2023-02-16 11:25:23
ላለፉት ሦስት ሳምንታት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታሪክዋ አይታው የማታውቀው ሐዋርያዊ ሰንሰለትዋን የሚበጥስ አንዳች ዱብ ዕዳ ገጥሞአት በብዙ ጭንቀትና መከራ ውስጥ አሳልፋለች፡፡ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ በጉዳዩ ተደናግጦ ለእናት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት የሚችለውን ሁሉ ለመክፈል ታይቶ በማይታወቅ አንድነት ተረባርቦአል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እስካይ ድረስ ለዓይኖቼ ዕረፍትን ለሽፋሽፍቶቼ እንቅልፍን አልሠጥም ብላችሁ ስለ ቅድስት ቤተ ክርቲያን በምትችሉት ቆማችኋል ፣ ብርድ ላይ አድራችኋል ፣ ለመሞትም ቆርጣችኋል፡፡ አሁን በሰማያዊትዋ የድል ነሺዎች ቤተ ክርስቲያን ሆናችሁ የምታዩን ፣ ዓይናችን እያየ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አትደፈርም ብላችሁ ሰማዕታት የሆናችሁት ልጆችዋም በረከታችሁ ይድረሰን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከብባችሁ አካላችሁ የጎደለ ፣ አሁንም ድረስ በአልጋ ላይ ያላችሁ ፣ ቤተሰቦቻችሁን ያጣችሁ ፣ ከቀዬያችሁ የተፈናቀላችሁ እስከ አሁንዋ ሰዓት ድረስ በወኅኒ ቤት ሆናችሁ ከእናንተ መፈታት ይልቅ የችግሩ መፈታት ያስጨነቃችሁ ወንድምና እኅቶቻችን ሥራችሁ በልበ ሥላሴ የተጻፈ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስለተገደሉ ልጆችዋ ስታለቅስና ማቅ ስትለብስም ከዳር ዳር ጥሪዋን ተቀብላችሁ ማቅ የለበሳችሁ ‘ቤተ ክርስቲያን ሆይ ማቅ ልልበስልሽ’ ያላችሁትን በአደባባይ በጥፊ የተመታላት የቤተ ክርስቲያን ራስዋ ክርስቶስ አይቶታል፡፡
ግራ ቀኝ የሚናፈስ ወሬ ነገሩን ሊያደፈርሰው ሲሞክርም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምእመናን ‘ከሲኖዶስ ሌላ ማንንም አንሰማም’ ብላችሁ ታዝዛችኋል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተ ክርስቲያን ክብርና የቅዱስ ሲኖዶስ ምንነት ሰምተው የማያውቁ ሰዎች ሳይቀር በዚህ የተነሣ የጉዳዩ መሠረታዊነት ግልፅ ሆኖላቸው ፣ ግድ የማይሰጣቸውና ሲኖዶስን ሲሳደቡ የነበሩ እንኳን ‘እኔ ነኝ ያስደፈርኩሽ ቤተ ክርስቲያኔ ይቅር በይኝ’ ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኔን ነገር አደራ ብሎ ያነባው ፣ ንስሓ የገባው ሕዝበ ክርስቲያን እልፍ አእላፍ ነበረ፡፡ መተዳደሪያ ሥራቸውን ፣ ዝናቸውን ፣ ሙያቸውን አደጋ ላይ ጥለው ብዙዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው ጮኸዋል፡፡ እምነታቸው ሌላ ሆኖ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን የቆሙ ባለውለታዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ምንም ዓይነት ማስፈራሪያና ጫና ያልበገራቸው ብፁዓን አበው ታሪክ በማይረሳው መንፈሳዊ ጥብዓትና ጽናት በአንድ ልብ ሆነው በመናገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠበቆች ሆነዋል፡፡ ሁላችሁም ‘ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ እግዚአብሔር አመጸኛ አይደለም’ ዕብ. 6፡10
‘ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?’ አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሚል መርሕ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ለማስከበርና የቅዱስ ፓትርያርኩን አባትነት ለማጽናት ፣ በዚህም በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት የተሻገረችውን ቤተ ክርስቲያን ሳትፈርስ እንድትቀጥል ለማድረግ ነው፡፡ ያ ሁሉ ዕንባና ልቅሶ ፣ ያ ሁሉ ሰማዕትነት አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቀኖናዊ ዶግማ (Canonical Doctrine) ለማስከበር ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት ከቅዱስ ሲኖዶስ እንደሰማነው በእግዚአብሔር ቸርነት ለሳምንታት ቤተ ክርስቲያንን እስከ ሰማዕትነት ድረስ ብዙ ዋጋ ያስከፈለው ችግር ተፈትቶ ‘አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መርሕ ተከብሮአል፡፡ ፓትርያርካችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ ሲኖዶሳችን አንድ ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም አንዲት ናት የሚለው ጸንቶአል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ስለ ክብሩ መደፈር ተቆርቁረን ብዙ የጮኽንለት ቅዱስ ሲኖዶስን የእውነት ማክበራችንና መውደዳችን በተግባር የሚፈተነው አሁን ነው፡፡ ከአባቶቻችን ጎን እንደነበርን ከዚህ በኋላ በሚመጣው ነገር ሁሉም አብረናቸው እንሆን ይሆን? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ በሰማናቸው መግለጫዎች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተከብሯል ፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የነበረው ሹመትም መሻሩን ሿሚዎቹ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን የመመለስ ጥሪ ተቀብለው ይቅርታ ጠይቀውም የተወገዙት ሊቃነ ጳጳሳት ተመልሰዋል፡፡ ልባችንን ያደማው የቤተ ክርስቲያን መከፈል ጉዳይ ባልተጠበቀ ፍጥነት ተፈትቶ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሰማ አይተናል፡፡
በሒደቱ ላይ ነገሮች በጣም በፍጥነት ከመለዋወጣቸው የተነሣ ብዙ ጥያቄ የሚፈጥሩ ዝርዝሮችና ከልባችን ገና ያልወጡ ሥጋቶች መኖራቸው ግን የማይካድ ነው፡፡ ክስተቱ ተመለሱ የተባሉ ሰዎች ሲወላወሉ ባየንበት ማግሥት የሆነ ነገር እንደመሆኑም ለማመን የቸገረንና በሙሉ ልብ ለመደሰት የፈራን ብዙዎች ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውግዘት የለየቻቸውን አበው መልሳ የምትቀበልበት አካሔድ እንዴት ነው? ፣ ከዚህ በኋላስ ምን ይፈጠር ይሆን? ፣ ወደነበርንበት ለመመለስ የከረምንበት ሁኔታ ይፈቅድልን ይሆን? መንግሥት በቃሉ ባይገኝስ? በፍርድ ቤት የታዩ ጉዳዮችስ? ይቅርታ የሚጠይቁ ሰዎች እያታለሉን ቢሆንስ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች የቤተ ክርስቲያኑ ነገር እንደ እግር እሳት ሲያንገበግበው ከሰነበተ ምእመን የሚጠበቅ ውስጣዊ ጥያቄ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ተግባራዊ ምላሽ እንደሚሠጥበት እንጠብቃለን::
መንግሥትን እንዴት ማመን እንችላለን? ለሚለው እኛ ሁልጊዜም የምናምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ አምነነው አሳፍሮን አያውቅም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ስለ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: በእግዚአብሔር መንፈስ ይመራሉ ብለን የምናምንባቸው አባቶቻችንንም እስከ አሁን ያዘዙንን ስናደርግ ሰንብተን ከዚህ በኋላ አባትነታቸውን ብንጠራጠርና በስሜታዊነት ብንሳደብ ‘ለሦስት ሳምንታት ቅዱስ ሲኖዶስ ክብርና ልዕልና ተነካ ብለን የጮኽነው ለምን ነበረ? ያስብላል፡፡
በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ከመንግሥት ጋር በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆነው ‘ቤተ ክህነቱ ሊወረር ነው ፣ አባቶች ሊታፈኑ ነው’ የሚል የሚያሸብር ዜና እየሰሙ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሰነበቱ አባቶች ፣ ጠባቂዎች ቢነሡባቸው እግዚአብሔርን ጠባቂያችን ብለው ስለ ሕገ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ በድፍረት የቆሙ ሊቃነ ጳጳሳት ዋናው ችግር ከተፈታ በኋላ በሚኖረው ሒደት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው ይሠጣሉ ብሎ መደምደም የሚያሳዝን ነው፡፡
አባቶችን ላታልላቸው ብሎ እንደ ሀናና ሰጲራ መንፈስ ቅዱስን ሊያታልል የሚሞክር ሰው የሚያታልለው ራሱን ነውና ይቀሰፋል፡፡ አርዮስ አባቶችን አታለልኩ ብሎ ሳያምን አምኛለሁ ብሎ የደረሰበትን ስንማር ኖረናልና ቤተ ክርስቲያንን ሊያታልል የሚሞክር ሁሉ በእርሱ እንደሚብስበት እናምናለን፡፡ ስለዚህ ተመለሱ በሚል ዜና እንደጠፋው ልጅ ወንድም አኩራፊ ፣ እንደ ሀናንያ ተጸያፊ ሳንሆን የእውነት ያድርገው ብለን በመጸለይ እንበርታ:: የነነዌ ለቅሶ መልስ ሲያገኝ ካኮረፍን ኩርፊያችን የዮናስ ኩርፊያ ይሆንብንና ትርፉ ቅላችንን ማድረቅና በፀሐይ መለብለብ ይሆናል:: (ዮና. 4:1-11) ልጅ ጠፍቶ ሲገኝ ደስ የሚል ከሆነ አባት ጠፍቶ ሲገኝ እንዴት ደስ አይልም? እንደ ልጅነታችን ዳግም አባት አልባ እንዳንሆን መለመን ነው እንጂ::
430 views08:25