2023-03-06 16:43:06
በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከሚሰጠዉ ትኩረት በላይ ለመልሶ ግንባታ የሚሰጠዉ ትኩረት ማየሉ ተገለጸ፡፡
ላለፉት ሁለት አመታት ሲካሄድ የቆየውን የሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በርካታ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን አሁን ላይም በዞኑ ሁለት ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የዋግኽምራ ዞን የአደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ዝናሽ ወርቁ ለአሃዱ ገልጸዋል፡፡
ካሉት ተፈናቃዮች መካከል እናቶችና ህጻናት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ የገለጹት ሃላፊዋ ተፈናቃዮቹ ያሉበትን የችግር ደረጃ ከግምት ያስገባ ትኩረት እየተሰጠ አይደለም ብለዋል፡፡
ዞኑ ለአማራ ክልል አደጋ ስጋት ቢሮ ተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረቡንም ገልጸው ‹‹ለተፈናቃዮች ከሚደረገው ድጋፍ ይልቅ ለተቋማት መልሶ ግንባታ ይበልጥ ትኩረት ሲሰጥ አስተውለናል ፣ ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ በየ 1 ወሩ የሚደረገው የምግብ ድጋፍ የቀጠለ ቢሆንም ለነፍሰ-ጡር እናቶችና ለጨቅላ ህጻናት ተጨማሪ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋል ፣ ነገር ግን እነዚህን ድጋፎች ካለፈው ህዳር ወር በኋላ ያቀረበልን አካል የለም›› ነው ያሉት፡፡
ይህንን በተመለከተ አሃዱ ያነጋገራቸው የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያለው የተፈናቃዮች አሃዝ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ውስንነቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
ሆኖም በተቻለ መጠን እርዳታዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው ፤እርዳታን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ቢቀርቡም ተቋሙ ከዞንና ወረዳዎች ጋር ሳይሆን ከክልል አደጋ ስጋት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ድህረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/ahadutelevision
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቴሌግራም፡- https://t.me/ahadutelevision
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/ahaduradio
ትዊተር፦ https://twitter.com/ahadu_radio?lang=en
አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን #አሐዱ_24
2.2K views13:43