2023-03-13 10:01:10
የንጉሠ ነገሥቱ የሄሊኮፕተር አደጋ
═════ ✦ ═════
ንጉሠ ነገሥቱ ሰኞ መጋቢት 6 ቀን 1963 ዓ.ም. ለጉብኝት ከአዋሳ ቤተ መንግሥታቸው ወደ ብላቴን እርሻ በአየር ኃይል ሄሊኮፕተር እንደሚሄዱ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለአየር ኃይሉ ትዕዛዝ ደርሶታል። በዚሁ መሠረት ንጉሠ ነገሥቱና አጃቢዎቻቸው ቁጥሩ 777 በሆነ የሶቪየት ስሪት ሚ-8 ትልቅ የአየር ኃይል ሄሊኮፕተርና በሌላ አነስተኛ የአርሚ አቪዬሽን ሄሊኮፕተር ተሳፍረው በተባለው ቀን በአራት ሰዓት አካባቢ ከአዋሳ ወደ ብላቴን በረሩ።
የብላቴን ጉብኝት ካለቀና ምሳ ከተበላ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱና አስራ አምስቱ ተከታዮቻቸው በዚሁ ሚ-8 ሄሊኮፕተር ተሳፈሩና ከብላቴን ለመነሳት በሚያደርገው ዝግጅት የያኔው የአየር ኃይል አዛዥ የሚቀጥለውን የጉዞ አቅጣጫ ለፓይለቶቹ ለማመልከት ሲባል ከዋናው ፓይለት ኋላ በሚገኘው የቴክኒሺያኑ መቀመጫ ላይ ይቀመጣሉ።
ሄሊኮፕተሩ ለወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ ከመሬት ብድግ ብሎ ትንሽ ቆም ካለ በኋላ ፍጥነት ለማግኘት ሲባል ከሦስት ሜትር ያህል ከፍታ ፊት ለፊት መብረር ጀምሮ የታረሰው መሬት አካባቢ ሲደርስ ራሱ ባስነሳው ከባድ አቧራ ሙሉ ለሙሉ ይሸፈናል። በዚህን ጊዜ የአየር ኃይሉ አዛዥ ፖል! ፖል! (የቆመ እንጨት!) በማለት በመደጋገም ጮክ ብለው ይናገራሉ። ፓይለቱ ከኮክፒቱ ውጪ ምንም ስለማይታየው ሄሊኮፕተሩን በትክክል ማብረር ባልቻለበት ሁኔታ ሄሊኮፕተሩ ወደ ግራ እየዞረና እየወረደ ሄዶ በግራ እግሩ መሬት ይነካል።
በሁኔታው የተደናገጠው ፓይለት ሄሊኮፕተሩን ወደ ቀኝ ለመመለስ ባደረገው ጥረት ሄሊኮፕተሩ ከአፍንጫው ከፍ ብሎ ወደ ቀኝ ጎኑ ይገለበጣል። ወዲያው ጭራው ላይ ያሉት አነስተኛ ውልብልቢቶች (Tail Rotors) መሬቱን እያረሱ መሰባበር ይጀምራሉ። ሄሊኮፕተሩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀኝ ሲወድቅ ዋነኞቹ ውልብልቢቶች (Main Rotors) መሬቱን እያረሱ መሰባበር ይጀምራሉ። በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ድምፅ እየተሰማ ሄሊኮፕተሩ መሬቱን እያረሰና እየተሰባበረ መዞሩን ቀጠለ።
ፓይለቶቹ በታሰሩበት ቀበቶ ተይዘው በጎናቸው ተንጠለጠሉ። በወንበሩ ቀበቶ ሳይታሰሩ የነበሩት የአየር ኃይል አዛዥና ቴክኒሺያኑ በጣም ተንገላቱ። በነበረው ሁኔታ ማናቸውም ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ሞተሮቹን እንኳን ቶሎ ለማጥፋት ሳይቻላቸው ቀረ። በመጨረሻም ሄሊኮፕተሩ መሬቱን እያረሰና እየተሰባበረ አንድ ሙሉ ዙሪያ ከዞረ በኋላ ቆመ።
ፓይለቶቹና ቴክኒሺያኑ የሞተሮቹንና ሌሎችንም መቆጣጠሪያዎች ካጠፉ በኋላ በጎን በኩል በተሰበረ መስኮት ሾልከው በመውጣት ከኋላ ዞረው የተሳፋሪዎችን በር ከፈቱት። ንጉሠ ነገሥቱና አጃቢዎቻቸው በየወንበሩ ላይ በሚገኘው ቀበቶ ታስረው በየጎናቸው ከተንጠለጠሉበት እየተፈቱ በነበረው ህዝብና ወታደር እርዳታ በደህና ለመውጣት ቻሉ።
በኋላ እንደተደረሰበት የውልብልቢቶቹ ስብርባሪዎች ከአደጋው ቦታ እስከ ሁለት መቶ ስድሳ ሜትር ድረስ በረው ሦስት ሰዎችን መትተው ገድለዋል። ከአደጋው በኋላ አብራሪዎቹ ለጊዜው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ነገር ግን ወዲያውኑ ከንጉሠ ነገሥቱ በተላለፈ ትዕዛዝ ተለቀዋል። .......
የአደጋ ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ለንጉሠ ነገሥቱ በጽሕፈት ቤታቸው ገለፃ ተደርጎላቸዋል። ከገለፃው በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ አንዳንድ ቴክኒካዊ ጥያቄዎችን ጠይቀው ሲያበቁ "ልጆቹ (ማለትም ፓይለቶቹና ቴክኒሺያኑ) ያለ ምንም ስጋት ሥራቸውን እንዲሠሩ ንገሯቸው..." ብለው ጉዳዩ በዚሁ ተዘጋ።
┈┈••┈┈••┈┈
(ከዚህ በላይ የቀረበውን ጽሑፍ ያዘጋጁት ሌ/ኮሎኔል ውብሸት ተፈራ በጊዜው የበረራ ሴፍቲ ዳይሬክተር የነበሩና አደጋውን በሊቀ መንበርነት መርምረው ውጤቱን ለንጉሠ ነገሥቱ ገለፃ ያደረጉ ናቸው።)
━━━━━━━━
አቪዬሽን በኢትዮጵያ
ካፒቴን መኮንን በሪ
https://t.me/Ethiobooks
475 viewsተስፋዬ መብራቱ, 07:01