2022-07-04 18:09:43
* እግዚአብሔር ከእኔ ጋር! *
" … በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።"
(ኦሪት ዘፍጥረት 35:3)
> ይህንን ቃል የተናገረው ያዕቆብ መሆኑንን ሳስብ ጥቂት ቆም ብዬ ራሴን እንድጠይቅ ያስገድደኛል። የያዕቆብን መንገድ ማሰላሰል ጀመርኩኝ። "በሄድኩበት መንገድ" እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነበረ ሲል ምን ማለቱ ነው? ያዕቆብ እየተናገረ ያለው ስለየትኛው መንገዱ ነው?
> ያዕቆብ የሚለው ስም በራሱ የሚናገረው ጥሩ አይደለም፤ የሥጋ አካሄዱን የሚያመለክት ነው። ከዘፍ፡25 ጀምሮ ያዕቆብ የሚታወቀው ነገሮችን በራሱ ብልጠት፣ ብልሃት አልፎም ተንኮልና ውሸት ለማግኘት የሚጥር ሰው ሆኖ ነው። የወንድሙን ደካማ ጎን ለራስ ጥቅም ያደረገ፣ አባቱን ያታለለና የዋሸ ይህ ሰው ጭንቅላቱን ከመተማመኑ የተነሳ ድርድር የሚወድ ሰው ነበር።
> ብኵርና የወሰደው፣ ከላባ ጋር 20ዓመት የኖረው፣ ሚስት ሳይቀር ያገባው በድርድር ነው። ሌላው ቀርቶ ዘፍጥ፡28 ላይ እንደምናየው ከእግዚአብሔር ጋር እንኳ ለመደራደር ጥያቄ ሲያቀርብ እናየዋለን። የቤተሰብ ሕይወቱም ብዙ አስደሳች አልነበረም። ከሚስቶቹ ጋር የነበረው የፉክክር ግንኙት እንዲሁም ጣዖት አምልኮ ቤቱ መኖሩ (ዘፍ፡35) አሳዛኝ ታሪኮች ናቸው።
#ስለ ራሱ ሕይወት የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር
" … የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ …"
(ኦሪት ዘፍጥረት 47:9)
#አዎን፣ ያዕቆብ "በሄድኩበት መንገድ" እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነበረ ሲል ምን እያለን ነው? እግዚአብሔር እንዲህ ያለህ ደስ ከማይል፣ የራስ ፈቃድ በነገሰበት፣ የሥጋ አካሄድ ይጓዝ ከነበረው ሰው ጋር ነበርን?
> ዘፍ፡28 ላይ እግዚአብሔር ለያዕቆብ እንዲህ ብሎት ነበር
" እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።"
(ኦሪት ዘፍጥረት 28:15)
#ለካ እግዚአብሔር የጠበቀንና ያልተወን የእኛን ሁኔታ አይቶ ሳይሆን ስለተስፋ ቃሉ የታመነ ስለሆነ ነው። ያዕቆብን እግዚአብሔር የጠበቀው ያዕቆብ ታማኝ ሆኖ ሳይሆን እርሱ ባይታመን እንኳ የታመነ ሆኖ የሚኖር አምላክ ስላለው ነበር (2ጢሞ፡2÷11)። ያዕቆብን ሊያጠፋ የተነሳው ላባ ለዚህ ምስክር ነው
" ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ።"
(ኦሪት ዘፍጥረት 31:29)
> በራሴ ፈቃድ በተጋዝኩባቸው መንገዶች እግዚአብሔርን ማሳዘኔ ያስከፋኛል። አለመታዘዝን በመታዘዝ ተበቅዬ የቤቴል ሕይወትን መኖር መሻቴ ነው። ነገር ግን እስከዛሬ በሄድኩባቸው ብዙ መውደቅና መነሳቶች ባሉበት መንገዶቼ እርሱ ታማኝ ስሆነ ብቻ ጠብቆ ዛሬ ላይ ያደረሰኝን አምላኬን በማሳብ እኔም እንደ ያዕቆብ እንዲህ እላለሁ
" … በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።"
(ኦሪት ዘፍጥረት 35:3)
106 viewsJesus-my-Saviour, 15:09