2023-04-08 09:01:09
_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፬__
አንቀጽ 16 ስለ ምጽዋት ይናገራል።
፩) ምጽዋት ከርኅራኄ ወገን የሚሆን ርኅራኄ ነው። ይኽውም ሰው አበድሬ እቀበላለሁ ሳይል በገንዘቡ የሚያደርገው ርኅራኄ ነው።
_
፪) ምጽዋት የማያልፍ የማይጠፋ ሰማያዊ ድልብ ነው። የተቻለውን ያህል በመስጠት ሰው ፈጣሪውን ይመስላል። የጌታ የባሕርይ የሰው የጸጋ ነውና።
_
፫) ምጽዋት ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖራት የብልህ አደራ ናት።
_
፬) ለለመነህ ስጠው። ለሰው የሚያዝኑ የሚራሩ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው። ለእነርሱም ሥላሴ ይራሩላቸዋልና። ጌታ በምጽዋት ለሰው ለሚራሩ ሰዎች ንዑ ኀቤየ ብሎ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባቸዋል።
_
፭) ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ ለተጠሙ፣ ለታረዙ፣ ለእንግዶች፣ ለታመሙ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለታሠሩ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሰደዱ ሊመጸውቱ ይገባል። እንግዳ መቀበል ከምጽዋት ወገን ነው።
_
፮) አሥራቱን፣ በኩራቱን፣ ስለቱን እግዚአብሔርን ለሚያገለግሉ ካህናት ከፋፍለው ይስጧቸው።
_
፯) በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ታገኙ ዘንድ፣ አሥራቱን፣ ስለቱን፣ እጅ መንሻውን፣ መጀመሪያ የደረሰውን እህል (ቀዳምያቱን) ስጡ። በረከት በሚመጸውት ሰው አትጠፋምና።
_
፰) ምጽዋት መጀመሪያ ሃይማኖታችንን አንክድም ብለው ለታሠሩ ሰማዕት ትገባለች። ከዚህ ቀጥሎ ለካህናት፣ ከዚያ ቀጥሎ ለዘመድ፣ ከዚያ ቀጥሎ ለምእመናን፣ ከዚያ ቀጥሎ ላላመኑ ሰዎች ትገባለች።
_
፱) ምጽዋትን ለተቸገረ ሁሉ ሊሰጧት ትገባለች። እግዚአብሔር ለኃጥአንም ለጻድቃንም ዝናምን እንደሚያዘንብ።
_
፲) ተመጽዋቾች ምጽዋቱን ስለ ሰጧቸው ሰዎች መጸለይ ይገባቸዋል። አብዝቶ ይጸልይላቸው።
_
፲፩) ያልተቸገሩ ሰዎች ምጽዋት መቀበል አይገባቸውም። እየተቻለው ምጽዋት የማይሰጥ ሰው እንደ ከሓዲ፣ እንደ ወንበዴ፣ እንደ ሌባ ነው።
_
፲፪) ምጽዋት ከኃጢአት ታነጻለች። ከመቅሠፍትም ታድናለች። ምጽዋት መስጠት እጥፍ ድርብ ዋጋን ያስገኛል።
_
፲፫) ምጽዋትን ከሰጡ በኋላ መጸጸት አይገባም። (ጸጸትን እንዳያመጣ አስቦ መስጠት ይገባል)።
_
፲፬) ምጽዋት የሚሰጥ ሰው በሚሰጠው ሰው ላይ መታበይ የለበትም።
_
፲፭) የሚመጸወተው ገንዘብ ነውር ነቀፋ የሌለበት ይሁን። ይኽም ላለፈው የተሰረቀ የተቀማ፣ ለሚመጣው ውዳሴ ከንቱ ያለበት አይሁን።
_
፲፮) ደስ ብሎት ደስ አሰኝቶ የሚሰጠውን ሰው እግዚአብሔር ይወደዋል።
_
፲፯) ከክፉዎች ምጽዋት ትቀበሉ ዘንድ አትውደዱ። ከእነርሱ ምጽዋትን ከምትቀበሉ በረኀብ ብትሞቱ ይሻላችኋል።
።
__አንቀጽ ፲፯___
ይህ አንቀጽ በምጽዋትና በቤተክርስቲያን ገንዘብ እንዲሁም በመብዓው ስለሚሾሙ ሰዎች ይናገራል
፩) ኤጲስ ቆጶስ በቤተክርስቲያን ገንዘብ ሁሉ ማዘዝ ይገባዋል። ለራሱ የሚሻውን፣ ከካህናት ወገን ለተቸገሩ ሰዎች ማወጣጣት ይገባዋል።
_
፪) ኤጲስ ቆጶስ የቤተክርስቲያንን ገንዘብ ምንም ድሆች ቢሆኑ ለዘመዶቹ መስጠት አይገባውም።
_
፫) የቤተክርስቲያን ገንዘብ፣ ልብስ፣ እርሻ፣ የተክል ቦታ፣ ላም፣ በሬ፣ ፈረስ እግዚአብሔርን በሚፈሩ በታመኑ ሰዎች እጅ ይጠበቅ።
_
፬) የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሸጠ፣ ገዝቶም የያዘ ሰው ይመልሱ። ባይመልሱ በኤጲስ ቆጶሱ እጥፍ አድርገው ይክፈሉ።
_
፭) ከምእመናን አንዱ ገንዘቤን ለቤተክርስቲያን ስጡ ብሎ አዝዞ ቢሞት የቤተክርስቲያኑ ገበዝ ይቀበል። የሚቀበለው ገንዘብ የንጉሥ ግብር ያለበት ከሆነ አይቀበሉት። ቤተክርስቲያን ከነገሥታት ሥልጣን በታች ልትሆን አይገባምና።
_
፮) በቤተክርስቲያን በገቢው ገንዘብ የተሾመው በወጭ ገንዘብ ከተሾመው ይለይ።
_
፯) በየሀገሩ ሁሉ ለታመሙ ለድኆች ለእንግዶች የሚያድሩበት ቤት ይለዩላቸው። እነርሱን ያስተዳድርለት ዘንድ ኤጲስ ቆጶሱ መነኩሴ ይሹም። ለሹሙ ቤት ምግብ ይመቻችለት። የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ቢያንስ ከምእመናን ሁሉ እንደአቅማቸው በየጊዜው ምግብ ይሰብስብላቸው። ስለዚህ ነገር ብዙ ኃጢአት ይሠረያል።
_
፰) አሥራት ሁሉ ለካህናት ሊሆን ይገባል።
_
፱) በሾላ፣ በሽንኩርት፣ በዱባ፣ በቅል እና እነዚህ በሚመስሉ አትክልት ከቤተክርስቲያን አግብተው አይጸልዩባቸው። በጽጌረዳ፣ በወይን፣ በበለስ፣ በሮማን፣ በዘይት፣ በሙዝ፣ በእንኮይ ግን ይጸልዩባቸው።
_
፲) ከመሥዋዕት የተረፈውን ለኤጲስ ቆጶሱ 4 ክፍል፣ ለቀሳውስት 3 ክፍል፣ ለዲያቆናት 2 ክፍል፣ ከዚያ በታች ላሉት እስከ ዲያቆናዊት ድረስ 1፣ 1 ክፍል ይስጧቸው።
።
__አንቀጽ 18
____
ይህ አንቀጽ ስለ አሥራት፣ ስለ በኩራት፣ ስለ ስለት፣ ስለ ጉልት ይናገራል።
፩) አሥራት፣ በኵራት፣ ስለት፣ ጉልት የምጽዋት ወገኖች ናቸው።
_
፪) በኩራት (ቀዳምያት) መጀመሪያ የተቀዳውን ዘይት፣ መጀመሪያ የተቆረጠውን ማር፣ መጀመሪያ የታለበውን ወተት፣ መጀመሪያ የተሸለተውን ጸጉር፣ ጽፈው ደጉሰው መጀመሪያ ያገኙትን ገንዘብ ለቤተክርስቲያን መስጠት ነው። ካህኑ ላመጡት ሰዎች ከመጋረጃ ውጭ ሆኖ እግዚአብሔርን ያመስግነው።
_
፫) ስለት ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ በጎ ነገርን ለማግኘት ሰው በራሱ፣ በልጆቹ፣ በገንዘቡ የተሳለውን ለመፈጸም ከፈጣሪው ጋር የተማማለው መሓላ ነው። የሚሻውን ነገር ባገኘ ጊዜ ስለቱን እንዲፈጽም ሰው ከመሳሉ በፊት በደንብ ያስብ።
_
፬) ይህ ዓለም ኃላፊ ያ ዓለም ኗሪ እንደሆነ አውቆ መሳል በጎ ነገርን ለማግኘት ነው።
_
፭) መከራ ባገኘው ጊዜ ተሳለ እንጂ የተሳለውን ስለት መፈጸም የማይቻለው ድኃ ቢሆን ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ወደ ቄሱ ይሂድ። ቄሱ ወይም ኤጲስ ቆጶሱም የሚችለውን መጠን አይተው ይወስኑለት።
_
፮) ስለትን አለመፈጸም ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍዳን ያመጣብናል።
_
፯) ሴት ልጅ በአባቷ ቤት ሳለ በራሷ ላይ ብትሳል ማለትም ንጽሕ ጠብቄ ሰውነቴን ለእግዚአብሔር ልዩ ገንዘብ አደርገዋለሁ ብላ የተሳለችውን ስለት መፈጸም ይገባታል። አባቷም ስለቷን አያፍርስባት። ስትሳል ሰምቶ ስለቷን ቢያፈርስባት ግን ስለቷ አይጸናላትም። እግዚአብሔርም በዚህ አይመራመራትም። ባል ብታገባ ግን በተሳለችው ስለት ባሏ ሊያዝበት ይገባል። ባሏ ስትሳል ቸል ብሎ ከዚህ በኋላ ቢከለክላት ኃጢአቱ በእርሱ ይሆናል።
2.1K views06:01