2024-05-15 05:01:57
እውነተኛ ሕይወት ሲመዘን!አንድ አሜሪካዊ ነጋዴ በአንዲት የሜክሲኮ የወደብ ከተማ ዳር ቆሞ ሳለ አንዲት ትንሽ ጀልባ አንድ አሳ አጥማጅ ይዛ ወደ ወደቡ ተጠጋች፡፡ በጀልባ ውስጥ አንድ የሜክሲኮ ተወላጅ አሳ አጥማጅ ያጠመዳቸው ቁጥራቸው ከመጠን ያለፈ ትናንሽ አሳዎች አሉ፡፡
አሜሪካዊው ሜክሲኮአዊውን ስለአሳ ማጥመድ ችሎታው ካደነቀው በኋላ አንድን ጥያቄ አቀረበለት፣ “እነዚህን አሳዎች ለማጥመድ ስንት ጊዜ ፈጀብህ?”
“በጣም አጭር ጊዜ” ብሎ መለሰ፣ ሜክሲኮአዊው፡፡
አሜሪካዊው፣ “ይህንን ያህል አሳ በአጭር ጊዜ ማጥመድ ከቻልክ ለምን ቀኑን ሙሉ ውለህ ብዙ አሳ ለማጥመድ አትሞክርም” ብሎ ጠየቀው፡፡
ሜክሲኮአዊው፣ “አሁን በምሰራበት ሁኔታ ለቤተሰቤ በቂ አቅርቦትን ይዤ እገባለሁ” ብሎ መለሰ፡፡
አሜሪካዊው ጥያቄውን በመቀጠል፣ “በቀረህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ?” አለው፡፡
ሜክሲኮአዊው ገበሬ፣ “ጠዋት በቂ እረፍት እወስዳለሁ፣ በቂ አሳ ካጠመድኩ በኋላ ልጆቼ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ከእነሱ ጋር እጫወታለሁ፣ ከዚያም ከባለቤቴ ከማሪያ ጋር ጣፋጭና አጭር የቀን እንቅልፍ እንወስዳለን፣ ከዚያም ወደ ከተማ ወጣ እልና ከጓደኞቼ ጋር ሻይ እየጠጣን ጊታሬን መታ መታ አደርጋለሁ፤ ቀኔ በእነዚህ ሁኔታዎች ሙሉ ነው”፡፡
አሜሪካዊው በመገረምና በማሾፍ፣ “እኔ የታዋቂው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ተመራቂ ነኝ፡፡ ልምከርህ! ከጠዋት እስከማታ አሳ ማጥመድ አለብህ፡፡ ከዚያም ተለቅ ያለ ጀልባ መግዛት ትችላለህ፡፡ ከዚያ በአሳ ጠመዳ የምታሳልፈውን ጊዜህን ትንሽ ጨመር በማድረግ በርካታ ጀልባዎችን ትገዛለህ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብዙ ጀልባዎች ይኖሩሃል፡፡ ከዚያም ዋና አከፋፋይ መሆን ትጀምርና ለአሳ ጠመዳ በምትወስደው ጊዜህ ላይ ጥቂት ጨመር በማድረግ የራስህን ፋብሪካ ትከፍታለህ፡፡ ከዚያም ከዚህች መንደር ትወጣና ወደ ሜክሲኮ ዋና ከተማ ትገባለህ፣ ከዚያ ወደ ሎስ አንጀለስ፣ ቀስ በቀስም የአለም የገበያ ማእከል ወደሆነችው ወደ ኒውዮርክ በመግባት ታላቅ ሰውና ሚሊየነር ትሆናለህ፡፡”
ሜክሲኮአዊው በመገረም፣ “ይህ የምትለው ጉዳይ ስንት ጊዜ ይፈጃል?” አለው፡፡
አሜሪካዊውም፣ “ከ20 እስከ 25 ዓመታት ይፈጃል” አለው፡፡
ሜክሲኮአዊውም መልሶ፣ “ከ25 ዓመታት በኋላ እዚያ ደረጃ ከደረስኩ በኋላስ?” አለው በፍጥነት፡፡
አሜሪካዊው በመሳቅ፣ “ያን ጊዜማ የሚያጓጓ ነገር ውስጥ ትገባለህ፡፡ ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቀህ ይህንን የገነባኸውን ንግድ ለሕዝብ በማቅረብ አክሲዮን ትሸጥና ብዙ ቢልየን ብር በማግኘት እጅግ ባለጠጋ ትሆናለህ፡፡”
አሁንም ሜክሲኮአዊው መልሶ፣ “በቢልየን የሚቆጠር ብር ካገኘሁ በኋላስ” አለው፡፡
“ከዚያማ ጡረታ ትወጣና ወደነበርክበት የባህር ወደብ ከተማ ትመለሳለህ፡፡ አሁን እንደምታደርገው ጠዋት በቂ እረፍት ትወስዳለህ፣ በቂ አሳ ካጠመድ በኋላ ከልጅ ልጆችህ ጋር ትጫወታለህ፣ ከዚያም ከባለቤትህ ከማሪያ ጋር ጣፋጭና አጭር የቀን እንቅልፍ ትወስዳለህ፣ ከዚያም ወደ ከተማ ወጣ ትልና ከጓደኞች ጋር ሻይ እየጠጣህ ጊታርህን መታ መታ ታደርጋለህ”፡፡
ሜክሲኮአዊው ተገረመ፡፡ በሃሳቡ፣ “አሁን የምኖረውን የተረጋጋ የሕይወት ሁኔታ ከ25 ዓመታት ልፋት በኋላ ለማግኘት ምን አስሮጠኝ” ብሎ በማሰብና በአሜሪካዊው ሃሳብ ስቆ መንገዱን ቀጠለ፡፡
1. ራሳችንን መመዘን ያለብን በሕይወት ዘመናችን ውስጥ ባሉት ዓመታት ሳይሆን በዓመታቶቻችን ውስጥ ባለው ጣፋጭ ሕይወት ነው፡፡
2. ስኬታችን መመዘን ያለብን በገነባነው ቤት ግዝፈት ሳይሆን በቤቱ ውስጥ በሚኖረው በፍቅር የተገነባ ቤተሰብ ነው፡፡
3. አቅጣጫችንን መመዘን ያለብን እኛ በነዳነው መኪና አይነት ሳይሆን እኛን በነዳን ራእይ ምንነት ነው፡፡
ስራ፣ ገንዘብ፣ ታዋቂነት፣ ውበት፣ ስልጣን፣ እውቀትና የመሳሰሉት ቁሳቁስ-ነክ ነገሮች ሰላምና ፍቅር የሞላበትን ቤተሰባዊ ሕይወት እንድንኖር ካላደረጉን ከንቱ ናቸው፡፡
https://t.me/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
11.7K views02:01