Get Mystery Box with random crypto!

  አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘከር የሚፈልግ ትውልድ መጣ፡፡ አድዋ ነጻነት ነው፤ አድዋ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

 
አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘከር የሚፈልግ ትውልድ መጣ፡፡ አድዋ ነጻነት ነው፤ አድዋ የሰው ልጆች የከፍታ፣ የእኩልነት ምልክት ነው፤ አድዋ የአሸናፊዎች ዓርማ ነው፡፡ አድዋ አንድነት የታየበት፣ የመለያየት ግንብ የፈረሰበት፣ ንጉሥ ከሠራዊቱ፣ ካህናት ከታቦቱ፣ ሳይለዩ በጋራ ለነጻነት የተሰለፉበት፣ የብርቱዎች ሰልፍ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የአድዋ ባለቤቶች ተገፍተዋል፤ ለፍላጎታቸው ባሪያ የሆኑ በተሸናፊው ጣሊያን ሐሳብ የተማረኩ፣ ኢትዮጵያዊ ሳሉ በግብራቸው ጣሊያናዊ የሆኑ አሸናፊዎቹን ሲሳደቡ የማይደነግጡ አንደበታቸው ያልተገራ፣ ውኃ የሌለባቸው ጉድጎዶች፣ ዝናብ አልባ ደመናዎች ዛሬ አገሩን ሞልተውታል፡፡
 
ታሪክ መሥራት አቀበት የሆነባቸው ታሪክንና ባለ ታሪኮችን የሚያዋርዱ፣ የድሉ  መሐንዲስ፣ የጦሩ ፊታውራሪዎችን የሚያናንቁ፣ ድንቁርናቸው በሱፍና በከራባት የተሸፈነ ብዙዎች ዛሬ የአድዋ ባለውለታዎችን ያራክሳሉ፤ ቤተ ክርስቲያንንም ከአድዋ ነጥለውና ውለታዋን አቃለው ይናገራሉ፡፡ አይችሉም እንጂ ክብሯን ለመዳፈር፤ ልዕልናዋን ለዋረድ ይመረምራሉ፤ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር እህል ላበደረ አፈር›› የሚሉት ብሂል ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፈጽሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከአድዋ ለመነጠል ጥረት ተደርጓል፡፡
 
በጥቅሉ አድዋን ያለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርበኞቿን አስተባብራ ባዕዳንን አሸንፋ ጠማማ ልጆቿን ማሸንፍ ተስኗታል፡፡ የሀገር አንድነትን የጠበቀች በአንድነት መቆም ርቋታል፡፡ ቁሳዊ ፍላጎቱን ያሸነፈ፣ ለእግሩ ጫማ ለሰውነቱ ሸማ የማይጨነቅ፣ ለሀገርና ለሃይማኖት ቅድሚያ የሚሰጥ ማኅበረሰብ የፈጠረች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የቁስ ፍላጎታቸው ጦር ሆኖ የሚወጋቸው አገልጋዮች ሞልተዋታል፡፡ ይህም ለታሪካዊ ጠላቶቿ በቀል በር የከፈተባት ትልቁ ክፈተት ነው፡፡
 
አድዋ አንድነት ነው፤ አድዋ እኩልነት ነው፤ አድዋ ነጻነት ነው፡፡ አድዋ የድሉ ባለቤቶችን መዘከር ነው፡፡ እነዚህን ዘንግቶ፣ የድሉ ፊታውራራዎችን በማንኳሰስ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሚና በመዘንጋት የሚከበር የአድዋ በዓል ትርጉም አልባና ታሪክን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡   

@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur