2023-04-01 17:41:30
የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ረቂቅ አዋጅየመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ ራስ ገዝ ሲሆኑ የሚሾሙላቸው ፕሬዝዳንቶች የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
ባለፈው ሐሙስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች አሿሿም እና የሥራ ዘመን ላይ ለውጦችን አድርጓል።
ረቂቁ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንት ሹመት የሚከናወነው “በዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ይሆናል” ሲል ያስቀምጣል።
የዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንት የሚሾመው “በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽ በሆነ ውድድር” መሆኑን የሚያትተው አዋጁ፤ በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ቦርድ አቅራቢነት ከሚቀርቡ ሦሥት ዕጩዎች መካከል የዩኒቨርሲቲው “ቻንስለር” ፕሬዝዳንቱን እንደሚሾሙ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
በረቂቁ መሰረት ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ያሸነፈ ግለሰብ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከሆነ ከፓርቲ አባልነት ለመልቀቅ መስማማት ይኖርበታል።
በቀዳሚነት ራስ ገዝ እንደሚሆን የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጣሰው ወልደሃና በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲን ወክለው አባል ናቸው።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊልም በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የፓርላማ አባል ናቸው።
ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሆነው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠናም በተመሳሳይ ብልጽግናን ወክለው ፓርላማ ገብተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ያስተዋወቀው ሌላኛው አዲስ ነገር “የዩኒቨርሲቲ ቻንስለር” የተባለውን የኃላፊነት ቦታ ሲሆን በአዋጁ መሰረት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት የሚጀምረው ከ“ቻንስለር” ነው።
ቻንስለሩ በዩኒቨርሲቲው የውስጥ አስተዳደር ውስጥ ሳይገባ “እንደ ከፍተኛ አምባሳደር የሚያገለግል፣ ሃብት የሚያፈላልግና ሌሎች በጎ ተግባራትን የሚያከናውን” እንደሚሆን በረቂቁ ተቀምጧል።
በአዋጁ መሰረት ራስ ገዝ ለሚሆኑ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች “ቻንስለር” የሚሾመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ቻንስለሩ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል ይሆናል።
በረቂቁ ጠንካራ የፋይናንስ አቅምና አካዳሚያዊ ተወዳዳሪነት፤ ራስ ገዝ ለመሆን ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች መካከል ተጠቅሰዋል።
ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ በትምህርት ሚኒስቴር ዕቅድ ተይዟል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ በጀት ዓመት የራስ ገዝ አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በመንግስት ከሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በስጦታ፣ በኑዛዜ፣ ከፈጠራ ገቢ እና ከትምህርት ከፍያ ሊያገኙ እንደሚችሉ በረቂቁ እንደሰፈረ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባ ያሳያል።
Join AND share our channel
https://t.me/+5UtUmeE0OYAwOGU8
https://t.me/+5UtUmeE0OYAwOGU8
2.5K viewsFOREVER, 14:41