2023-03-17 16:06:02
* የአጭር ጊዜ መንፈሳዊ ህክምና! *
> ወቅቱ ሳኦል በተደጋጋሚ ለእግዚአብሔር ቃል ባለመታዘዙ ምክንያት የእግዚአብሔር መንፈስ ከእርሱ ተወስዶ ለክፉ መንፈስ ተላልፎ የተሰጠበት ነበር፡፡
> ሰውዬው እንደ አንድ ግለሰብ ወይም የቤተሰብ ራስ ብቻ ሳይሆን የአገር መሪ የነበረ እንደመሆኑ ሁኔታ ከባድ ነበር፡፡ ዙሪያው የነበሩ ባሪያዎቹ ነገሮችን ተመልክተው መፍትሔ ፍለጋ ውስጥ መግባታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡
> የነገሩን ምንጭ ተመለከቱና ለሳኦል እንዲህ አሉት
“እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል” (1ሳሙ.16፡15)
> በትክክል ምስቅልቅሉ ከየት እንደመጣ ገብቷቸዋል፤ ሳኦል በእግዚአብሔር ፍርድ ስር መሆኑን ተገንዝበዋል፡፡
#መፍትሔው ምን ይሁን?
> የሳኦል ባሪያዎች ያቀረቡት መፍትሔ በገና ደርዳሪ መፈለግ ነበር፡፡ ይህ በራሱ መልካም ነገር ነው፤ በገና ደርዳሪው የእግዚአብሔርን ቃል በዜማ የሚያንጎራጉር እንደሆነ ጥያቄ የለውም፤ ለዚህ የታጨውም ዳዊት መሆኑን ስናይ፣ የሰዎቹ መፍትሄ በራሱ ጥሩ እና እግዚአብሔር እየተጠቀመበት መሆኑን አመልካች ነው፡፡ ሳዖል በክፉ መንፈስ በሚሰቃይበት ሰዓት ይህ መንገድ ረድቶታል፡፡
“ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር” (2ሳሙ.16፡23)
#አሁን ጥያቄው ይህ መፍትሔ ምን ያህል ያስጉዛል ነው?
> የሳኦል ባሪያዎች ትኩረት ሳኦል ላይ ክፉ መንፈስ በሚመጣበት ሰዓት ላለው ችግር እንጂ ክፉ መንፈስ ሳኦል ላይ መምጣቱ ላይ አይደለም (ቁ.16)፡፡ “ክፉ መንፈሱ መምጣቱ የማይቀር ነው፤ ነገር ግን ሲመጣ ምን ይደረግ” የሚለው ላይ ያነጣጠሩ ይመስላሉ፡፡
#ከዚህ ከፍ የሚል መፍትሔ አለን?
> አዎን! ክፉ መንፈሱን እዳይደርስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ያም ሳኦል ንስዓ እንዲገባና የበደለውን እግዚአብሔርን ይቅር በለኝ ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ ከእግዚአብሔር “ጋር ተስማማ ሰላምም ይኑርህ ይላል” (ኢዮ.22፡21)፡፡
> የሳዖል ባሪያዎች መፍትሔ ጊዜያዊ ችግሮችን ማከም ችሎዋል፤ ለአገርም ጥቅም ነው፡፡ ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ ሳኦልን ከክፉ መንፈስ ነፃ አያወጣውም፤ መጨረሻ ላይ ሕይወቱና አሟሟቱ አስከፊ ነበር፡፡
#ነጥቡ ምንድን ነው?
> በጌታ ኢየሱስ ያላመኑ፣ ክፉ መንፈስ የሚያውካቸው፣ ሰላምን ያጡ ቤተ-ዘመዶች፣ ከዚያ ውጭ ያሉ ብዙ ሰዎች እንድንረዳቸው፣ እንድንጸልይላቸው፣ መዝሙር እንድንከፍትላቸው ወዘተ ይጠይቁናል፤ እኛም እንርዳችሁ እንል ይሆናል፡፡ ያንን ስንናደርግ እግዚአብሔር በጸጋ አሰራሩ አንዳች ነገር እንደሚያደርግ ጥያቄ የለውም፤ ማድረጋችም መልካም ነው፡፡
> ነገር ግን ያ ጊዜያዊ ህክምና ብቻ ነው፤ ዘላቂው መፍትሔ ንስዓ ገብቶ በጌታ ኢየሱስ ማመንና ከዲያብሎስ እስራት ነፃ መውጣት ብቻ ነው፡፡
> ዛሬ ብንጸልይላቸው፣ ነገ ዲያብሎስ መመለሱ አይቀርም፡፡ ኢየሱስን ግን የግል አዳኛቸው አርገው ሲቀበሉ እነርሱ ራሳቸው ክፉ የሚጫወትባቸው ሳይሆኑ፣ ክፉ ለሚጫወትባቸው የእረፍት ሰው ሆነው ይገለጣሉ፡፡
> እናም ምንም አይነት መንፈሳዊ እገዛ ብናደርግላቸው ያለ ኢየሱስ ግን ዘላቂ መፍትሔ እደማያገኙ ቁርጡን መንገር መልካም ነው!
66 viewsJesus-my-Saviour, 13:06