2023-06-12 10:00:16
እስኪ እንመሰጋገን
═══✦═══
➠ ➠ ➠
ፊቷ በእሳት የተቃጠለ እናት የነበረችው አንድ ልጅ ነበረ። ምንጊዜም ሲወራ የሚሰማው ስለ እናቱ የተቃጠለ ፊት ስለነበረ በእናቱ ያፍር ነበር። ለጓደኞቹም ስለ እናቱ አይናገርም፣ እናቱም ከጓደኞቹ ጋር እንድትገናኝ አይፈልግም ነበር። በኋላም አድጎ ትልቅ ደረጃ ላይ ሲደርስ እናቱን የቤት ሠራተኛዬ ናት ብሎ ነበር የሚያስተዋውቃት። እናቱም ነገሩ ሁሉ ከምትታገሠው በላይ ሲሆንባት አንድ ቀን ጠራችው።
«ለመሆኑ ፊቴ ለምን እንደተቃጠለ ታውቃለህን?» ስትል ጠየቀችው። እርሱም ምንም እንደማያውቅ ነገራት። እርሷም እንዲህ አለችው፤ «ልጅ ሆነህ አንተን ቤት ውስጥ አስተኝቼ ከውጭ እህል ሳሰጣ እሳት ተነሣ። የእሳቱ ነበልባልም በአንድ ጊዜ ቤቱን ሞላው።
እኔም ያንተ መቃጠል ስላሳሰበኝ እየጮኽኩ ወደ ውስጥ ገብቼ በልብስ ሸፍኜ አንተን አወጣኹህ። አንተን አድናለሁ ብዬ እኔ ተቃጠልኹ። ዐየኽ፣ ያን ጊዜ ለራሴ ባስብ ኖሮ እተውኽና ትቃጠል ነበር። እኔ ግን ከራሴ በላይ ላንተ በማሰቤ በእሳት ውስጥ ገብቼ አወጣኹህ። የእኔ ውበት ካንተ ላይ ነው፤ ያንተ ጠባሳ ደግሞ ከእኔ ላይ ነው።» ብላ ነገረችው።
ጠባሳችንን ተሸክመው ምስጋናውን ያጡ ስንት ወገኖቻችን አሉ። ክፉ ክፉውን ብቻ እየተነጋገርን ለማመስገን፣ ለማክበር፣ ለማድነቅ፣ ለማበረታታት ዕድልኮ አላገኘንም። እስኪ በዓመት አንድ ቀን
የምስጋና ቀን ይኑረን።
በመንግሥት ደረጃ፣ በፓርቲ ደረጃ፣ በአካባቢ፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተሰብ መልካም የሠሩ፣ ለሕይወታችን መቃናት አስተዋፅኦ ያደረጉ፣ በበጎ ሐሳባቸው እና በበጎ ሥራቸው አርአያ የሚኾኑ፣ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉ ሰዎች
የሚመሰገኑበት ቀን።
የግድ ተስማምተን፣ ኮሚቴ አቋቁመን መምረጥ የለብንም። የሚያደርገው ካለ ግን እሰየኹ። በግላችን፣ በአካባቢያችን፣ በቤተሰባችን እኛ፣ መልካም ሠርቷል፣ መልካም ሥራውንም ልናደንቅለት፣ ልናውቅለት ይገባል። "በርታ ጠንክር" ልንለው ያስፈልጋል፤ የምንለውን ሰው ቢቻል በአካል፣ ባይቻል በስልክና በደብዳቤ «እግዜር ይስጥልን» የምንልበት -
የምስጋና ቀን።
በቤተሰብ ደረጃ በዚያ ዓመት በጠባዩ፣ በሥራው፣ በትምህርቱ ወዘተ... የተሻለ ኾኖ የተገኘውን ከማመስገን ጀምሮ ሌላው ቀርቶ ባል እና ሚስት እንኳን መጨቃጨቅ አቁመው አንዱ ለሌላው ያደረጉላቸውን በጎ ነገር የሚያወሩበት የሚያደንቁበት ቀን። ከመመራረር፣ ከመተቻቸት፣ ከመሰዳደብ፣ ከመወራረፍ በጎ በጎውን
የምናወራበት ቀን። ...
አበው «
ወድሶ ለሰብእ በዘኢኮነ ድልወ» ይላሉ። ይኸውም "
ሰውን በማይ'ገባው ነገር እንኳን ቢኾን አመስግነው" ማለት ነው። "ሳላደርግ እንዲህ ያመሰገነኝ ባደርገውማ ይበልጥ እመሰገናለሁ" ብሎ እንዲተጋ!
━━━━━━━━
የሁለት ሀውልቶች ወግ እና ሌሎች
ዳንኤል ክብረት
ገፅ 174 -176
2002 ዓ.ም
https://t.me/Ethiobooks
472 viewsተስፋዬ መብራቱ, edited 07:00