2023-04-18 08:03:51
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ብረት ለበስ ተሽከርካሪው " ሆን ተብሎ " በጥይት መደብደቡን ኢምባሲው ያስታወቀ ሲሆን ድርጊቱን የፈፀመው ሄሜቲ የሚመሩት RSF ቡድን መሆኑን ኤምባሲው ለአል አረቢያ ገልጿል።
ኤምባሲው ተሽከርካሪው በ100 ጥይት መደብደቡን ገልጾ ድብደባው ያደረሰው ምንም ጉዳት የለም ብሏል።
በሌላ በኩል ፤ የአሜሪካ መንግሥት ጦርነት ውስጥ ካለችው ሱዳን ዜጎቹን የማስወጣት እቅድ እንደሌለው ዋይትሃውስ አሳውቋል።
በተያያዘ ዜና በሱዳን ካርቱም ሚገኙት የአውሮፓ ህብረት (EU) አምባሳደር በመኖሪያ ቤታቸው ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ተሰምቷል ።
አምባሳደሩ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ያሳወቁት የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል ናቸው (በትዊተር ገፃቸው)።
ቦሬል ስለ ጥቃቱ ምንም አይነት ዝርዝር ነገር ባይገልጹም አምባሳደሩ ግን " ደህና ናቸው " ብለዋል።
የዲፕሎማቲክ ቦታዎችን እና ሰራተኞችን ደህንነት ማስጠበቅ የሱዳን ባለስልጣናት ቀዳሚ ኃላፊነት ነውም ሲሉ ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ቦሬል ፤ በሱዳን የአውሮፓ ህብረት አምባሳደርን ስም ባይፅፉም ስማቸው አይዳን ኦሃራ የሚባሉ ሲሆን የ #አየርላንድ ዲፕሎማት ናቸው።
ቦሬል ካርቱም ውስጥ የተፈፀመው ጥቃት ፤ በሌሎች ሀገራት የሚሰሩ ዲፕሎማቶች ጥበቃን የሚደነግገውን የተመድ ስምምነት የ " ቪይና ኮንቬንሽን " በእጅጉ የጣሰ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ፥ የአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይ ናቢላ ማስራሊ ለAFP በሰጡት ቃል " የሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው " ብለዋል፤ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ቡድን ከካርቱም እንዲወጣ እንዳልተደረገ ተናግረዋል።
ቃል አቀባይዋ ፤ በሱዳን ያለው የፀጥታ እና ደህንነት ሁኔታ እየተገመገመ ነው ብለዋል።
ተመድ በሱዳን ጦር ሠራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ መካከል በቀጠለው ግጭት ከ180 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከ1800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።
አሜሪካ የሱዳኑ ግጭት ባስቸኳይ እንዲቆም ከጀኔራል ቡርሃንና ከጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ጋር ግንኙነት እያደረገች መኾኗን አስታውቃለች።
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ፣ ግጭቱ ሱዳናዊያን ብቻ የሚፈቱት የውስጥ ጉዳይ ነው ሲል ትናንት ማምሻውን አስታውቋል።
ሚንስቴሩ፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደራዊ ጠቅላይ መምሪያውን፣ ቤተ መንግሥቱን፣ የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያንና ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያውን "አማጺ" ሲል ከፈረጀው ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ማስለቀቁን የገለጠ ሲሆን፣ የጀኔራል ደጋሎ ኃይሎች ግን ያስተባብላሉ።
6.2K viewsEl Tigre, edited 05:03