2022-08-28 21:51:08
እንዲህ ብናደርግስ ወገኖች!
1) ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ምሽግ በማድረግ ነው የኖረው። እኛ የትግራይን ሕዝብ ብንፈርጅለት ደስታው ነው። ይቀሰቅስበታል። ስለሆነም ለትህነግ ላለማገዝ ትኩረታችንን ቡድኑ ላይ እናድርግ። በደስታም ሆነ ተናድደን የምንፅፈውን ትህነግ በሀሰት ለመቀስቀሻነት እንዳይጠቀምበት፣ ጠምዝዞ ሕዝብን እንዳያሳስትበት መጠንቀቅ ብንችል መልካም ነው። የትግራይ ሕዝብ በትህነግ አፈና ውስጥ ነውና ነፃ እንዲወጣ እየሰራ ያለውን የወገን ጦር በቀናነት ብናግዝ ለሁላችንም ይጠቅማል።
2) አሁን ያለንበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ነው። የወገን ጦር ሲያሸንፍ ያን ክፉ ቡድን ጥፋቱ ይቀንሳል። ትህነግ ባይሸነፍ ህልውናችን አደጋ ውስጥ ይገባል። ስለሆነም የያዝነው የህልውና ጉዳይ መሆኑን አውቀን ያደሩ ልዩነቶቻችን ብንችል ማስታረቅ፣ ካልሆነ በይደር መተው ብንችል አሸናፊዎች እንሆናለን።
3) የወገን ጦር ጫካና ተራራ፣ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁበት ነው ለእኛው የቆመው። እኛ ፌስቡክ ላይ በሚፃፍብን ጉንተላ ወዘተ ስንጣላ፣ የወገን ጦር በምሽጉ አናት መድፍ እየጮኸበት፣ የሞርታር ጋጋታን እየጣሰ ነው ለእኛ የቆመው። ስለሆነም የወገን ጦር ለእኛ ሲል እየከፈለው ያለው ጋር አነፃፅረን እኛ ያለንበትን አለመግባባት ወዘተ ቀለል ብናደርገው መልካም ነው። በኮሜንት መተጋተግን እንደ ትልቅ ጦርነትና ፍልሚያ ከማየታችን በፊት እጅና እግሩ ቆስሎ እየተዋጋልን ያለውንም ብናስታውስ ጥሩ ይሆናል።
4) የወገን ጦር ሲያሸንፍ የምንደሰተውን ያህል ሳይቀናውም መታገስ አለብን። ብዙ ፈተናዎች አሉበት። ተከብቦ ለቀናት ውሃና ምግብ ሊያጣ ይችላል። ከራሱ ወገን ጋር ተመሳስሎ የሚመጣበት ትህነግን ማሰብ አለብን። እኛ በፕራንክ ስንደነግጥ እየዋል፣ የወገን ጦር የጥይት አረር ሰውነቱን ሲገርፈው እንደሚውልም ማስታወስ ይገባናል። እኛ የፌስቡክ ጩኸት አልችል ብለን የወገን ጦር ጆሮ የሚቀደውን የከባድ መሳርያ ድምፅ ብቻ ሳይሆን ጥይቱም በየአቅጣጫው እየመጣበት ችሎ እንደሚታገል ማስታወስ አለብን። ስለሆነም በብቃቱ ሲያሸንፍ የእኛ ድል እንደምናደርገው፣ በተለያየ ምክንያት ባይቀናው መረጃዎች ሳይኖሩን ዘልለን ተጠያቂ ከማድረግ ብንቆጠብ። ድክመቱንም የጋራ ማድረግ ብንለምድ መፍትሔ ለማምጣት ይቀልለናል።
5) የገጠመን ኃይል አወናባጅ ነው። መረጃን እንደዋነኛ ጦርነት ስልት ይጠቀምበታል። ሰርጎ ገብነትን ትልቅ ስልት አድርጎ ይጠቀምበታል። የእኛን መወዛገብ ይጠቀምበታል። ተደስተንም ሆነ ተናድደን የምናሰራጨውን እንደ መረጃ ይጠቀምበታል። ስለሆነም የገጠመንን ኃይል በሚገባ ተገንዝበን የምናሰራጨውን መረጃ ጉዳትና ጥቅም መዝነን መሆን ይኖርበታል። ሲቀናው ብቻ ሳይሆን ድክመቶች ሲኖሩም ለመታገስ፣ ተጋግዞ ችግሮቹን ለመቅረፍ ለራሳችን ቃል መግባት አለብን።
6) የወገን ጦር አባል ከመዋጋት ይልቅ ሰርቶ መብላትም የሚችልበት አቅም አለው። ባለሙያ፣ ባለሀብት ሆኖ ለእኛ ሕልውና የቆመ አለ። በዝናብና በፀሐይ የቡድን መሳርያ የሚሸከመው ከፍ ያለ አላማ ይዞ እንጅ ይህ አላማ ባይኖረው የቀን ስራ ሰርቶ፣ ሰራዊቱ ከሚያድርበት አውላላ ሜዳ አንፃር የሞቀ ከሚባል ቤት ማደር ይችል ነበር። ይህ ባይሆን እንኳን እንደ ክፉ ወጣት ዘርፎም መኖር ይችላል። በአንፃሩ ግን አሁን የግሉን ምቾት ህይወት አስይዞ ዋጋ እየከፈለ ነው። ለዚህ ዋጋ እኛም የበኩላችን ማውጣት አለብን። ማገዝ አለብን። ስንቅ፣ ልብስ፣ ደጀንነት ያስፈልጋል። እንደዚህ አግዘን፣ በቅርብ አይተነው፣ መረጃ ይዘን ሲያጠፋ፣ ሳይሳካለት ሲቀር ብንተቸው የተገባ ነው። ምንም አይነት ድጋፍ ሳናደርግለት፣ ሲያሸንፍ እየተደሰትን፣ ሳይቀናው ልንጮህበት ሞራል የለንም! ስለሆነም ከወገን ጦር የበኩላችን ማድረግ ይጠበቅብናል።
7) የወገን ጦር ወደ ትግራይ ከገባ ትልቁ ፈተና የሚሆነው ታፍኖ የከረመውን ሕዝብ ጉዳይ ማስተካከል ነው። ትህነግ የእርዳታ እህሉን ሲዘርፈው የከረመው የትግራይ ሕዝብ እርዳታ ይፈልጋል። ትህነግ አጥሮት የከረመው ድንበር ሲከፈትም በርካታ ስደተኛ ይኖራል። ስለሆነም ስለ ሰብአዊነት ያገናኛል የሚል ሁሉ የትግራይ ሕዝብን ለማገዝ ከአሁኑ ማሰብ፣ መዘጋጀት ይኖርበታል። ከአሁኑ ከታሰበበት የትግራይ ሕዝብን ማገዝ ቀላል ይሆናል።
8/ ይህ ጦርነት ብዙ ጉድ አሳይቶናል። ሞት ረክሶ ከርሟል። የምናውቀውንም የማናውቀውንም ወገናችን አጥተናል። ውድመቱና የተፈፀመው ሁሉ ስሜታዊ ያደርጋል። ቦታ ተያዘ ተለቀቀ እየተባለ ጭንቅ ከርሟል። ይህ ሁሉ ባሕሪያችንን ሊቀይር፣ ስሜታዊ ሊያደርገን ይችላል። በዚህ ምክንያት ብንሳሳት፣ ለወገን ጦር የማይጠቅም ነገር ብናጋራ መተራረምን መልመድ ይኖርብናል። ያልተጣራ መረጃን ወዳጅ ጠይቀን አረጋግጠን ማጋራት ብንችል።
24.0K viewsedited 18:51