2022-01-01 19:16:36
ዓይንህን አንሳ!
ዓይንህን ከሰው ላይ አንሳ።
ዓይንህን ከሰው ስኬት፣ ከሰው ንብረት፣ ከሰው ሀብት ላይ አንሳ። የሌላን ሰው ወዳጁን፣ ንብረቱን ይቅርና ሠራተኛውንም አትመኝ። ትኩረትህን ከሰው ላይ ንቀል።
የሰውን ነገር መመኘት ኃጢዓት መሆኑ በመጽሓፍ ላይ ተነግሯል። የሰውን ንብረት አትመኝ። የሰውን ንብረት አትመልከት። የሰውን ወዳጅ፣ ጓደኛውን፣ አጋሩን ለራሱ ተውለት።
የሰው ስህተትና ጉድለት ላይም ብዙ አታተኩር። ዓይንህን ከሰው ድክመት ላይ አንሳ። ዓይንህ ውስጥ ያለው ግንድ ከሌላው ሰው ጉድፍ ይበልጣልና አንተ ማነህ የሰውን ጉድፍ የምታጠራ?
ብትችልስ ራስህን አጥራ። የራስህ አመለካከት ሲጠራ ደስታህና መልክህ እንደፀሓይ ያበራል።
ያንተ ማለት በእጅህ ያለው ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ያንተ ማለት የበላኸውና የለበስከው እንጂ በኪስህ ያለው እንኳ ሌላ ሰው ሊወስደው ይችላል ይላሉ።
የሰው ድካም ይገርማል። በአፉ ያለውን ሳያጣጥም ሌላ ለመቁረስ ይጣደፋል። እንዲሁ በእጁ ላልገባው እንደተንገበገበ ዘመኑ አንድ ቀን ያልቃል።
አንተ ግን በእጅህ ባለው መደሰትን እወቅበት።
ባለህ ማመስገን ስትችል ሌላው ወዳንተ እየተሳበ ይመጣል። በአቶዝ የሚያመሰግን ኢላንትራ ብሎም RAV4 ይጠራል። በኮሮላ የሚያመሰግን ውሎ አድሮ ሬንጅሮቨር ከዚያ አልፎም ሮልስ ሮይስ ይስባል። የሚያማርር ግን ያለውንም ያጣል።
ምስጋና/Gratitude ትልቅ ስጦታ ነው። ማመስገን መቻል ትልቅ ችሎታ ነው። አመስግን።
ጀሊሉ ከላይ በለቀቀልህ በረከት ለሌሎች በማካፈል አመስግን። አካፍሉኝ አትበል፣ ሲሰጡህ ግን ማመስገንን እወቅበት። ፈጣሪ የሚያስፈልግህን በትክክለኛ ጊዜው እንደሚሰጥህ እመን።
ፈጣሪህን አመስግን፣ ወላጆችህን አመስግን፣ ቤተሰብህን ባለቤትህን ልጆችህን አመስግን፣ እህቶችና ወንድሞችህን አመስግን፣ ጓደኞችህን፣ ጎረቤቶችህን፣ አለቆችህን፣ መሪዎችህን... አመስግን። ሁሉንም ምንም ባይሰጡህ አብረውህ እንዲሆኑ ስለተሰጠህ እድል አመስግን።
ማመስገን የማይችል ግን እንዴት ተበድሏል?
ጉድፍህንና ነቀፋህን ለሚከታተሉ ብዙ ቦታ አትስጥ። ለእነርሱ አንተ በውሃ ላይ መራመድ ብትችል እንኳ አስማት እንጂ ቅድስና አይመስላቸውም፣ እንዲያውም ዋና ስለማይችል ነው ሊሉህ ይችላሉ።
በጥቂቱ አግኝቶ ማመስገን የማይችል ለብዙ አይታጭም። በብዙ ተመኝተህ "ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ" እንዳትሆን በየጉዞህ ምዕራፍ አመስግን። ለምስጋና የሩቅ ረጅም ጉዞህ እስኪጠናቀቅ አትጠብቅ። በረጅሙ ጉዞ እየተጋህ በየምዕራፉ "ተመስገን" በል።
ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ከመሆን ይሰውረን።
አትቸኩል። የምትፈልገውን ለማግኘት በትዕግስት መትጋትንና በትጋት ውስጥ መጠበቅን ተለማመድ። ነገርህን "የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች" አታድርገው። እስራኤሎች የተስፋይቱን ምድር ለማየት 40 ዓመት በምድረ-በዳ መቆየታቸውን አስታውስ።
ትዕግስት፣ እምነትና ምስጋና ከሌለህ ግን ኑሮህ ምሬት የሞላው ይሆናል። ምሬተኛ ሁሌም በተሰጠው ጸጋና በረከት ከመደሰት ይልቅ በጎደለው ላይ አትኩሮ ይብሰከሰካል። ምሬተኛ ጋ ማንም ብዙ አይቆይም። የምሬተኛ ሞገድ/frequency ሰው በሩቅ ያባርራልና አታማርር።
ይልቅስ ባለህ አመስግን፣ አድንቅ/appreciate አድርግ። አቦ ሰው ሲደናነቅ ሲመሰጋገን ማየትና መስማት እንዴት ደስ ይላል!
ምስጋና የደስታ ውጤትና ምንጭ ነው።
ባለህ ተደሰት!
የሌለህን ለማግኘት በትዕግስት ትጋ!
አትዋከብ! አትቸኩል።
ምስጋናህ ግን በኑሮህ ላይ ባለህ ደስታ ይገለጽ።ኑሮህ፣ ህይወትህ፣ ስብከትህ ደስታህን ይመስክር።
በአፍህ ሳይሆን በኑሮህ ስበክ።
Getu k toughe
መልካም ምሽት
@EthioHumanity
@EthioHumanity
1.6K viewsedited 16:16