2023-04-04 07:30:02
_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፱__
አንቀጽ ፲ ስለ መነኮሳት ይናገራል።
፩) ምንኩስና ወንጌል ያመጣቻት ሕግ ናት። መነኮሳት ምድራውያን መላእክት ናቸው።
_
፪) መነኮሳት ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እየኖሩ፣ ጌታን ስለወደዱ ሰውነታቸውን ሁሉ ሳይቀር የናቁ ናቸው።
_
፫) መነኮሳት ጌታ ፍጹም ልትሆን ከፈለግህ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ተከተለኝ ያለውን ቃል የተገበሩ ናቸው።
_
፬) መነኩሴ የማለውን መሓላ ለመፈጸም የማይነዋወጥ ኅሊና ያለው ሊሆን ይገባል። ከመነነ በኋላ ወደኋላ አይመለስ።
_
፭) ጋኔን ያደረበት ሰው አይመንኩስ። ልጁን፣ ቤተሰቡን፣ አባቱን፣ ሚስቱን ጥሎ የመጣ ሰውን ሳይመረምሩ አያመንኩሱት። ልጆች ወልዶ ያለምግብ የሚተዋቸው ከሆነ አያመንኩሱት። እናት አባቱ የሚረዱ ሆነው ሳለ ትቷቸው የመጣን ሰው አያመንኩሱት። በምን ምክንያት ሊመነኩስ እንደመጣ ይጠይቁት።
_
፮) ሚስቱ የፈቀደችለት፣ ባሏ የፈቀደላት መመንኮስ ይችላሉ። ከምእመናን ለአንዱ ባሪያ ሆኖ ጌታው ሳይፈቅድለት አያመንኩሱት። በአባቱ ፈቃድ የሚኖርን ሕጻን አባቱ ሳይፈቅድለት አያመንኩሱት። ራሱን የቻለ ቢሆን ያመንኩሱት።
_
፯) በድንገት በእጁ ሰው የሞተበት ሰው መመንኮስ ቢፈልግ ያመንኩሱት። ከመነኮሰ በኋላ ባለደሞቹ እንገድላለን ቢሉ እርሱን ለማዳን አበምኔቱም ማኅበሩም ይውጡ። ወዶ አልገደለምና። ይህ አንቀጽ ግዘት የለበትም። አውጥተን እንገድላለን ቢሉ ያልተወገዘበት አንቀጽ ነው።
_
፰) ሰው ከመመንኮሱ በፊት በገንዘቡ ማዘዝ ይችላል። ከመነኮሰ በኋላ ግን ገንዘቡ ሁሉ ለገዳሙ ይሆናል።
_
፱) ደናግላንም ያገቡትም መመንኮስ ይችላሉ። ድንግል ሆነው የመነኮሱት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል የጠበቁ ናቸው። ያላገባ የበለጠ እግዚአብሔርን አገለገለ እንዲል። አግብተው የመነኮሱት ደግሞ ስለእኔ ሚስቱን የተወ የዘለዓለም ሕይወት አለው ያለውን የጌታ ቃል የጠበቁ ናቸው።
_
፲) ምንኩስና የዚህን ዓለም ሹመት ሽልማት መተው ነው። ምንኩስና በገዳም ጸንቶ መኖር ነው። መነኩሴ ማቅ ለብሶ ወገቡን በዝናር (ቅናት) ይታጠቃል። ምንኩስና ሥጋን መብላትንና ወይንን መጠጣትን መተው ነው። ወይን ለመጠጣት የሚያስፈልግ ደዌ ካላገኘው። ምንኩስና ለቁመተ ሥጋ ያህል ምግብን ከፍሎ (ቀንሶ) መመገብ ነው።
_
፲፩) መነኮሳት በገዳም ተሰብስበው እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነው ይኑሩ።
_
፲፪) አበ ምኔት በኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ ይሾማል። ቆሞስ የሆነ ይሾማል። አበ ምኔቱ በሕይወተ ሥጋ ሳለ ከእኔ ቀጥሎ እገሌ ይሾም ብሎ ቢያዝዝ ከዘመዱ ወገን ያይደለ ሃይማኖቱ የጸና ለገዳሙ የሚረባ ምግባር ያለው ከሆነ ይሾም። ይህ አንቀጽ ውግዘት የለበትም። ሌላ የበለጠ አግኝተው ቢሾሙ እዳ የለባቸውም።
_
፲፫) አበ ምኔት በገዳሙ ያደገ፣ ድንግልና ከምንኩስና ያለው፣ መጽሐፍ የተማረ ይሁን። አበምኔት ለመነኮሳቱ እንደ አባት ይሁናቸው።
_
፲፬) መንፈሳውያን አባቶቻችንን ፈጽመን መርዳት ማገልገል ይገባናል። መምህራንም ደቀመዛሙርቶቻቸውን እንደ ልጆቻቸው ሊንከባከቧቸው ይገባል። ከፍጹምነት አድርሳቸው በሃይማኖት አጽናቸው እያሉ ይጸልዩላቸው።
_
፲፭) አበምኔት እግዚአብሔር የሚመሰገንበትን ሥራ ይሥራ (ቁጥር ፫፻፸፫)። ዕረፍት ወዳጅ አይሁን። ወደ ገዳም ከሚመጡ ሰዎች አንዱንስ እንኳ አይናቅ አያቃል።
_
፲፮) የገዳሙን በር የሚጠብቀው ሰው ቃለ ሻካራ ሳይሆን ቃለ ልዝብ ይሁን። ግንባረ ቆጣራ አይሁን። ፈጽሞ ትሁት ይሁን። ሲረግሙት ሲሰድቡት የሚታገሥ ይሁን። በረኛው ከገዳሙ ወጥቶ ይሄድ ዘንድ ለማንም ለማን ሥልጣን አይስጥ።
_
፲፯) መነኮሳት ዘወትር የሚጾሙ የሚጸልዩ ክቡራት መጻሕፍትን የሚመለከቱ ሊሆኑ ይገባል።
_
፲፰)መነኮሳት ሥጋዊ ጌጥ አያጊጡ፣ ሽቱ አይቀቡ።
_
፲፱) በገዳም ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ፈጽመው ሠራተኞች የሆኑ መነኮሳት በአንድ ቀን ሁለት ጊዜ መመገብ ይገባቸዋል። ይኽውም በ፮ ሰዓትና በሠርክ ነው። ሠራተኞች ካልሆኑ ግን በ፱ ሰዓት ወይም በሠርክ አንድ ጊዜ ይብሉ።
_
፳) መነኮሳት ከበዓታቸው ከመሬት ላይ ይተኙ። አበ ምኔቱ እና የታመሙ መነኮሳት ግን ከአልጋ ላይ ሊተኙ ቢወዱ አበምኔቱ ስለክብሩ ታማሚዎች ስለሕመማቸው መተኛት ይገባቸዋል።
_
፳፩) የሹመት ፍቅር ሰይጣን ያለማው ደዌ ነው። ሐዋርያት በይሁዳ ክፋት ከአንድነታቸው አልተለዩም። እንዲሁ መነኮሳት አንዱ ክፉ ቢሆን ከአንድነታቸው አይለዩ።
_
፳፪) እውነተኛ ምንኩስና አስቀድመህ ዓይንህን ክፉ ከማየት ጆሮህን ክፉ ከመስማት ወስነህ ገትተህ ትይዝ ዘንድ ነው። ከዚህ በኋላ ልቡናህን ክፉ ነገር ከማሰብ አንደበትህን ክፉ ነገር ከመናገር ወስነህ ገትተህ መያዝ ነው።
_
፳፫) በሥራው ሁሉ በጎ ብንሠራ እግዚአብሔር ያይልናል ብለን እንዲያይልን አድርገን መሥራት አንድም ክፉ ብንሠራ እግዚአብሔር ያይብናል ብለን እንዳያይበን አድርገን ክፉውን መተው ይገባናል። ፈሪሀ እግዚአብሔር በልቡናችን ጸንታ ትኑር።
_
፳፬) ታመህ ሥጋ ብትበላ ለትሩፋት መሰናክል ይሆንብሃል እንጂ ኃጢአት ተብሎ አይቆጠርብህም።
_
፳፭) መነኩሴ መነኩሴን ቢደበድበው 40 ቀን ከማኅበሩ ይለይ። እርስ በእርስ ከተደባደቡ ሁለቱም 40 ቀን ከማኅበሩ ይለዩ።
_
፳፮) ድንግል ሴት አካለ መጠን ካደረሰች በኋላ ብቻዋን መሄድ አይገባትም። ፀሐይ ከገባ በኋላ ከደጅ ወጥታ ለሰው መታየት አይገባትም [ማንም ይንጠቀኝ ማለት ነውና] ስትናገርም ቃሏን ከፍ ከፍ አድርጋ መናገር አይገባትም።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው
782 views04:30