Get Mystery Box with random crypto!

*የእምነት ጊዜ* '10፤ ኢያሱም ሕዝቡን። እኔ። ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁን | የጸጋ ወንጌል

*የእምነት ጊዜ*

"10፤ ኢያሱም ሕዝቡን። እኔ። ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው።"
(ኢያሱ 6:10፤)

እግዚአብሔር ለኢያሱ ያስተላለፈውን ይህን ትዕዛዝ ሳስብ ለምን እግዚአብሔር የዝምታውን ጊዜ አረዘመው? ብዬ አሰብኩኝ። ምክንያቱም የሚጮሁት አንድ ጊዜ ሲሆን በዝምታ እየዞሩ የሚያሳልፋት ደግሞ ስድስት ቀን ነውና!

ዕብራውያን 11፥30 ይህን ክፍል ሲገልጠው እንዲህ ይላል……

"30፤ የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ።"
(ዕብራ 11:30፤)

ምንአልባት ይህ ክፍል ሳይገባን "የዝምታው ጊዜ ትንሽ አረዘመም?!፤ለእግዚአብሔር ደግሞ የሚሳነው ነገር የለም……ታዲያ ለምን በአንድ ጊዜ ቅጥሩ አልፈረሰም?!" ብለን ይሆናል። ነገር ግን የስድስት የዝምታ ቀናቶች ቅሉ እምነት ሥራዋን እየሠራች ስለነበር ነው። ስለዚህ የሥራዋ ውጤት የኢያሪኮ ቅጥር ዳግም ላይሰራ እስከ ወዲያኛው አሰናበተው!

"20፤ ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ………"
( ኢያሱ 6:20፤)

አንድ ዘማሪ እንዲህ ሲል የተቀኘውን ቅኔ አስታውሳለሁ

*አንተን መጠበቅ ብዙ ትርፍ አለው
ለታገሰ ሰው ጸጋህ ላስቻለው
አንተን ጠብቆ ያፈረ የለም
በዚህ ምድር ቢሆን በወዲያኛው ዓለም
ከቶ አልተገኘም*

ወዳጆቼ ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን አምኖ በትዕግስት ከመጠበቅ ይልቅ በችኮላና በጥድፊያ ድምፃችንን ማሰማት ይቀናናል። ነገር ግን እግዚአብሔርን አምነን በዝምታ ልንጠብቀው ይገባል። አንደበታችን ሳይሆን እምነት ብቻ ሥራዋን እድትሠራ ጊዜ ልንሠጥ ይገባናል። ያን ጊዜ ግዙፉ ተራራ ደልዳላ ሜዳ ይሆናል፤ባሕሩም የብስ ይሆናል፤ቅጥሩም ዳግም ላይሰራ ይወድቃል !

"26፤ በዚያን ጊዜም ኢያሱ። ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኵር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ።"
(ኢያሱ 6:26፤)