2022-11-06 20:28:19
#የሮሜ_መልእክት_ጥናት
ስለዚህ ሥራችንን በማየት እግዚአብሔር እምነታችን እውነት ወይም ሐሰት እንደሆነ ያውቃል። እግዚአብሔር በሥራችን መጠን ሲፈረድብን በእምነታችንም ላይ ነው የሚፈረድብን። ነገር ግን ማስታወስ የሚገባን ደኅንነትን የምናገኘው በእምነት እንጂ በሥራ አለመሆኑን ነው። እምነት ከሥራ ቀድሞ መገኘት አለበት። ከእምነት በኋላ ደኀንነት፤ ከደኅንነት በኋላ ሥራ መምጣት አለበት።
ብዙ ሰዎች መልካም ሥራ የሚሠሩት አንድ ሃይማኖታዊ በረከት ለመቀበል ወይም አንድ መንፈሳዊ ብጽዕና ለማግኘት ነው። ይህን የመሰለ መልካም ሥራ ከስስት ሊመነጭ ይችላል። በተቃራኒው ከዚህ ከስስት ከሚመነጭ "መልካም ሥራ" አንጻር ከእምነት የሚመነጭ መልካም ሥራ ከስስት ነፃ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ከእምነት የተነሣ የሚመጣው መልካም ሥራ ሁልጊዜ የሚደረገው ለእግዚአብሔር ክብርና ሌሎችን ለመጥቀም ነው።
7. በመልካም ሥራ መጽናት በጣም አስፈላጊ ነው። የእኛ መልካም ሥራ የማያቋርጥ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም መልካም ሥራዎቻችን የሚመነጩት ከማያቋርጥ እምነታችን ነው።
ጳውሎስ እነዚህን ዘወትር መፈለግ አለባችሁ ብሎ የሚያሳስበን ስብሐት፥ ክብርና ለዘላለም ነዋሪነት የምድር ሳይሆኑ፥ የሰማይ ናቸው። ዓይናችንን በሰማያውያን ነገሮች ላይ ማተኮር አለብን (ቆላ. 3፥1)። እግዚአብሔር ስብሐትን፥ ክብርንና ለዘላለም ነዋሪነትን ንስሓ ለገቡና በክርስቶስ ላመኑ ሁሉ በሰማይ ይሰጣቸዋል።
8-9. እዚህ ላይ የተጠቀሰው መዓትና ቁጣ (ቁ. 8)
የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ፍርድ የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ፍርድ በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ ቀጥሎም ለአረማዊ (ግሪካዊ) ነው የሚሆነው። ለአይሁዳውያን ታላቅ መወደድና ታላቅ ዕውቀት ተሰጥቶአቸው ስለነበረ ለኃጢአታቸውም የሚቀበሉት ቅጣት ታላቅ ይሆናል። የምንቀጣውም በሠራነው ክፉ ነገር ብቻ ሳይሆን፥ ባወቅነው የእግዚአብሔርንም ፈቃድ መጠን ነው። ለትንንሽ ሕፃናት አነስተኛ ቅጣት እንሰጣቸዋለን፤ ምክንያቱም ትክክል የሆነውንና ስሕተት የሆነውን ለይተው የሚያውቁት አነስተኛ በሆነ ሁኔታ ነው። ነገር ግን ዕውቀታቸው ታላቅ ለሆነው፥ ቅጣታቸውም ታላቅ ይሆናል (ሉቃ. 12፥47-48)።
10-11. የእግዚአብሔር ሽልማትም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ ቀጥሎም ለአረማዊ ነው። አይሁዳዊያን ሽልማታቸውን ለመቀበል መጀመሪያ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም እነርሱ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ስለሆኑ ነው። ይሁን እንጅ አይሁዳዊም ሆነ አረማዊ የሚሸለሙት ወይም የሚቀጡት በሥራቸው መጠንና በዕውቀታቸው መጠን ነው። እግዚአብሔር አይሁዳውያንም ሆነ አረማውያንን የሚቀጣው በአንድ ዓይነት ሁኔታ ነው፤ እግዚአብሔር በፍርዱ አድሎ አያደርግም (ቆላ. 3፥25)። አይሁዳውያን ከቅጣት የሚያመልጡ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን ሊያመልጡ አይችሉም።
12. እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሕግ የአይሁዳውያን ሕግ ሲሆን ይህም እግዚአብሔር ለአይሁዳውያን የሰጣቸው ሕግ ማለት ነው። ይህ ሕግ የሚገኘው በብሉይ ኪዳን በመጀመሪያዎቹ አምስት መጻሐፍት ውስጥ በተለይም በዘጸአት፥ በዘሌዋውያን፥ በዘኁልቁና በዘዳግም መጻሕፍት ውስጥ ነው። እዚህ ላይ ጳውሎስ "ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ ኃጢአት የሚሠሩ" ሲል የሚያመለክተው አረማውያንን ነው።
አይሁዳውያንም ሆኑ አረማውያን በኃጢአታቸው ምክንያት ይቀጣሉ። ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ ኃጢአት የሠሩት አረማውያን ጽድቅ በተሞላበት በእግዚአብሔር ፍርድ ይቀጣሉ፤ ከሕግ በታች እያሉ ኃጢአት የሠሩት አይሁዳውያን ደግሞ በአይሁድ ሕግ መሠረት ይቀጣሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሕግ ለአይሁዳዊም ቢሆን መሰናክል ይሆንበታል እንጅ ምንም ጥቅም አይሰጠውም፤ ምክንያቱም በሁሉ አቅጣጫ ለሕግ ታዛዥ ሆኖ መገኘት ስለማይቻል ነው። ስለሆነም ሕግ እነርሱን ከመከላከል ይልቅ ይፈርድባቸዋል (ገላ. 3፥10፤ ያዕ. 2፥10)።
እዚህ ላይ ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፥ አረማውያን ሕግ ከሌላቸው እንዴት ሊቀጡ ይችላሉ? አረማውያን ሕግ አላቸው ፤ ነገር ግን ሕጉ የአይሁዳውያን ሕግ አይደለም፤ ሕጋቸው ተፈጥሮአዊ ሕግ ነው። ይህም ወደኋላ መለስ ብለን በምዕራፍ 1 ላይ ጳውሎስ ያቀረበውን ገለጻ እንድንመለከት ያደርገናል። እርሱም በዚያ ላይ ሰዎች የማይታዩትን የእግዚአብሔርን ባሕሪያት ማለትም ዘላለማዊ ኀይሉና አምላክነቱን ለማየት ይችላሉ ይላል (ሮሜ 1፥20)። ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ ትክክል በሆነ ነገርና ስሕተት በሆነ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ይችላሉ። ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ ኃጢአት ምን እንደሆነ ለይተው ማወቅ ይችላሉ። ሰዎች ሁሉ ሕሊና አላቸው፤ ስለዚህ ለሰዎች ሁሉ የተፈጥሮ ሕግ አለ ማለት እንችላለን። ይህም ሕግ በልባቸው ተጽፎአል (ቁ. 15)። እንግዲህ በአረማውያን ላይ የሚፈረድባቸው በዚህ ሕግ መሠረት ነው።
13. ጳውሎስ አይሁዳውያንን የሚነግራቸው፤ በሕይወት የማይተረጉሙት ከሆነ ሕግን መስማት ብቻ ምንም ጥቅም የለውም (ያዕ. 1፥22) በማለት ነው። ሰው ጻድቅ የሚሆነው ወይም ደኅንነትን የሚያገኘው ሕግን ሙሉ በሙሉ የሚፈጽም ከሆነ ብቻ ነው።
14–15. ብዙ አረማውያን ምንም እንኳ የአይሁዳውያንን ሕግ የማያውቁ ቢሆኑም፤ ሕግ የሚለውን ሁሉ በተፈጥሮ ያደርጉታል (ቁ. 14)፥ ለተፈጥሮ ሕግም ይታዘዛሉ። ለምሳሌ የአይሁዳውያን ሕግ አትግደል ይላል (ዘጸ. 20፥13) እንደገናም አትስረቅ ይላል (ዘጸ. 20፥15) ይሁን እንጂ አረማውያንም ቢሆኑ ምንም እንኳ የዘጸአትን መጽሐፍ አንብበው ባያውቁም መግደልና መስረቅ ትክክል እንዳልሆነ ያውቃሉ። የአይሁዳውያን ሕግ ሰው ለጎረቤቱ ምሕረት ማሳየት አለበት ይላል፤ አረማውያንም ቢሆኑ እነዚህን ሁሉ ያደርጋሉ። አረማውያን በትክክለኛ ድርጊትና በስሕተት መካከል ያለውን ልዩነት ያውቃሉ፤ ምክንያቱም ሕሊናቸው (ቁ. 15) ልዩነቱን ያሳያቸዋል። ክፉ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜ ሕሊናቸው ይወቅሳቸዋል፤ መልካም ነገር በሚያደርጉበት ጊዜ ሕሊናቸው ይመሰክርላቸዋል።
በአንዳንድ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ በአይሁዳዊ ሕግና በአረማዊ የተፈጥሮ ሕግ መካከል ብዙ ልዩነት የለም። ዋናው ልዩነት ግን ይህ ነው የአይሁድን ሕግ በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ የጻፈው እግዚአብሔር ሲሆን (ዘጸ. 24፥12)፤ የአረማውያን የተፈጥሮ ሕግ ግን የተጻፈው በልባቸው ነው (ቁ. 15)።
16. እግዚአብሔር የሚፈርድበት ቀን የመጨረሻው የፍርድ ቀን ይባላል (ቁ. 5)። እግዚአብሔር በሰዎች ላይ የሚፈርደው በውጪያዊ ሥራቸው መሠረት ብቻ አይደለም ነገር ግን በሚስጥራዊ ሥራቸውም ጭምር ይፈርድባቸዋል። ይህም በውስጣዊ አሳባቸውና ዓላማቸው ጭምር ማለት ነው። እግዚአብሔር የእያንዳንዳችንን "ምስጢር" ያውቃል፤ ሁሉንም ነገር ያያል።
እግዚአብሔር የሚፈርደው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። ክርስቶስን የሚቀበሉ ሁሉ ይድናሉ፤ ክርስቶስን አንቀበለውም ብለው የናቁት ሁሉ ይጠፋሉ። እንደ እውነቱ ከሆነም ፈራጃችን ራሱ ክርስቶስ ነው፤ (ዮሐ 5፥22፤ ሮሜ 14፥10፤ 1ቆሮ. 4፥4፤ 2ቆሮ. 5፥10)።
ምንጭ፦ የአዲስ ኪዳን ማብራሪያ፣ ገጽ 348-349
━━━━━━✦✗✦━━━━━━━
⇲⇲⇲⇲ ሼር ያድርጉ!! ⇲⇲⇲⇲
─── ❖ ── ✦ ── ❖ ───
SHARE SHARE SHARE
JOIN US
@christ_mossion
@christ_mossion
@christ_mossion
381 views✞Natneal, 17:28