2023-04-02 04:45:27
__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፰___
አንቀጽ ፱ የካህናትን ሁሉ ነገር ይናገራል። ካህናት የሚላቸው የሚከተሉት ናቸው።
፩) ሊቀ ጳጳሳት (ፓትርያርክ)
፪) ጳጳስ (መጥሮጶሊስ)
፫) ኤጲስ ቆጶስ
፬) ቆሞስ (ኮሬ ኤጲስ ቆጶስ)
፭) ቀሳውስት
፮) ዲያቆናት
፯) ንፍቀ ዲያቆናት
፰) አናጉንስጢስ
፱) መዘምራን
፲) አፃዌ ኆኅት. ናቸው።
፩) ከተጠመቀ በኋላ የገዘሩትን (የገረዙትን)፣ በግድ ሰዎች የሰለቡትን፣ ባለመድኃኒት በደዌ ምክንያት አባለ ዘሩን መድኃኒት አድርገት የተቆረጠውን ለክህነት በቅተው ከተገኙ ይሾሙ። በፈቃዱ ራሱን የሰለበ ግን አይሾም።
_
፪) ባሮች ጌቶቻቸው ሳይፈቅዱላቸው ከክህነት ሥራ ወገን በማናቸውም አይሾሙ። ጌታው ነጻ ያወጣው ቢሆንና በራሱ ፈቃድ ያድር ዘንድ ነጻ ቢያወጣው ለክህነት የበቃ ቢሆን ይሾም።
_
፫) ምእመን በክርስቶስ ስም አምኖ መከራ ቢቀበል ዲቁና ቅስና ተሹሞ ለማገልገል በአንብሮተ እድ አይሹሙት። አምኖ በሰማዕትነት በተቀበለው መከራ መንፈስቅዱስ አክብሮታልና። መንፈስቅዱስ ሹሞታልና። የክርስቶስን ስም አልክድም ብሎ አምኖ ወደ ዓላውያን ነገሥታት ገብቶ መከራ ባይቀበል፣ እጁን በሰንሰለት እግሩን በእግር ብረት ታሥሮ መከራ ያልተቀበለ ቢሆን ከሰው የተለየ መከራ ባያገኘው ግን በአንብሮተ እድ ይሹሙት። ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾም ቢሆን ግን በአንብሮተ እድ ይሹሙት።
_
፬) ሰው በአካሉ ነውር ስለተገኘበት ከሹመት አይከልከል። አንካሳም ቢሆን፣ አንድ ዓይናም ቢሆን፣ ግራኝም ቢሆን በቅቶ ከተገኘ መቀደስ የሚችል ከሆነ ይሾም።
_
፭) ቤተክርስቲያን ሁላችንንም በጥምቀተ ክርስትና ወልዳናለች።
_
፮) ሁለተኛ ያገባ፣ ሚስት ካገባ በኋላ ገልጦ ወይም ሰውሮ ዕቁባት ያኖረ፣ አግብታ የተፈታችውን ያገባ፣ ዘማዊትን ያገባ፣ ወደዘፈን ቤት የምትሄደውን ያገባ ክህነት አይሾም።
_
፯) አዲስ አማኝ የሃይማኖቱ መረዳት ንጽሕናው እስኪመረመር ድረስ ክህነት አይሾም።
_
፰) አንዱስ እንኳ ለክህነት ይበቃል ብለው ሳይመሰክሩለት አይሾም። ካህናት ከመሾማቸው በፊት ሊቀ ዲያቆኑ አስቀድሞ በንባብ ይፈትናቸው።
_
፱) ለጸሎት ለአገልግሎት እንዳያንሱ በቤተክርስቲያን የሚኖሩ ካህናት ጥቂቶች አይሁኑ። ዳግመኛም ቤተክርስቲያን የምትሰጠው ምግብ እንዳታጣ ካህናት አይብዙ። ምግብ ልብስ መስጠት በሚቻላት መጠን ትሹም እንጂ።
_
፲) ኤጲስ ቆጶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሾመ ነፍስን ሥጋን ከጥፋት ይጠብቅ ዘንድ ነው። ክህነት በክብር ከመንግሥት ትበልጣለች።
_
፲፩) በብሉይ ኪዳን ደቂቀ ሜርያርይ ንዋየ ቅድሳትን ይሸከሙ ነበር፣ ደቂቀ ጌድሶር አዕማደ ደብተራ ኦሪትን ይሸከሙ ነበር፣ ደቂቀ ቀዓት ታቦተ ጽዮንን ይሸከሙ ነበር፣ አልዓዛር ኢታምር መሥዋዕተ ሠክር መሥዋዕተ ነግህ ይሠው ነበር፣ ናዳብ አብዩድ አርደው አወራርደው ያቀርቡ ነበር፣ አሮን ከዓመት አንድ ጊዜ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ይሠዋ ነበር፣ ሙሴ አሮንን ከሾመ በኋላ የክህነት ሥራን አልሠራም።
_
፲፪) ወደ ቤት ስትገቡ "ሰላም ይኵን ለሰብአ ዝንቱ ቤት" በሉ። በረከት የሚገባው ሰው ከዚያ ቢኖር በረከታችሁ ይደርበት። በረከት የሚገባው ሰው ባይገኝ ግን በረከታችሁ ወደእናንተ ይመለስ።
_
፲፫) በከንቱ የሚራገም ሰው ራሱን ብቻ ረገመ። በማይገባ የሚሆን መርገም በማንም በማን አይደርስም። [ቁጥር ፪፻፺፫]።
_
፲፬) (ሐተታ) እየጸለይን ሳለ አንዱ ሊያነጋግረን ቢመጣ አረማዊ ከሆነ ውዳሴ ማርያም እየደገምን ከሆነ የዕለቱን ጨርሰን፣ ዳዊት እየደገም ከሆነ አሥሩን መዝሙር ጨርሰን በአቡነ ዘበሰማያት አሥረን እናነጋግረው። ክርስቲያን ከሆነ የያዝነውን አንቀጽ ጨርሰን በአቡነ ዘበሰማያት አስረን እናነጋግረው። ከዚያ ካረፍንበት መቀጠል ነው። አቋርጠን ከተነጋገርን ግን እንደገና ጀምረን መጸለይ ይገባናል።
_
፲፭) መዓርጋቸውን እንዳያስነቅፉ ካህናት ምጽዋት መቀበል አይገባቸውም። ከቤታቸው ይስጧቸው እንጂ ከአደባባይ ወድቀው አይለምኑ።
_
፲፮) ካህናት ከሠርግ አዳራሽ ሄደው ዘፈን መስማት አይገባቸውም። የሚፈክሩት የሚዘፍኑት ሳይመጡ በልተው ጠጥተው መርቀው ይመለሱ እንጂ።
_
፲፯) ካህን ከሰው ወገን ለአንዱስንኳ አይገዛ። ካህናት የሰው ተገዦች ሊሆኑ አይገባም። ክፉ ሥራ በመሥራት ለሰው አብነት አይሁኑ። ካህን ከሥጋዊ ሹማምንት ለአንዱስንኳ ሹም አይሁን። [ቁጥር ፫፻፯]
_
፲፰) ካህናት ፈጽመው አይነግዱ። እደ ጥበብ ይማሩ እንጂ። ጽፈው ደጉሰው ራሳቸውን ያኖሩ ዘንድ።
_
፲፱) በካህናት የሚፈረደውን ፍርድ ወደ መኳንንት አይውሰዱት። የዚህ ዓለም ነገሥታት መኳንንት በካህናት ላይ አይፈርዱምና። እያንዳንዱ ካህናት በመኳንንት ይፈርዳሉ እንጂ።
_
፳) በኤጲስ ቆጶስ ክፉ ቃል የሚናገር ሰው እነሆ እግዚአብሔርን በደለ።
_
፳፩) ልጄ ሆይ ቃለ እግዚአብሔር ወንጌልን ያስተማረህን ልጅነትን ለማግኘት ምክንያት የሆነኽን እንደ እግዚአብሔር አክብረው።
_
፳፪) ካህናት በጨዋ ዳኛ መዋስ አይገባቸውም። ራሱን የሰለበ ካህን ከሹመቱ ይሻር።
_
፳፫) ገበጣ የሚጫወት ካህንን ተው ይበሉት። ባይተው ከክህነቱ ይሻር። ሕዝባውያንም ካሉ ከምእመናን ይለዩ።
_
፳፬) በአንድ ዓይና፣ በአንካሳ፣ በዕውር የዘበተ ካህን ቢኖር ከምእመናን ይለይ።
_
፳፭) በሐሰት የማለ ካህን ከሹመቱ ይሻር። ሥጋዊ በሽታ ሳይከለክለው ዐቢይ ጾምንና ረቡዕ እና ዓርብን የማይጾም ካህን ከሹመቱ ይሻር።
_
፳፮) የቅስና መዓርግ ከተቀበለ በኋላ ሚስት ያገባ ለሹመቱ ይሻር።
_
፳፯) ቄስ ጠጥቶ ቢሰክር፣ ቢራቆት ከሰው ተለይቶ ሰባት ሱባዔ ይጹም። ከቅስና በታች ባለ መዓርግ በዲቁና እያገለገለ አንድ ዓመት ይኑር። ዲያቆን ቢሆን አምስት ሱባዔ ይጹም። በንፍቀ ዲያቆናት አራት ወር ያኑር።
_
፳፰) ጨዋው ጨዋውን ቢሰድብ እንደ ሕፃን ተቆጥተው ይተውት። ካህን ካህኑን ቢሰድብ ይለይ። ቀኖናውን እስኪፈጸም ድረስ ከምእመናን ይለይ።
_
፳፱) ነገር እያሠራ ዘወትር የሚያጣላ ሰው ቢኖር አንድ ጊዜ ሁልጊዜ ይተው። ዘወትር ነገር መሥራቱን ባይተው ከሹመቱ ይሻር።
_
፴) የወታደር ልብስ የለበሰ ቄስ ቢኖር አራት ወር ከቤተመቅደስ በአፍአ ይቁም። ዲያቆን ቢሆን በአፍኣ ሁለት ወር ይቁም።
2.1K views01:45