2023-02-16 14:41:46
ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ቢከፈትም አሁንም እየተጉላላን ነው ሲሉ አሽከርካሪዎች ቅሬታ አቀረቡ፡፡
ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ በሚወስደው መንገድ ልዩ ስሙ ጎሃ-ጺዮን የተሰኘው አካባቢ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎችን የሚያዋስን ሲሆን አካባቢውን አልፈው መንገደኞችን ጭነው የሚመጡ አሽከርካሪዎች ግን የነዋሪነት መታወቂያቸው እየታየ እንዳያልፉ መደረጉን በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
ማለፍ ባለመቻላቸው ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ ለ 5 ቀናት ያህል በከፍተኛ እንግልት ውስጥ መቆየታቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹መንገዱ ከማክሰኞ ጀምሮ ተከፍቷል ቢባልም አሁንም እየተጉላላን ነው›› ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል፡፡
ይህንን በተመለከተ አሐዱ ያነጋገራቸው የደጀን ወረዳ የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ጋሻዬ በበኩላቸው የአማራ ክልል መንግስት በተለይም የደጀን ወረዳና አካባቢው አስተዳደር ከኦሮምያ ክልል መንግስት ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ ውይይት መንገዱ ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ክፍት በመደረጉ ምንም አይነት ችግር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንገዱ ክፍት ቢደረግም አሁንም መጉላላት እንዳለ አሽከርካሪዎች እየገለጹ ነውና ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምንድነው በሚል ከአሐዱ ለተነሳላቸው ጥያቄም ‹‹እንደሚባለው አይደለም አሁን ላይ መንገደኞች በሰላማዊ ሁኔታ እያለፉ ነው›› የሚል ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ካለፉት ቀናት የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም አሁንም እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሁሉንም መንገደኛ ማሳለፍ ያልተቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም ነው ያሉት፡፡
አሐዱም የኦሮምያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን በዚህ ዘገባ ላይ ለማካተት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም፡፡
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ድህረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/ahadutelevision
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቴሌግራም፡- https://t.me/ahadutelevision
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/ahaduradio
ትዊተር፦ https://twitter.com/ahadu_radio?lang=en
አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን #አሐዱ_24
2.3K views11:41