2023-04-28 20:29:30
የአቶ ግርማ የሺጥላ የአስከሬን ሽኝት እሑድ ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከናወን የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በነበሩት በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈጸመው ድንገተኛ ግድያ እንዳሳዘነው በመግለጫው ገልጾ ድርጊቱ የሚወገዝ ነው ብሏል፡፡
የሰኔ 15 የልብ ስብራት ሳይጠገን ሌላ ስብራት መከሰቱ አሳዛኝ ነው ያለው የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ወንድምን በመግደል አሸናፊ መኾን አይቻልም፤ የድል ባለቤትም አያደርግም ነው ያለው፡፡ የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ድርጊቱ የሕዝቡን ባሕል እና ሥነልቦና የማይመጥን እንደኾነም ገልጿል፡፡
የአማራ ሕዝብ በባሕሉ መሪውን ይጠብቃል ይንከባከባል፤ አልመራኝም ብሎ ሲያስብም እንዳይመራው ያደርጋል እንጅ ሰው እንዲሞት አይፈቅድም ነው ያለው የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው፡፡ ድርጊቱ ሀገርንም ክልሉንም እንደሚጎዳ አብራርቷል።
ድርጊቱ ከተሰማ በኃላ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከፍ ባለ ሁኔታ እንዲፈጸም የተለያዩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን አስረድተዋል፡፡
ዋናው ኮሚቴ በክልል ደረጃ መዋቀሩን የገለጸው ኮሚቴው የቀብር ቦታው በወላጆቹ ፍላጎት እና ጥያቄ መሰረት በተወለደበት ሰሜን ሸዋ ዞን ማሀል ሜዳ እንዲኾን ፍላጎት በመኖሩ ሌላ ኮሚቴም እንዲዋቀር መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡
ቀብሩ ወደ ትውልድ ቀየው ከመሄዱ በፊት በአዲስ አበባ የሽኝት ፕሮግራም እንደሚኖር የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው አስረድቷል፡፡
የሽኝት ፕሮግራሙም እሑድ ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም ጠዋት ከ1ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ገልጾ በፕሮግራሙ ላይ ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
9.1K views17:29