2023-03-06 19:04:09
ከ760 ሺህ በላይ ሠልጣኞች ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ይገባሉ
**
በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 760 ሺህ 832ቱ ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ገብተው እንደሚሰለጥኑ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የሚሰጠው ሥልጠና ወደ ደረጃ ስምንት ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በትናንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015 ዓ.ም ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ሊገቡ የሚችሉ ሠልጣኞች ቁጥር 760 ሺህ 832 ሲሆን፣ 20 በመቶ የሚሆኑት ከቴክኒክ እና ሙያ ውጪ ባሉ ማሠልጠኛ ተቋማት ይገባሉ።
በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ ቴክኒክ እና ሙያ የሚገቡት ሠልጣኞች ቀጥር 608 ሺህ 666 መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በ2015 ዓ.ም የመቁረጫ ነጥብ የሠልጣኞች ድልድል የኢንዱስትሪውን የሰው ኃይል አሰላለፍ መሠረት በማድረግ የተሰላ በመሆኑ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሥራ ገበያውን፣ የሰው ኃይል ፍላጎት እና የአከባቢውን የልማት ቀጠና መሠረት በማድረግ ቅበላ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
መቁረጫ ነጥቡ የ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን የወሰዱ ተማሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ለ2015 ዓ.ም ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ያነሡት ሚኒስትሯ፣ መቁረጫ ነጥቡን እስካሟሉ ድረስ በመረጡት የሥልጠና መስክ በመንግሥት እና የግል ማሠልጠኛ ተቋማት ላይ መሠልጠን የሚችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በ2013 ዓ.ም እና በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ሥርዓት ያልገቡ ተማሪዎች የሚስተናገዱት በ2014 ዓ.ም በነበረው የመቁረጫ ነጥብ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመደበኛ የሥልጠና ፕሮግራም ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ገብተው መሠልጠን ያልቻሉ ተማሪዎች 11ኛ ክፍል ገብተው መማር አለበለዚያም በአጫጭር ሥልጠና የቴክኒክ እና ሙያ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በተፈጥሮ እና ማኅበራዊ ሳይንስ 12ኛ ክፍል አጠናቅቀው የመቁረጫ ነጥቡን የሚያሟሉ ተማሪዎች በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ውስጥ በሚሰጡ ሁሉም ሙያዎች ላይ እኩል የመወዳደር እና የመሠልጠን መብት እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ ጥራት እና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ታቅዶ በትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲው ላይ በተደረገው ማሻሻያ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የሚሰጠው ሥልጠና ወደ ደረጃ ስምንት ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ ደረጃ አምስት አድቫንስድ ዲፕሎማ፣ ደረጃ ስድስት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ደረጃ ሰባት ማስተርስ እና ደረጃ ስምንት ዶክትሬት (PHD) እኩሌታን የሚይዝ ሲሆን ዘርፉን ተወዳዳሪ እና ተፈላጊ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትን የማዘመን፣ ተደራሽ የማድረግ እና በትኩረት መስክ የማደራጀት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ መግለጻቸውንም ኢፕድ ዘግቧል።
የትምህርት እና ሥልጠና ሥርዓቱን ለሥራ ገበያው በሁሉም ደረጃዎች የሠለጠነ የሠራተኛ ኃይል እና ተስማሚ ቴክኖሎጂ የማቅረብን ተልእኮ ለቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና የተሰጠ ነው ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ተልዕኮውን ውጤታማ ለማድረግ በእውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ ብቁ የሆነ ዜጋ ለማፍራት ከሠልጣኝ ቅበላ እስከ ሥራ ማስተሳሰር ያሉ ሂደቶች ጥንቃቄን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
፨ለጥቆማ
@atc_newsbot
ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@atc_news @atc_news
@atc_news @atc_news
2.5K views16:04