2023-03-20 10:01:20
ዘ - አልኬሚስት >>>
አንድ ባለ ሱቅ ልጁ ደስተኛ የመሆንን ሚስጥር እንዲያውቅ በዓለም ላይ ካሉ ጠቢባን ሁሉ በላይ ጥበበኛ ወደ ሆነ ሰው ላከው። ወጣቱ ለአርባ ቀናት በበረሃ ላይ ተጓዘ፤ በመጨረሻም ተራራ ጫፍ ላይ የተገነባ የሚያምር ህንፃ አገኘ። ጥበበኛውም የሚኖረው እዛ ነበር።
ቅጽሩንም አልፎ ሲገባ፣ ግርግር ተመለከተ። ነጋዴዎች ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ሰዎች በየጥጋጥጉ ያውካካሉ፤ ሙዚቀኞች ልብን የሚማርክ ዜማ ያወጣሉ፤ እናም አንድ ግዙፍ ጠረጴዛ ላይ ጣፋጭ ምግቦችና መጠጦች ተሰድረዋል። ጥበበኛውም እርሱን ሊጠይቁ ከመጡ ሰዎች ጋር እየተጫወተ ነበር።
ወጣቱም ተራው እስኪደርስ ለሁለት ሰዓታት ያህል መጠበቅ ነበረበት። ተራውም ሲደርስ ወደ ጥበበኛው ፊት ቀረበ።
ወጣቱ ለምን ወደዚህ እንደመጣ አብራራ። ጥበበኛውም የወጣቱን ምክንያት በጥሞና ካዳመጠ በኋላ "አሁን ለአንተ ደስተኛ የመሆንን ሚስጥር ለማስረዳት ጊዜ የለኝም፤ ከዚሁ ሳትርቅ ዙሪያ ገባውን እየቃኘህ ቆይና ከሁለት ሰዓታት በኋላ ተመለስ" አለው።
"ፍቃድህ ከሆነ፣ አንድ ነገር ላስቸግርህ" አለ ጥበበኛው፤ ለወጣቱ ዘይትን የተሞላ ማንኪያ እያቀበለው። "አጸዴን ስትጎበኝም ይህንን ማንኪያ ይዘህ ሂድ፤ አንዲትም ጠብታ ዘይት እንዳታፈስ።"
ወጣቱም ብዙ ደረጃዎችን ወጣ ወረደ። ብዙ ግርግሮችን፣ ብዙ ሰዎችንም አለፈ፤ ነገር ግን ዓይኖቹ ከማንኪያው ላይ አልተነቀሉም። ከሁለት ሰዓታት በኋላም ጥበበኛው ወደ ነበረበት ስፍራ ተመለሰ።
"እና?" ጥበበኛው ጠየቀ፤ "የምግብ አዳራሼ ውስጥ የተነጠፈውን የፋርስ ምንጣፍ አየኸው? አትክልተኞች ለመገንባት አስር ዓመታት የፈጀባቸውን የአትክልት ስፍራ ውበቱን አደነቅክ? ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ የነበሩትን ግዙፍ መጻሕፍትስ አስተዋልካቸው?"
ወጣቱ እንደ ማፈር አለና ምንም ነገር እንዳላየ ተናዘዘ። የእርሱ ማስተዋል በማንኪያው ዘይት አለመደፋት ላይ ያተኮረ ነበር።
"እንደዚያ ከሆነ፣ ተመልሰህ ሂድና ድንቁን ዓለሜን ተመልከት" አለ ጥበበኛው፤ "ቤቴንም ስታይ ስለኔ ጥበበኛነት ታውቃለህ።"
አሁን ጣራ እና ግድግዳው ላይ ያሉትን ጥበቦች በሙሉ ማድነቅ ጀመረ። የአትክልት ስፍራውን አየ፤ ስፍራው በበረሃ መሃል ያለ ገነት እንደሆነም አሰበ። ውብ አበቦችን፣ ጣፋጭ ምግቦችን፣ ቆነጃጅቶችንም ተመለከተ። የአእዋፋትን ዜማ ሰማ፣ የአበቦችንም መዓዛ ማገ።
ሁሉንም አይቶ ሲጨርስም ወደ ጥበበኛው ተመለሰ። ለጥበበኛውም አንድም ሳያስቀር ያየውን ሁሉ ተረከለት።
"አስደሳች ጊዜ ያሳለፍክ ትመስላለህ፤ ሆኖም ማንኪያው ላይ የነበረው ዘይት የት አለ?" ጥበበኛው ጠየቀ። ወጣቱ በእጁ ወደ ያዘው ማንኪያ ተመለከተ፤ የቀረ ዘይት የለም።
"ያው፣ ልሰጥህ የምችለው ምክር አንድ ነው" አለ ጥበበኛው ሰው። "
የደስተኛነት ሚስጥር ይሄ ነው፤ ዓለምን ሁሉ ተመልከት፣ በውበቷም ተደነቅ፣ በማንኪያ የያዝከውንም ዘይት አትርሳ!"
>>>
━━━━━━━━
ፓውሎ ኮኤልሆ
ጥበበ መልከ ጼዴቅ እንደተረጎመው
ገፅ 43 - 45
https://t.me/Ethiobooks
547 viewsተስፋዬ መብራቱ, 07:01