2023-01-01 19:52:55
#ቃልም_ሥጋ_ሆነ
ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ወልድ ክፍል-1
ኢየሱስ ማነው? ይህ በምድር ላይ የሚኖር ሁሉም ሰው ሊመልሰው የሚገባ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ እርሱ ታላቅ የሃይማኖት መምህር ነበርን? ወይንስ አእምሮውን የሳተ ሰው? አምላክ ነበር ወይንስ ሰው ብቻ? የእርሱን ማንነትና ሥልጣን በተመለከተ ትልቅ ክርክርና ጭቅጭቅ አለ፡፡ ብዙ ሰዎች ትህትናን የተሞላ ሥነ ምግባርን ያስተማረ ሥርኣት ላለው ማሕበረሰብ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሰው ብቻ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ነገር ግን ሕይወቱንና ትምህርቱን በጥንቃቄ ካጠናን ይህ አማራጭ ውድቅ ይሆናል፡፡
ሲ ኤስ ሌዊስ የተሰኘው ዝነኛ የእንግሊዝ ጸሐፊና ፈላስፋ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“እንደ ሞኝ ሰው ቆጥራችሁት ዝም ልታሰኙትና እንደ ክፉ ጋኔን ቆጥራችሁ ልትገድሉት ትችላላችሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በእግሮቹ ስር ተንበርክካችሁ ጌታዬና አምላኬ ብላችሁ ልትጠሩት ይገባል፡፡ ነገር ግን ታላቅ የሆነ ሰብዓዊ መምህር ብቻ ነበር የሚለውን የቂላቂል ንግግር አንናገር፡፡ ያንን አማራጭ እንድንይዝ ምንም ክፍተት አልተወልንም፡፡ በጭራሽ አላሰበውም፡፡”
እውነታው ኢየሱስ አምላክ መሆኑ ነው፡፡ የስህተት ትምህርቶችን የመለያ ጥሩ መንገድ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚያስተምሩ መመርመር ነው፡፡ ኑፋቄዎችና ሐሰተኛ አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ የክርስቶስን አምላክነት ይክዳሉ፡፡ ለክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ የምናምነው ነገር ደህንነታችንን ይወስናል፡፡ ስለ እርሱ ያለን ዕውቀት ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ዓላማ ያለንን መረዳት እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ይወስናል፡፡
ሰዎች ማንነቱን በተመለከተ ግራ ቢጋቡም እውነተኛ ተከታዮቹ እንደሚያውቁትና እርሱም እንደሚያውቃቸው ኢየሱስ ተናግሯል (ማቴ. 7፡21-23)፡፡ ስለዚህ የኢየሱስን ማንነት ጠንቅቆ መረዳት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ራሱን ስለገለጠልን ስለ ኢየሱስ ለማወቅ ዋነኛ ምንጫችን እርሱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረው ነገር ብዙ ጎን ያለው ምስል ይሰጠናል፡፡ ኢየሱስ ስለ ራሱ የተናገረውንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን የተናገሩትን በማየት እግዚአብሔርን የበለጠ ልናውቀው እንችላለን፡፡
መለኮትነቱዛሬ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስን ሰው መሆን ይጠራጠራሉ ነገር ግን አምላክነቱን የሚክዱት እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር መገለጥ ገና ከጅምሩ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ የኢየሱስን ልደትና ንግሥና አስቀድሞ በተነበየበት ትንቢቱ ውስጥ አምላክነቱን ይናገራል፡-
“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡” (ኢሳ. 9፡6)
ኢየሱስ ራሱ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ በማወጅ አምላክነቱን ተናግሯል (ዮሐ. 10፡33)፡፡ የዘመናችን ምሑራንና ተጠራጣሪዎች ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ሊከራከሩ ይችላሉ ነገር ግን በእርሱ ዘመን የነበሩት አድማጮቹ በትክክል ተረድተውታል፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡-
“ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት፡፡” (ዮሐ. 10፡33)
ኋላ ላይ ደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞና አለመረጋጋት በበዛበት ሰዓት ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” በማለት አረጋገጠላቸው (ዮሐ. 14፡9-13)፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ አብን ሊገልጠው ነው የመጣው (ዮሐ. 1፡18)፡፡ አምላክ መሆኑንና ከአብ ጋር ያለውን ቁርኝት በግልፅ ስለ ተናገረ ተከታዮቹ ሊረዱና በዚህ እውነት ሊፅናኑ ይችላሉ፡፡
በብሉይ ኪዳን የኢየሱስ አምላክነት ከመነገሩና ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ መሆኑን ከመናገሩ በተጨማሪ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያንም መለኮት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክርስቶስን ታላቅነትና የዘፍጥረትን የፍጥረት ጅማሬ ትረካ በማመላከት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፡- “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፡፡” (ቆላ. 1፡16) የመፍጠር ሥልጣን የእግዚአብሔር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ሥልጣን ከኢየሱስ ጋር አያይዞታል፡፡
የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ የኢየሱስን አምላክነት በተመለከተ አስገራሚ ነገር ይናገራል፡-
“እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፡፡” (ዕብ 1፡3)
በዚህ ቦታና በመላው አዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተገለጠው የኢየሱስ አምላክነት የተልዕኮውና የአገልግሎቱ ማዕከላዊ ነገር ነው፡፡ ሰዎች ይህንን እውነት ቢቀበሉም ቢቃወሙም ከልባቸው ሊክዱት አይችሉም፡፡
ይቀጥላል...
━━━━━━✦✗✦━━━━━━━
⇲⇲⇲⇲ ሼር ያድርጉ!! ⇲⇲⇲⇲
─── ❖ ── ✦ ── ❖ ───
SHARE SHARE SHARE
JOIN US
@christ_mossion
@christ_mossion
@christ_mossion
535 views✞Natneal, 16:52