2024-03-16 03:35:57
ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል ለበርካቶች የተሰጠው የ African Leadership Magazine Award ምንድን ነው?
አዩሬ አታፎሪ የተባለ ጋናዊ ጋዜጠኛ ሰሞኑን ያዘጋጀው የ African Governance Award ለኢንደስትሪ ሚኒስትራችን መበርከቱንና ከጀርባው ያሉ አንዳንድ መረጃዎችን አካፍዬ ነበር።
እስቲ የትናንት ምሽቱን ሽልማት ትንሽ እንፈትሸው።
የ African Leadership Magazine Award የሚዘጋጀው ደግሞ በናይጄርያዊው ጋዜጠኛ ኬን ጊአሚ ነው። ኬን ከዚህ በፊት 11 ግዜ ሽልማቶችን አዘጋጅቶ ሸልሟል፣ የዚህ አመት ሽልማቱም እንደ ሁል ግዜው ግርታን የሚፈጥር ሆኗል።
እንዴት?
1. ድርጅቱ በፌስቡክ ገፁ ላይ የዘንድሮ የሽልማቱ አሸናፊዎች ብሎ የዘረዘራቸው የኬንያው ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ፣ የቀድሞው የላይቤርያው መሪ ጆርጅ ዊሀ፣ የታንዛኒያዋ ፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሁሉ... ወዘተ ነበሩ (ማስረጃ: ስክሪንሾት ይመልከቱ)። ተሸላሚዎቹ በዛሬው እለት በስካይ ላይት ሆቴል ተገኝተው ሽልማት እንደሚወስዱ በስፋት አስተዋውቆ የመግቢያ ትኬት የሸጠ ቢሆንም በስፍራው አልተገኙም።
2. የቀድሞው ጠ/ሚር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ተሸላሚ እንደሆኑ በሰበር ዜና ገልፆ ነበር (ማስረጃ: https://www.facebook.com/share/p/pwqFJvcY4eFx4TjM/?mibextid=Nif5oz) እርሳቸው ግን መገኘት እንደማይችሉ ሲገልፁ ከሽልማት ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተቱ የደረሰኝ መረጃ ይጠቁማል። መገኘት ያልተመቸው ባይሆን በተወካይ ይወስዳል እንጂ እንዴት ከዝርዝር ይወጣል የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው።
3. ልክ እንደ አቶ ሐይለማርያም ሁሉ የቦትስዋናው 'ሉካራ' ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ናሲም ላህሪ የዘንድሮው 'ምርጥ የሴት መሪ/አመራር' ተብለው ይፋ ከተደረጉ በኋላ ማምሻውን ሽልማቱ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ ተበርክቷል (ማስረጃ: ስክሪንሾች ተያይዟል)።
4. የትናንት ምሽቱን ፕሮግራም ወጪ የሸፈነው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ነበር። እንደገና ይሄው መፅሄት የኮሚሽኑን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ "በመንግስት አገልግሎት ላበረከቱት አስተዋፅዖ" በሚል ሽልማት ሰጥቷል። የፕሮግራም ስፖንሰርን መልሶ መሸለም የጥቅም ግጭት መፍጠሩ የማይቀር መሆኑ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ መሸላለም መሆኑ ግልፅ ነው። አቶ ደበሌ ከዚሁ ተቋም የዛሬ አመት ሌላ ሽልማት ወስደው ነበር (ማስረጃ: https://www.facebook.com/share/p/cvKWKss1tzg9g66u/?mibextid=Nif5oz)
ማሳረጊያ:
አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ነገር ቢኖር የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች "ሽልማት አገኘን" የሚል ዜና መስማት ነው። እርግጥ ነው ትክክለኛ አለም አቀፍ እውቅና የሚያገኙ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይነት ተቋማት አሉ፣ ግን ሌላ ጨዋታም አለ።
ታድያ ለእንዲህ አይነት ዜና ያለውን ከፍተኛ ጥማት የተረዱት በተለይ ናይጄርያውያን እና ጋናውያን ጋዜጠኞች ተፍ ተፍ እያሉ ይገኛሉ፣ ሽልማቶችን በገፍ ያከፋፍላሉ። ከዛም ለሚድያቸው የሚሆን ለማስታወቂያ በሚል ዳጎስ ያለ ክፍያ ይቀበላሉ፣ የሽልማት ስነ-ስርዐት አዘጋጅተው አንደኛ-ሁለተኛ-ሶስተኛ ደረጃ ስፖንሰር ብለው ከፋፍለው ገቢያቸውን ያጦፋሉ።
@EliasMeseret
36.5K viewsElias M, 00:35