንን ቁስል ችላ የምንል ከኾነ ሊደረግልን የሚችል ምሕረት እንደ ምን ያለ ምሕረት ነው? እኮ የምናገኘው ይቅርታ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ነው?

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ - በእንተ ሐውልታት መጽሐፍ #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ

@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
15.0K views19:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-05 22:28:26 ​​#ትንሽ_ይበቃኛል
አስተማሪ ታሪክ

በአንድ የገጠር መንደር በቤተሰቦቻቸው የእርሻ ማሳ በጋራ እያመረቱ የሚተዳደሩ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ #አንደኛው ትዳር መስርቶ ብዙ ቤተሰብ የሚያስተዳደር ሲሆን አንደኛው ግን ገና አላገባም፡፡ ብቻውን ነው የሚኖር፡፡ በምርት መሰብሰቢያ ወቅት ያገኙትን ምርት እኩል ይካፈሉም ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ትዳር ያልመሰረተው ለእራሱ እንዲህ አለ፡፡ “ያገኘነውን ምርት እኩል መካፈል ፍተሃዊ አይደለም፡፡ እኔ ብቻየን ስለሆንኩ ትንሽ ነገር ነው ሊበቃኝ የሚችለው፡፡” እንዲህ ብሎ መሸት ሲልለት ጨለማውን ተግን አድርጎ ከጎተራው ኬሻ ሙሉ ጥራጥሬ እያነሳ በቤታቸው መካከል ባለው መስክ አቋርጦ ከወንድሙ ጎተራ ይሞላለት ነበር፡፡ በተመሳመሳይ ሁኔታ ትዳር የመሰረተው ወንድሙም ለእራሱ እንዲህ ይላል “ምርታችንን እኩል መካፈላችን ትክክል አይደለም፡፡ ሁኖ ሁኖ እኔ ባለ ትዳር ነኝ በመጭዎቹ ዓመታት አንዳች ነገር ቢፈጠር እንኳን ልጆቼና ሚስቴ ይንከባከቡኛል፡፡ ይሄ ወንድሜ ግን ብቻውን ነው፡፡ ማንም የሚንከባከበው የለውም ስለሆነም” አለና መሸት ሲልለት ጨለማውን ተግን አድርጎ ኬሻ ሙሉ ጥራ ጥሬ እየወሰደ ከላጤ ወንድሙ ጎተራ ይጨምራል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያሉ ዓመቱ ተጋመሰ፤ የእህል ጎተራቸው ያልቀነሰበት ምክንያት ግን እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡ ከዛም አንድ ቀን ምሽት ሁለቱም እንደልማዳቸው አንደኛው ላንደኛው ኬሻ ሙሉ ጥራጥሬውን ይዘው ሲተላለፉ ሁኔታዎች ተገጣጠሙና መንገድ ላይ ይጋጫሉ፡ ቀስ አድርገው ሸክማቻን አውርደው ሲተያዩ ወደንድማማቾቹ ነበሩ፡፡ በልባዊ ፍቅር ተቃቀፉ፡፡

#ጭብጥ - ፊት ለፊት ተነጋግረው የበለጠውን አንደኛው መውሰድ እንዲችል ማድረግ ጠፍቷቸው አይደለም ግን አንተ ትብስ አንተ ትብስ እየተባባሉ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደማይችሉ ስላወቁ የፈጠሩት መላ ይመስላል፡፡

እንኳንስ ስጡ ሳይባሉ ለመስጠት መፍቀድ ቀርቶ ቢጠየቁ እንኳ እኩል ድርሻየ ነው ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የበለጠውን ለመስጠት መሻት ከልባዊ ፍቀር ውጭ ሊመጣ አይችልም፡፡ ለሰጨውም ሆነ ለተቀባዩ ሳይቀንስ የሚሰጥ ስጦታ ቢኖር ልባዊ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ፍቀር ይስጠን፡፡

ለእህት ወንድሞች ይማሩበት ዘንድ አጋሩ
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
12.6K views19:28
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-02 10:59:17
@ortodoxmezmur
የአድዋ ጦርነት አዋጅ ደብዳቤ

የአድዋን በዓል መላው ሕዝብ በሰላም የሚያከብርበት ግዜ እሩቅ አይደለም።
20.4K viewsedited  07:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-01 22:18:16  
አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘከር የሚፈልግ ትውልድ መጣ፡፡ አድዋ ነጻነት ነው፤ አድዋ የሰው ልጆች የከፍታ፣ የእኩልነት ምልክት ነው፤ አድዋ የአሸናፊዎች ዓርማ ነው፡፡ አድዋ አንድነት የታየበት፣ የመለያየት ግንብ የፈረሰበት፣ ንጉሥ ከሠራዊቱ፣ ካህናት ከታቦቱ፣ ሳይለዩ በጋራ ለነጻነት የተሰለፉበት፣ የብርቱዎች ሰልፍ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የአድዋ ባለቤቶች ተገፍተዋል፤ ለፍላጎታቸው ባሪያ የሆኑ በተሸናፊው ጣሊያን ሐሳብ የተማረኩ፣ ኢትዮጵያዊ ሳሉ በግብራቸው ጣሊያናዊ የሆኑ አሸናፊዎቹን ሲሳደቡ የማይደነግጡ አንደበታቸው ያልተገራ፣ ውኃ የሌለባቸው ጉድጎዶች፣ ዝናብ አልባ ደመናዎች ዛሬ አገሩን ሞልተውታል፡፡
 
ታሪክ መሥራት አቀበት የሆነባቸው ታሪክንና ባለ ታሪኮችን የሚያዋርዱ፣ የድሉ  መሐንዲስ፣ የጦሩ ፊታውራሪዎችን የሚያናንቁ፣ ድንቁርናቸው በሱፍና በከራባት የተሸፈነ ብዙዎች ዛሬ የአድዋ ባለውለታዎችን ያራክሳሉ፤ ቤተ ክርስቲያንንም ከአድዋ ነጥለውና ውለታዋን አቃለው ይናገራሉ፡፡ አይችሉም እንጂ ክብሯን ለመዳፈር፤ ልዕልናዋን ለዋረድ ይመረምራሉ፤ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር እህል ላበደረ አፈር›› የሚሉት ብሂል ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፈጽሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከአድዋ ለመነጠል ጥረት ተደርጓል፡፡
 
በጥቅሉ አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርበኞቿን አስተባብራ ባዕዳንን አሸንፋ ጠማማ ልጆቿን ማሸንፍ ተስኗታል፡፡ የሀገር አንድነትን የጠበቀች በአንድነት መቆም ርቋታል፡፡ ቁሳዊ ፍላጎቱን ያሸነፈ፣ ለእግሩ ጫማ ለሰውነቱ ሸማ የማይጨነቅ፣ ለሀገርና ለሃይማኖት ቅድሚያ የሚሰጥ ማኅበረሰብ የፈጠረች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የቁስ ፍላጎታቸው ጦር ሆኖ የሚወጋቸው አገልጋዮች ሞልተዋታል፡፡ ይህም ለታሪካዊ ጠላቶቿ በቀል በር የከፈተባት ትልቁ ክፈተት ነው፡፡
 
አድዋ አንድነት ነው፤ አድዋ እኩልነት ነው፤ አድዋ ነጻነት ነው፡፡ አድዋ የድሉ ባለቤቶችን መዘከር ነው፡፡ እነዚህን ዘንግቶ፣ የድሉ ፊታውራራዎችን በማንኳሰስ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሚና በመዘንጋት የሚከበር የአድዋ በዓል ትርጉም አልባና ታሪክን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡   

@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
13.5K viewsedited  19:18
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-01 08:48:12
ሰይጣን ጾመኛ ነው በተፈጥሮው መልአክ ነበርና። ሰይጣን ድንግል ነው እንደ ሰው አይጋቡምም አይወልዱምምና። ትህትና ስለሌለው ግን ወደቀ!

አንተም ጾመኛም ብትሆን ድንግልም ብትሆን ትህትና ከሌለህ ግን ከሰይጣን እኩል ነህ።

"እግዚአብሔር ስለ ንጽሕናው /ድንግልናው/ ከሚመካ ጻድቅ ይልቅ ስለ ዝሙቱ የሚያለቅስ ኃጥያተኛን ይወዳል።"

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
15.7K viewsedited  05:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-28 21:43:33 1. የተከበራችሁ አበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ እንዳለ በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ምእመናንን አቅጣጫ በመስጠት የቀደሙ አባቶቻችሁን ፈለግ በመከተል ዛሬም በጽናት እንድትተጉ፤ ያከበረቻችሁን ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ሆናችሁ እንድትጠብቁ በልጅነት መንፈስ በትሕትና እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም የአባትነት የዋህ ልቦናችሁን በመጠቀም ያዘኑ፣ የጠቀሙ፣የተቆረቆሩ መስለው ቀርበው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈጸም የሚጥሩ ስለሚኖሩ ሁሉንም በጥንቃቄ እንድትመረምሩ፤ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በመዋጀት አንድነታችሁን እንድታጠነክሩና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ስለሚፈጠሩ ችግሮች በጥልቀት እንድትወያዩና እንድትመካከሩ እናሳሰስባለን።

2. ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅማት ጉዳይ የግል ፍላጎትንና ምድራዊ ዓላማን መሠረት አድርጋችሁ ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ቀኖና ውጭ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን ለመተካት፣ ፓትርያርክ ለመሾምና የመሳሰሉትን ለመፈጸም የምትንቀሳቀሱ አንዳንድ አባቶች ከድርጊታችሁ እንድትታቀቡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ማኅበራችን ይህንን ጉዳይ እየተከታተለ መረጃውን ለምእመናን የሚያደርስ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡

3. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናት ሆይ በጸሎትና በትምህርት ምእመናንን በማጽናናት፤ ከእውነት ጋር በመቆም እውነታውን በማሳየት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ በማድረግ ድርሻችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን።

4. ውድ ምእመናንና የማኅበራችን አባላት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ከአሳዳጆቿ የመጠበቁ ዋነኛ ኃላፊነት በዘመኑ ባለን ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርሰቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ሁላችን እጅ ላይ ወድቆአል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለአባቶችና ለካህናት ትተን “እኔ አያገባኝም፤ አይመለከተኝም” ልንል አይገባም፡፡ ሁሉም በየድርሻው ቤተክርስቲያኑን ለመጠበቅ መትጋት አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥፋትና ሊመጣ ያለውን ፈተና አስቀድሞ በመረዳት ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በወሰነው መሠረት በየአጥቢያችን፤ በተለያየ መልኩ በመደራጀት፤ በቤተክርስቲያን ላይ ጥፋት ለማድረስ የሚመጡትን በመከላከል የቤተ ክርስቲያንን ስደት ለማስቆም መንፈሳዊ ግዴታችንን እንድንወጣ እንጠይቃለን፡፡

5. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልዩ ልዩ አገልግሎት እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ማኅበራትና ሌሎችም ሁላችንም አንድነታችንን በመጠበቅ በጋራ አገልግሎቶችን በመፈጸም ድርሻችንን እንድንወጣ ለተግባራዊነቱ ጥሪ እናቀርባላን፡፡

6. ገዳም ድረስ ገብቶ መሣሪያ ያልያዙና: ራሳቸውን እንደሞቱ ቆጥረው እየኖሩ ያሉ መነኮሳት ላይ ግድያ የፈጸመ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል (መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ: በግልም ይሁን በቡድን: አማኝም ይሁን ኢአማኝ) ድርጊቱ ከሰውነት ተፈጥሮ የወጣ ነው፡፡ ምናኔንና የክህነት ክብርን በተቃረነ መልኩ ሰብእና የጎደለው ጥቃት ማድረስ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም፡፡ ጥቅም የሌለው ከንቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ጤነኛ በሆነ አእምሮ ታስቦ የተፈጸመ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ማስተዋል ተወስዶባቸው እውቀት ተሰውሮባቸው እንጂ ይህንን ማድረግ ቀርቶ ማሰቡም የሙት ሐሳብ ነው፡፡ ቀድሞ የሞተው ሟቹ ሳይሆን ገዳዩ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲበዙ እንጂ ሲያንሱ በታሪክ አልታየም:: ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ሲያጠነክር እንጂ ሲያዳክም ታይቶ አይታወቅም፡፡ መጽሐፍ “ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንን ቤት ገፋው በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያን በጽኑ ዐለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነ አታሽነፏትም። ዲዮቅልጥያኖስም አላጠፋትም:: ዲያብሎስም ዝናሩን እንዲሁ ጨረሰ:: ስለዚህ አትድከሙ: አትሳቱም እናንተ ሳትወለዱ የነበረች ቤተ ክርስቲያን እናንተ አልፋችሁም እንደ እናንተ ላሉት በስሑት መንገድ ለሚጓዙት ሁሉ እየጸለች ትቀጥላለች:: ሐሳቧም፣ ሥራዋም፣ ዓላማዋም፣ ግቧም ሰማያዊ ነውና።

በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ህልውና በላይ የሚያስቀድመው አንዳች ነገር የሌለ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመናበብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣማ እያሳወቅን፥ የሁላችንም የመሰባሰብና የአገልግሎት ማእከል ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተን ሊመጣ ካለው አደጋ ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ ኀላፊነት በትጋት እንወጣ ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡
13.4K views18:43
ክፈት / አስተያየት ይስጡ