2021-11-19 18:22:55
ከወረቀት ያልተዋደደ ብዕር ምን ምስጢር ያወራል?
ብቻውን የቆመ ግድግዳ ለማን ከለላ ይሰራል?
ተከታይ የሌለው ነብይ ምን እውነት ይናገራል?
ከሰው ያልተዋሃደ ሰው መች ከልቡ ይኖራል?
ይህ አለም ጥምረት ነው አንዱን ካንዱ ያዋቀረ
በተፈጥሮ ጉጉን ጎንጉኖ ሁሉን ያስተሳሰረ
ከዚህ የህይወት ጉንጉን እራሱን ሊያወጣ የሞከረ
የዳር ተመልካች ሆነ እንጂ መች ከልቡስ ኖረ?
ከአበባው መሃል ቆሜ ይህን እያሰብኩኝ
አንዲት ቢራቢሮ ......አበባውን ስትስም ታዘብኩኝ
ስማ......ስትቀስም
ለመላምቴ ማስረጃ ፈጣሪ እጁን ሲሰጠኝ
ከአበባው ቀና አድርጎ ከቢራቢሮ አፋጠጠኝ
እዛው እንደቆምኩኝ.....
ይህ የትስስር ኑሮ ጠልቆ ይገባኝ ጀመረ
ሰው የራበው ልቤም ፍለጋውን አመረረ!!!
ሰው ያለሰው ፤ ሰው ያለዙሪያው ህይወትን ሙሉ በሙሉ ሊኖራት አይችልም። ሰው ስንል ግዴታ በአንድ ጣሪያ ስር የሚኖርን ወዳጅ አይደለም፤ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ እንጂ። እኛ ከአለም ውጪ አለም ከእኛ ውጪ አንደኛችም መኖራችን አይረጋገጥም ። የሰው ዘር ከእኛ ህይወት ውስጥ ፤ እኛም ከሰው ዘር ውስጥ መውጣት አንችልም። ልክ ገጣሚው እንደሚለው “አንተ የውቂያኖሱ ጠብታ ሳትሆን ውቂያኖሱ ያንተ ጠብታ ነው” እንዳለው መሆኑ ነው።
ብዙ የከበዱን ነገሮች ሊቀሉን የሚችሉት፤ እራሳችንን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት ማቅረብ ስንችል ነው። አሁን ከፊት ለፊቴ የተቀመጠችው ወጣት፤ እራቅ ብለው የቆሙት አዛውንት፤ ከአስፓልቱ ባሻገር የሚለምነው ለማኝ፤ ከለማኙ ጀርባ ባለው ፎቅ ውስጥ የተቀመጠው ባለሃብት፤ ሁላችንም የተሳሰርን ነን። እንዴት? እሱ በማስረዳት የሚመለስ አይመስለኝም፤ በመኖር ውስጥ ብቻ ሊገባን የሚችል ግላዊ እውነት እንጂ። ለብቻ የተሰራ አንድም ታሪክ የለም፤ ሁሉም የጥምረት ውጤት ነው።
የሰውን ከዙሪያው ጋር መዋሃድ አስፈላጊነቱን ስናወራ፤ በጥገኝነት መልኩ ብቻ አይደለም። ሁላችንም በራሳችን ምሉዕ ነን ብለን ልናስብ እንችላለን፤ በእርግጥም ምልዑ እንሆን ይሆናል። አንዳንድች ከሌላችን ጋር የተሳሰርንበትን ክር መበጠስ ስንሞክር ነው ችግሩ የሚፈጠረው።
በዚህ አለም ውስጥ የገለልተኝነት ስሜት ሊሰማን አይገባም፤ በቅርብ የምናወራው ሰው ባይኖረን፤ አብሮን ሌሊቱን የሚያሳልፍ ወዳጅ ባያድለን፤ ለቡናና ለሻይ የሚሆን ጓድ ቢጠርብን እንኳን፤ ከዚህ የህይወት ትስስር ውስጥ ክራችን እንደተቆረጠ ሊሰማን ፈጽሞ አይገባም። ለብቻ መሆን አይደለም የብቸኝነት መንስዔው፤ የብቸኝነት መንስዔው መንፈሳችንን ከዙሪያችን መነጠል ነው። ሁሉም ነገር የእኛ አካል ነው፤ እኛም የሁሉም ነገር አካል ነን፤ ይህ ተፈጥሮ የቆጣጠረው በእኛ ሃይል የማይፈታ ቋጠሮ ነው። ዙሪያችንን ወደእኛ በማቅረብ እኛም ወደዙሪያችን በመቅረብ ይህችንን ህይወት ትንሽ ትርጉም እንስጣት።
A wall standing alone is useless
But put three or four walls together And they will support a roof and keep The grain dry and safe.”
ሚስጥረ አደራው
ውብ አሁን
@EthioHumanity
@EthioHumanity
8.2K views15:22