2022-08-30 18:05:48
ሕዝብን ማሸበር እውነተኛ አያስብልም!
ጉዳዪ የጦርነት ነው። አውዳሚ ነው። ወገናችን የተሰቃየበት ነው። ሴቶች የተደፈሩበት ነው። ሕዝብ ይህ አደጋ መልሶ መጣ ሲባል ቢፈናቀል አይገርምም። ስራ ያልሰራነው እኛው ነው። አሸባሪው ከተፈናቃይ ጣቢያ አምጥቶ ሲወርረን እኛ የሞቀ ቤቱ ያለውን ሕዝብ እንዲሳደድ እያደረግን ነው። ከባለፈው ጦርነት በኋላ ብዙ ስራ አልተሰራም። ያ አልበቃ ብሎ ግን ሕዝብን በሆነው ባልሆነው ማሸበር ከጠ*ላ*ት የማይለት ተግባር ነው። ጠ*ላ*ት በሰርጎ ገብ በኩል ውጡ መከላከያ ሸሽቷል እያለ ሲያሸብር እናውቀዋለን። የሰራዊት ልብስ ለብሶ ጭምር ብዙ ድራማ ሰርቷል። ፌስቡክ ላይም ይህን ሽብር እየፃፉ ያሉ ሰዎች እንደ እውነተኛ እየተቆጠሩ የጀግንነት ስራ አድርገው ቀጥለውበታል። ሕዝብ ሰግቶ በሸሸበት ለሰራዊቱ ደጀን የሚሆን አይገኝም። ሕዝብን ከቀየው እንዲሸሽ እያደረግን ከሌላው የኢትዮጵያ ጫፍ የመጡ ወንድሞቻችን ሕዝብ ነቅሎ ከወጣ ለምን እዋጋለሁ ብለው ቢሸሹ ችግሩ የእነሱ ብቻ አይሆንም። ችግሩ በሕዝብ ላይ ሽብር የሚፈጥረው አካል ነው።
ትህነግ ሰሞኑን በገባባቸው አካባቢዎች ከየትኛውም በላይ ተዘግተው የተገኙ ቤቶች ምንም ሳይተርፋቸው ተዘርፈዋል። ያልሸሹት ቢያንስ የተወሰነ ነገር ተርፎላቸዋል። ሕዝብ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚፅፈውን አመዛዛኝና አሳቢ አድርጎ ያስባል። ያምናል። እውነትም ሆነ ሀሰት እንዲሳደድ የሚያደርገው መረጃ ሲለጠፍም ከእነዚህ አረመኔዎች ለማምለጥ ቢሞክር በእሱ አይፈረድም። የመጀመርያው ችግር ሳያውቀው ህወሃት ለሰርጎ ገብ የሰጠውን ሚና የሚወጣው አካል ነው።
የሚገርመው ደግሞ የሽብር ወሬ ሲነዙ ከቆዩ በኋላ ሕዝብ አካባቢውን ለቅቆ ሄደ ብለው የሚወቅሱ፣ ፎቶውን እየለጠፉ ሁለተኛ ሲዘልፉት የሚውሉ ለህዝብ ያገባናል የሚሉ ሰዎችም አሉ። ሕዝባችን ከጥይት በላይ የማሕበራዊ ሚዲያ ዜና እንዲያሸብረው ብዙ ተሰርቶበታል።
አንዳንዶቹ ደግሞ እውነቱ ካልተዘገበ ወዘተ ይላሉ። እውነት ምንድን ነው? ከተማ ተያዘ ብሎ መፃፍ የሀቀኝነት መለኪያ የሆነበት ምክንያት በራሱ ግራ የሚያጋባ ነው። አሁን አሁንማ የእኛው ፌስቡከኛ ቀድሞ ስለሚያስጮኸው የትህነግ ፌስቡከኞች ሰበር ዜና ብለው መስራቱን ትተውታልኮ። ጥቅሙ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ የሚለጠፈው ነገር በዝቷል። ሕዝብን የሚያስጨንቅ ነገር በደፈናው ይፃፋል። ማስፈራሪያ ይፃፋል። በጦርነቱ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ሳይሆን ራቅ ካለ ቦታ የሚኖረው ዘመድ አዝማድ፣ ወገን እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። ይህ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆን መልካም ነበር። ያለንን መረጃ ለሕዝብ በሚጠቅምና፣ ጠላት በማይጠቀምበት መንገድ ብንገልፅ ጥሩ ነው።
ፌስቡከኛው እንደዚህ አያያዙኮ እውነት ሁሉ መፃፍ አለበት ብሎ በጀግንነት የተሰዋን ሰው ሁሉ በፌስቡክ ሊያረዳ ይችላል። በተለመደው መንገድ እንኳን ሰው ሲረዳ ጊዜና ቦታ ተጠብቆ ነው። ገበያ ላይ እያለ አይነገርም፣ ሰርግ ላይ ሆኖ አይነገርም፣ መንገድ ላይ ሆኖ አይነገረውም። ግዴታ ካልሆነ ምሽት ላይ አይነገረውም። ብዙውን ጊዜ ቤቱ ከገባ በኋላ በጠዋት ይነገረዋል። ያውም መቸ ይነገረው፣ ማን ይንገረው፣ እንዴት ይነገረው ተብሎ ነው። ራቅ ያለ አካባቢ ከሆነ ደግሞ የሞተ ዘመዱ እንደታመመፐተደርጎ ነው ድረስ ተብሎ ነው የሚላክበት፣ አሊያም ሰበብ ተፈልጎ እንዲሄድ ይደረጋል። ይህን ያደረገው ውሸታም አይባልም። ይህ ሁሉ ሰውን ላለመጉዳት ሕዝባችን የሚያደርገው ነው። አይደለም የጦርነትን ያህል የግለሰብ ጉዳይ እንኳን በሕዝባችን ዘንድ የሚነገርበት ወግ አለው። ህፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አዛውንቶች እንዳይሰሙ ተብሎ የሚደበቃቸው እውነት አለ። ይሸበራሉ፣ ይጨነቃሉ፣ ይታመማሉ ተብሎ ነው። የሕዝባችን ወግ ይሄ ነው። እውነት የተባለው ሁሉ ሲዘረገፍ አይውልም። እያንዳንዱ ፌስቡክ ላይ ሲሆን የሕዝብን ጉዳይ "እውነት ስለሆነ ይፃፍ" የሚለው ለቅርብ ቤተሰቡ ይጨነቃል ብሎ የማይነግረው እውነት አለው። ለራሱም ደግሞ ደጋግሞ የማይነግረው ማስረሻ የሚፈልግለት አስጨናቂ እውነት አለ። የአሁኑ ፌስቡከኛ ግን እንዲሁ ያገኘውን ሳያጣራም ጭምር ይለጥፋል። እውነቱ ይውጣ ወዘተ ይባላል። ሕዝብ የሚያሸብር እውነት ምኑን ይጠቅማል? ሕዝባችን ስለተሳደደ ምን ጠቀምነው?
የሕዝብን ስነ ልቦና መጠበቅ አንደኛው የትግሉ አካል ነው። ስነ ልቦናው የተጎዳ ሕዝብ ሁሉ ተጠቂና ተሳዳጅ እንደሆነ ነው። ሕዝባችን እረፍት የሚነሱ ነገሮችን ጥሬ እውነት ናቸው ብለን አደባባይ ላይ ስንደፋ መዋል የለብንም። ሕዝባችን ያጠቁት አካላት በርካታ ሰው ሞቶባቸዋል። ነገር ግን በአደባባይ ሲያለቅሱ አናያቸውም። ሟቾቹን ስለማይወዷቸው አይደለም። ከስነ ልቦና አንፃር ስለሚያዩት ነው።
እውነት የሚገለፅበት አግባብ፣ ቦታና ሁኔታ አለው። ዝም ብሎ የትም አይጣልም። ፌስቡክ የሚጠቅምም የማይጠቅምም እውነት የሚጣልበት ሜዳ ሆኗል። በዚህ ጦርነት ወቅት ከዚህ መለየት ይኖርብናል። ለሕዝብ የሚጠቅመው እውነት ብቻ ነው መነገር ያለበት። ሰበር ዜናውም የህዝባችን ስነ ልቦና የሚሰብር ዜናም እውነት እየተባለ ባይለጠፍ ጥሩ ነው።
ይህ የፖለቲካ መድረክ ነው። የጦርነት ወቅት ነው። ሌሎች በሴራ፣ እውነታን ከእነሱ አንፃር በመመንዘርና በመጠምዘዝ ፕርፖጋንዳ በሚያበዙበት ወቅት እውነት ነው እየተባለ የሆነ ያልሆነው አይለፈፍም። እውነተኛም አያስብልም።
23.2K viewsedited 15:05