2023-04-17 09:08:46
ያ ገ ር ባ ህ ል
══ ❁ ══
ከፍቅሩ ኪዳኔ
'
ጥንት ልጆች ሆነን ባገራችን ባህል መሠረት የሚከበሩትን በዓሎች በሙሉ በደንብ እናከብር ነበር። ዋናው የወንዶች ልጆች በዓል በነሐሴ ወር የሚከበረው ቡሄ ነው። ለቡሄ ሳምንት ሲቀረው እያንዳንዳችን ጅራፍ ገምደን ስናጮህ እንውላለን እንጂ አንጋረፍም። በቅርብ የሚተዋወቁ የሠፈር ልጆች የራሳቸውን ቡድን አቋቁመው በቡሄ ማግስት ፀሐይ ሲጠልቅ ጀምረው ዱላቸውን ይዘው እየጨፈሩ ወደ ቤተሰብ ዘንድ እየሄዱ የቡሄ ዳቦና ፍራንክ በመሰብሰብ ያገኙትን ሁሉ ያለ ጭቅጭቅ ይካፈላሉ።
የኛ ሕዝብ ደግነቱንና ቸርነቱን የሚገልፀው በብዙ መንገድ በመሆኑ፣ በድሃም ሆነ በሀብታም ቤት፣ ልጆች ኖሩ አልኖሩ፣ እናቶች የቡሄ ዳቦን መጋገር እንደ ግዴታ በመውሰድ ወጣቱን ያስደስታሉ። የሚሰበሰበው ዳቦ ስለሚበዛ ለተቸገረ ማካፈል የተለመደ ነው። የቡሄ ጭፈራና ዘፈኖች ሆያ ሆዬና አሲዮ ቤሌማ ወግና ሥርዓት አላቸው። ሆያ ሆዬ ጉዴ፣ ጨዋታ ነው ልማዴ በማለት እውነት መናገር ነው።
የሴቶች ልጆች በዓል ደግሞ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ጋር የተያያዘ ነው። ከሜዳ የሚቀጥፉትን አደይ አበባ ይዘው እየዘፈኑ አበባ መስጠት ገንዘብ ያስገኛል። ወንዶቹም የተለያዩ የአበባ ሥዕሎችን በቀለም በመሳል ለቅርብ ቤተሰብና ለዘመዶቻቸው በማበርከት ሣንቲም ያጠራቅማሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ሸራ ጫማ የገዛሁት በዕንቁጣጣሽ ባገኘሁት ብር ነው። ፒያሳ የነበረው (አሁን የፈረሰው) ኪንግ ጆርጅ ቡና ቤት ገብቼ ኬክና አረንቻታ ገዝቼ የቀመስኩት በዚያን ወቅት መሆኑን አውቃለሁ። በመስቀል በዓል ሁሉም ችቦውን አዘጋጅቶ ወይም ገዝቶ እያንዳንዱ ሰው በአጥር ግቢው ውስጥ ከማቀጣጠሉ በፊት በየሠፈሩ ልክ እንደ ቡሄ ይጨፈራል። ያኔ ጉለሌ ጫካ ስለነበረው የአበባ፣ ዱላ፣ ጅራፍና ችቦ ችግር አልነበረም።
ገናን ሁሉም ከቤተሰቡ ጋር የሚያከብር ሲሆን፣ በጥምቀት ሁላችንም የሠፈራችንን ታቦት (ዮሐንስን) ተከትለን ወደ ጃንሆይ ሜዳ በመሄድ ብርድ እየፈደፈደን እናድራለን። በዚያን ጊዜ ሰዓት እላፊ ስለነበረ ከእኩለ ሌሊት በኋላ መነቃነቅ አይቻልም። ከቤታችን ውጭ የማደር ነፃነት የምናገኘው በጥምቀት በዓል ምክንያት ነው። በየሠፈራችን ከሚገኘው ዓረብ ሱቅ ዕቃ ለመግዛት ስንላክ ዓረቡ "ምራቂ" ብሎ ከሚሰጠን ብትን ስኳር በስተቀር ከረሜላ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ቴምር፣ ስኳር ድንች፣ ጉልባን፣ ተልባና እርጎ እንደልብ የምናገኘው በበዓላት ወቅት ነው።
በፋሲካ ትላልቆቹ ስለሚጾሙ እኛም በግድ እንጾማለን። ለፋሲካ ወደ ቤተክርስትያን መሄድ የተለመደ ነው። ትላልቆቹ ኃጢአታቸውን ከተናዘዙ በኋላ ስንት መስገድ እንዳለባቸው ሲነገራቸው፣ እኛ ደግሞ ተሰባስበን አንዱ የሌላውን ኃጢአት እያጋለጠ ስግደቱን ወደ ስፖርት ቀይረን ስንሰግድ ውለን እንገባለን። እግዚአብሔርም አልተቆጣንም። ...
በኛ ዘመን ልጆች ካባትና እናታቸው ጋር ወይም ከትላልቆቹ ሰዎች ጋር አብረው መብላት ክልክል ስለነበረ ቅልጥሙና የዶሮው ቆዳ ለኛ አይደርሰንም። እኔ ልጄን ሳሳድግ ጥሩ ጥሩውን ብልት እየመረጥኩ ስሰጠውና የፈለገውን ብስኩት፣ ጀላቲና ፉርኖ ገዝቼ ሳበላው ዕድለኛ መሆኑን የሚያውቅ አልመሰለኝም።
የዶሮ ዳቦ የሚደፋው ለፋሲካ ስለነበር ዕድል ያጋጠመው ዕንቁላል ያገኛል። ሌሊት ተነስተን ለማስፈሰክ ጠዋት ስንነሳ ፍትፍታችንን ግጥም አድርገን መብላት ነው። እኔ ከዶሮ ወጥ ይልቅ የሥጋ ወጥ የምመርጠው በእንጀራ የሚጠቀለል የተከተፈ ሥጋ ስለሚገኝበት ነው።
በዚያ በልጅነት ዕድሜ ቤተሰቦቻችን ናቸው ግብረ ገብን፣ ጨዋነትን፣ ታዛዥነትንና ሰው አክባሪነትን ያስተማሩን። ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ፀባይና ልምድ ያወረሱን።
>>>
━━━━━━━━
የፒያሳ ልጅ
ገፅ 25 - 27
https://t.me/Ethiobooks
745 viewsተስፋዬ መብራቱ, 06:08