2022-08-29 22:16:00
ከተራራው ላይ
ክፍል አስር
(ፉአድ ሙና)
.
‹‹ከሰማይ በላይ ያለኸው ፣ ነፍሴን ለስቃይ ፈጥረኸው፣
ለአፍታ ሊያርፍ ቢደገፍ፣ ምነው ምርኩዙን ቀማኸው፣
በሱም ቀናህ?››
***
እራት ከተበላ በኋላ አብዱኬ ትንሽ ተጫውቶ ሄደ፡፡ ትንሿ ጎጇችን ውስጥ ሶስታችን ብቻ ቀረን፡፡ እማዬ ተኝታለች፡፡ ከኢንቱዬ ፊት ለፊት ተቀምጬ አይን አይኗን እያየሁ እስክትነግረኝ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ፊቷ ላይ መከፋት ይነበባል፡፡ መከፋቷን በውሸት ፈገግታ ልትሸፍነው እየሞከረች ‹‹ምንድነው የምትቁለጨለጨው?›› አለችኝ፡፡
አይኖቼን ፊቷ ላይ እንደተከልኩ ‹‹ንገሪኛ!›› አልኩ፡፡
እንባዋ አይኗን ሞልቶ ለመፍሰስ መታገል ጀመረ፡፡ ሳግ ባጠረው ድምፅ ‹‹እነግርሀለሁ ……›› አለች፡፡
ፍራሹ ላይ ከጎኗ ተቀምጬ አቀፍኳት፡፡ ማልቀስ ጀመረች፡፡ እያለቀሰች ‹‹ኢቦዬ አልቻልኩም …… ሁሉም ከቁጥጥሬ ውጪ ሆነ!›› አለችኝ፡፡ በእጄ ፀጉሯን እየዳበስኩ በዝምታ እስክትቀጥልልኝ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡
‹‹ኢቦዬ …… እጄ ላይ ምንም ገንዘብ የለም፡፡ ነገ እንኳን ለምሳ የምቋጥርልህ ነገር የለኝም! ከስራ ተባርሬያለሁ፡፡ በቻልኩት አቅም ለመሸፈን ሞክሬያለሁ፡፡ ግን አሁን ከአቅሜ በላይ ሆነ፡፡ አታፍርብኝም አይደል?››
ጭምቅ አድርጌ አቀፍኳት፡፡
‹‹ግን አይዞህ እሺ …… ብንራብም ይኼን ሳምንት ብቻ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ገንዘብ አገኛለሁ፡፡ እሺ?››
እንባዋን እየጠረገች ‹‹እሺ ኢቦዬ?›› አለች፡፡
ግንባሯን ሳምኳት፡፡
‹‹ኢንቱዬ …… እንደዚህ በግልፅ ስትነግሪኝ እኮ ላንቺም ለእኔም ይቀላል፡፡ አትጨነቂ …… ደግሞ ለዚህ ሳምንት መፍትሔ አናጣም!››
ተንሰቀሰቀች፡፡ አቅፌ ላረጋጋት ሞከርኩ፡፡
‹‹ኢንቱዬ …… እኔን እኮ ከረሀቡ በላይ የሚያመኝ አንቺ ከፍቶሽ ሳይ ነው፡፡ እኛ ለረሀብ አዲስ ነን እንዴ? ረሀቡንም መከራውንም መቋቋም የቻልኩት ግን አንቺን በማየት ነው፡፡ አንቺን ማየት …… ደስ ብሎሽ ማየት ከሁሉም በላይ ያጠነክረኛል፡፡ ኢንቱዬ በጣም እወድሻለሁ፡፡ በጣም! አትዘኚ! አብረን እናልፈዋን እሺ?!››
እንባዋን እየጠረገች ‹‹እሺ!›› አለች፡፡
‹‹ፈገግ በያ!››
‹‹እሺ›› ፈገግ ለማለት ሞከረች!
ጎኗን እየነካሁ ስኮረኩራት መሳቅ ጀመረች፡፡ መኝታችንን አነጣጠፍኩና ተቃቅፈን ተኛን፡፡
ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ በእኔና በኢንቱ መካከል ትራስ ገብቷል፡፡ ኢንቱ ተዘርራ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሰጥማለች፡፡ በመካከላችን ያለው ትራስ የእማዬ ፍራሽ ላይ የነበረ ነው፡፡ ግራ ግብት አለኝ፡፡ ማታ ተቃቅፈን እንደተኛን ትዝ ይለኛል፡፡ ተነስቼ ለትናንትና አቅጄው የነበረውን ለመጨረስ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ትንሽ ቆይታ ኢንቱዬ ነቃች፡፡ እየሳቀች መሀከላችን በነበረው ትራስ መታችኝ፡፡
ሳቋ እየተጋባብኝ ‹‹ይኼ ከየት መጥቶ ነው?›› አልኳት፡፡
‹‹ፍቅረኛ ምናምን ጀምረሀላ!?›› በአይኖቿ ልታወጣጣኝ ሞከረች፡፡ ሳቅኩኝ!
‹‹ተናገራ የምሬን እኮ ነው፡፡››
‹‹ኧረ ወፍ የለም!››
‹‹እሺ ትናንት የተመቸችህ…… የሳምካት ወይም ብስማት ምናምን ያልካት ሴት የለችም?››
‹‹ባይሆን የሚያምር ከንፈር አይቻለሁ፡፡ ግን ማንንም አልሳምኩም፡፡››
‹‹ወረኛ አሳሳምህማ ልምድ ያለው ሰው አሳሳም ነበር!››
‹‹የምን አሳሳም ነው?›› ግራ አጋባችኝ፡፡
‹‹ማታ በእንቅልፍ ልብህ ስትስመኝ ነበር …… ለዛ ነው ትራሱን መሀል ላይ ያደረግኩት!››
‹‹ማን እኔ? ምንሽን?››
‹‹ከንፈሬን ነዋ! የሆነ ሰዓት ስባንን አይንህን ዘግተህ ……›› ሳቀች፡፡
‹‹ቆይ እንዴት ይሆናል? ማለቴ እንዴት ከንፈርሽን አገኘሁት?››
‹‹ብዙም ሩቅ አልነበረም …… ፊት ለፊትህ ነበር እኮ!›› ሳቀች፡፡ ‹‹ደግሞ አቅፈኸኝ ስለነበር በደመ-ነብስም አይጠፋህም!››
አፈርኩ! እሷ ትስቃለች፡፡ በትራስ እየመታች ሙድ ትይዝብኛለች፡፡
‹‹ባይሆን እውነቱን ተናገር! ስመህ አታውቅም ማንንም?››
‹‹ኢንቱዬ …… ማንንም አልኩሽ እኮ! ማንንም!››
ተነስቼ መለባበስ ጀመርኩ፡፡ ከቻልኩ ስልኩን ዛሬ እንደምንም ለመሸጥ አስቤያለሁ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስዘገጃጅ አብዱኬ መጣ፡፡ እጁ ላይ ሁለት ፓስቲ ይዟል፡፡
እንደሌላው ጊዜ ምድጃው ላይ የተጣደ ነገር ሲያጣ ‹‹ሻይ የለም እንዴ?›› አለ፡፡
ኢንቱዬ ፈገግ ብላ እያየችው ‹‹ዛሬ ሻይ ፎርፈናል!›› አለች፡፡
‹‹አትነግሪኝም እንዴ!›› አኮረፈ!
‹‹በቃ እኛ ውጪ ‘ሚቀማመስ እንፈላልጋለን! ለእናንተ ስሪ!›› ከኪሱ ሀምሳ ብር አውጥቶ ሰጣት፡፡
‹‹ኧረ አብዱኬ ……›› ኢንቱዬ በሀፍረት አንገቷን ሰበረች፡፡
‹‹ምን ልትዪ ነው ደግሞ …… ወንድምሽ አይደለሁ እንዴ!?››
‹‹እሱማ ነህ …… አበዛሁት ብዬ እኮ ነው፡፡ አላህ ይስጥልኝ …… መቼስ ምን እልሀለሁ ……››
ፓስቲውን ከሰጣት በኋላ ተሰናብተናቸው ወጣን፡፡ መንገድ ላይ እየሄድን አብዱኬን ከሌላው ጊዜ በተለየ ተመለከትኩት፡፡ መልዓክ መልዓክ መሰለኝ፡፡
በስስት እየተመለከትኩት ‹‹አብዱኬ ……›› አልኩት፡፡
‹‹ኧ››
‹‹ታውቃለህ ትምህርት ቤት ስማር ሁሉም በጣም Smart እንደሆንኩ ይነግሩኛል፡፡ ለእኔ ግን በጣም smart ማን እንደሆነ ታውቃለህ?››
‹‹ማነው?››
‹‹አንተ ነህ!››
‹‹ምን ቀላቅለህ ቅመህ ነው?››
‹‹ቀልዴን አይደለም አብዱኬ! እኔን Smart የሚሉኝ በሚታወቅ ቀመር ሂሳብ፣ ፊዚክስ ወይም ደግሞ በሽምደዳም ቢሆን ሌሎቹን ትምህርቶች በደንብ መረዳትና መስራት ስለምችል ነው፡፡ ይኼ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ጥረት እንጂ ልዩ ጥበብ አይጠይቅም፡፡ ልዩ ጥበብ የሚጠይቀው ያልተፃፈን ነገር መረዳት ነው፡፡ የሰውን ልጅ መረዳት! የሰውን ጭንቀት ያለምንም ንግግር መረዳት! ከጭንቀቱ መፈወስ! ህይወትን መረዳት! ተቋቁሞ መኖር መቻል! ብዙ ሰው እኔን መሆን ይፈልጋል፤ እኔ ግን የምፈልገው አንተን መሆን ነው!››
‹‹የእኔን Smart ልንገርህ?››
‹‹ንገረኝ ……››
‹‹የእኔ Smart ኢንቲሳር ናት፡፡ ለራስ ሳይጨነቁ ለሌላ ሰው የመኖር ምሳሌዬ ናት፡፡ ድሮ ስራ ስጀምር ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ አላውቅም ነበር፡፡ ሁሉንም ያስተማረችኝ እሷ ናት፡፡ የከፋኝ ቀን የምሄደው ወደሷ ነው፡፡ ከባድ የመሰለኝን አቅልላ ታሳየኛለች፡፡ ያጣሁ ጊዜ ያላትን በአቅሚቲ ታካፍለኛለች፡፡ አንዳንዴ ምናለ ከእሷ ጋር ከአንድ መሀፀን በወጣን …… የስጋም እህቴ በሆነች ብዬ እመኛለሁ፡፡ ኢቦዬ እህትህ በጣም በጣም ልዩ ሰው ናት!››
‹‹እሷስ ልክ ነህ ልዩ ናት!››
ባጃጅ ተራ ደርሰን አንድ ሻይ ቤት ገባንና ፓስቲ በሻይ በላን፡፡ አለምባንክ ደርሰን ከአብዱኬ ጋር ልንለያይ ስንል እጄን ይዞ ‹‹ይኸውልሽ ኢቦ …… ችግር ሁሌም ያጋጥመናል፡፡ ግን ደግሞ ያልፋል፡፡ ገባሻ! ዛሬ ቢቸግረን ነገ እናገኛለን፡፡ አትጨነቅ!›› አለኝ፡፡ አሁን አሁን አብዱኬን በአንድ አመት እንደምበልጠው መርሳት ጀምሬያለሁ፡፡ ታላቅ ወንድሜ …… ታላቅ ወንድሜ ይመስለኛል፡፡
ከአብዱኬ ጋር ተለያይተን ወደ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ቀኑን ሙሉ በቻልኩት መጠን ስልኩን ለመሸጥ ለብዙ ተማሪዎች ሳሳይ ዋልኩ፡፡ በርካሽ ስምንት ሺህ ድረስ ልሸጥላቸው ብዙዎችን አጠያየቅኩ፡፡ የሚደፍር አልተገኘም፡፡ ባዶ እጄን ወደ ቤት መግባት ቀፈፈኝ፡፡ ማህሌትን ላስቸግራት አሰብኩና ወደ ማታ ደወልኩላት፡፡ ስልኳ ዝግ ነበር፡፡ ማታ ቤተል ቤተ-መፅሀፍት ከአቤላ ጋር ተቀምጬ አብዱኬ ስለዘገየብኝ ለመደወል ሞከርኩ፡፡ ስልኬ ካርድ አልነበረውም፡፡ በአቤላ ስልክ ደወልን፡፡ ስልኩ ዝግ ነው፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ትንሽ ጠብቄው ሲቆይ ወደ ቤት ሄድኩ፡፡ ለብቻዬ ስለሆንኩ ነው መሰል መንገዱ በጣም ረዥም
301 views19:16