2023-03-10 11:37:43
*የተረሳው የእግዚአብሔር ቃል አገልጋይ!*
" እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ። "
(መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3:20)
> ሳሙኤል የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ በነበረበት ዘመን በእግዚአብሔር ቃል የተሞላ እና ለእስራኤል ሁሉ የሰማዩን ምክር የሚያደርስ፣ ከተናገረው ቃል አንዳች የማይወድቅ የእግዚአብሔር ሰው ነበር። በዚህም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው ሕዝቡ ሁሉ ይህን የእግዚአብሔር ሰው ያውቅ ነበር።
> ከምዕራፍ 1 ጀምሮ እስከ ምዕ:3 ከ25 ጊዜ በላይ የተጠራውን እንዲህ ያለውን ሰው፣ በሚያስገርም ሁኔታ ቀጥለው ባሉት ሶስት ተከታታይ ምዕራፎች(4፣ 5፣ 6) ውስጥ ሌላው ቀርቶ ስሙን እንኳ አንዴም አናገኘውም። እነዚህ ምዕራፎች ያያዙት ታሪክ የ20 ዓመታት እንደሆነ ምዕራፍ 7 ይናገራል። እናም ሳሙኤልን ዳግም የምናገኘው ከ20 ዓመታት በኋላ ነው።
" ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ"
(መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 7:2)
#ከዳር እስከ ዳር፣ መላ እስራኤል የእግዚአብሔር ቃል እንዳለበት የሚያውቁትን ሰው እንዴት ረሱት?
> ሰዎቹ ማን ጋር እውነተኛውን ቃል እንደሚያገኙ ያውቃሉ። ነገር ግን ልባቸው ልክ አልነበረም(7÷3)። ሳሙኤል ጋር ቢሄዱ መልሱን ያውቁታል። ታማኙ የእግዚአብሔር ሰው ቀጥታ ቅዱስ ቃሉን ስለሚነግራቸው እርሱን ማናገር አልቻሉም(7÷3-4)።
> ፈረንጆቹ "አንድ ዓይነት ላባዎች አብረው ይበራሉ" እንደሚሉት፣ ሕዝቡ አካሄዱን የማይወቅስበት፣ ሐይማኖተኝነቱ እንዳይቀርበት ደግሞ እግዚአብሔርን የሚጠራለት፣ እንደ አፍኒን እና ፊንሐስ ካሉት ጋር እንዳሻው መሆን ፈልጎ ነበር።
> ስለዚህ ሳሙኤል በዚህ ወቅት አይፈለግም። ምክር አይጠየቅም (5÷3-4)።
#የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው የሚናገር ታማኝ የእግዚአብሔር ነብይ፣ የፈለገውን ያህል ሕዝቡ ቢያከብሩት፣ ቃሉን ግን ለመስማት ፍላጎት ከሌላቸው መካከል ምን ያደርጋል?
#ቃሉ ዝም እንዲል በሚፈለግበት ቦታ የሳሙኤል አፍ ሊከፈት፣ እርሱም እዚያ ሊገኝ አይችልም(ምዕራፍ አራት ላይ ያን የሚያክል ትልቅ አገራዊ ክስተት ወቅት ሳሙኤል የለም)።
> ለእኛ ጥያቄው ይህ ነው፦ ውስጣችን እያወቀው፣ አካሄዳችንን ይወቅሱብናል በማለት ከእግዚአብሔር ሰዎች እንርቃለን? የማይረባውን እንደሚነግሩን የምናውቃቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ከምናጠፋ እና ሳሙኤሎች ዝም ከሚሉን፣ የእግዚአብሔር ቃል የሚነግሩንን ሰምተን ምልልሳችንን ማስተካከሉ አያዋጣምን?
54 viewsJesus-my-Saviour, 08:37