2023-05-08 09:49:10
ከአቅም በላይ
══❁══
አቦነህ አሻግሬ
'
>>>
እንግሊዛዊው የታሪክና የሥነ-ኅብረተሰብ ምሁር ሔንሪ ቶማስ በክል፣ የአስራ ስምንት ዓመት ወጣት ሳለ፣ ስለ ዓለም ስልጣኔ ታሪክ ሊጽፍ ወሰነ። እንዲህ ዓይነቱን ታላቅና ሰፊ ሥራ ለመሥራት በተፈጥሮአዊ ሳይንስ፣ በተለያየ ቋንቋ፣ በታሪክ፣ በሕግና በዓለም ስነ-ጽሑፍ የጠለቀ እውቀት ተክኖ መገኘትን በመጠየቁ፤ በክል ይህን ሁሉ ለማጥናት ቆርጦ ተነሳ።
አብዛኛውን ጊዜውን በመጻፊያ ክፍሉ ውስ ጥ በመወሰኑ ከነአካቴው ከሰው ጋር ከመገናኘትና ማኅበራዊ ጭውውት ከማድረግ ራቀ። ከስነ-ጥበብና ከሙዚቃ ተለየ። ከሞዛርትና ከቤትሆቨን ሊለይ እንኳ አይችልም ነበር። ወደ ቲያትርና የስዕል ኤግዚቢሽን አይደርስም። ይወደው ከነበረው የቼስ ጨዋታም ተገለለ።
ይህ ከፍተኛ ጥረት ግን ፍሬ አፍርቶለታል። በክል አስራ ዘጠኝ ቋንቋዎችን አጠና። ከሚነጋገርበት ደረጃ ላይ ባይደርስም ለሥራው የሚያስፈልጉትን ሀሳቦች በንባብ ከሚረዳበት ደረጃ ላይ አደረሱት። ውሎ ሲያድር ግን ሊሠራው ያቀደው ሥራ እጅግ ሰፊና ከቶ ሊጠናቀቅ የማይችል መሆኑን ተረዳ።
«የሰው ልጅ ስልጣኔ ታሪክ» በሚል ሊጽፍ የነበረውን ሰፊ ርዕስ አጥብቦ ስለ አውሮፓ ስልጣኔ ታሪክ ብቻ መጻፍ ጀመረ። ቆይቶ ሲያስበው ይህም የማይቻለው ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻው ላይ «የእንግሊዝ ስልጣኔ ታሪክ» ወደሚለው ርዕስ ወረደ። ታሪኩን በአስራ አምስት ጥራዝ ሊያጠቃልልም እቅድ አወጣ። ምን ያደርጋል ታዲያ፣ ሁለት ጥራዝ ብቻ እንደጨረሰ በ41 ዓመቱ ሞተ። ያለመውን ሳያጠናቅቅ ሥራው ቀድሞ አጠናቀቀው።
ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት አስፈላጊ ነበር? አልነበረም። በአኳያውም በአነስተኛ ጥረት መወሰን ደግ አይደለም።
አንጎልን በበቂ ሁኔታ አለማሠራት እድገቱን ቀስ በቀስ ማቀጨጭ ነው። የማሰብ ችሎታውን ውስን አድርጎ ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥበትን የአፍላቂነት ኃይሉን መግታት ነው። የአፍላቂነት ኃይል መዳከምና ሐሳበ ውስንነት ደግሞ ጠንክሮ ለመሥራት ብርታት የሚጎድላቸው ሰዎች ባህርይ ነው።
በረቀቀና የሰከነ እቅድ ከሚመሩ ታታሪ ተማሪዎች ይልቅ፣ አነስተኛ ጥረት የሚያሳዩ ተማሪዎች የበለጠ የድካምና የጭንቀት ስሜት እንደሚታይባቸው የስነ-አእምሮ ጥናት ያመለክታል።
የሰው ልጅ ሥራው የሚጠይቀውን ያህል አእምሮውን ሊያሠራው ይገባል - ባቅሙ፣ በልኩ። ... ይህን በወጉ ያልመለሰ ታታሪ፣ በአሰቃቂ ጭንቀትና ድካም ሕይወቱን አልፍቶ አላፊ ይሆናል። ...
>>>
━━━━━━━━
እፍታ - ቅጽ 1 (44 ትረካዎች)
በ29 ጋዜጠኞችና ደራሲያን
1991
https://t.me/Ethiobooks
1.1K viewsተስፋዬ መብራቱ, 06:49