Get Mystery Box with random crypto!

ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

የሰርጥ አድራሻ: @zephilosophy
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 18.78K
የሰርጥ መግለጫ

"Strong minds discuss ideas, average minds discuss events, weak minds discuss people."
Rinu Ruzvelt

Ratings & Reviews

3.67

3 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

2

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 9

2022-12-05 19:34:14 ግለሰባዊነት

ምንጭ ፦ ከፍስሀ ጋር መወለድ (ኦሾ)
ትርጉም ፦ ዩሐንስ አዳም

ሰዎች የሚኖሩት ግለሰባዊ ባልሆነ ዓይነት ህልውና ውስጥ ነው:: እነርሱ የሚኖሩት እንደ በጎች ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ግለሰባዊነቱ አመፁ ፣ ነፃነቱ ፣ የሚናገር ኢየሱስን ወይም ቡድሐን የመሰለ ሰው እዚያ ሲኖር መጠላቱ ወይም አለመወደዱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ስብስቡ (መንጋው) ይፈራል መሰረታቸው ይነቃነቃል፡፡ ኢየሱስ ትክክል ከሆነ ከዚያም መላው የስብስቡ የህይወት ንድፍ መቀየር ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ብዙ ስራን ይጠይቃል ሰዎች ደግሞ በባርነታቸው ላይ ብዙ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡

የኢየሱስ መገኘት ወይም አሁናዊነት ሰዎችን የኪሣራ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ቡድሐን ባገኛችሁበት ቅፅበት ወደ በጣም አስቀያሚ ኢ-ሰባዓዊ ፍጥረት ዝቅ ትላላችሁ፡፡ ሁሉንም ክብር ታጣላችሁ፤ ኢ-ሰባዓዊ በሆነ መንገድ እንደታያችሁ ይሰማችኋል፡፡ ምጡቆች ከሆናችሁ የቡድሐን መገኘት እንደ ማንሠራሪያነት ትጠቀሙበታላችሁ፡፡ በአላዋቂነት ውስጥ፣ በእንቅልፍ ውስጥ ስትኖሩ እንደነበር የምታዩ ትሆናላችሁ:: እናም የቡድሐ መገኘት እና አሁናዊነት በጨለማው የነፍሣችሁ ሌሊት ውስጥ የብርሃን ጨረር እንደሆነ በመገንዘብ ለቡድሐ ታላቅ ምስጋናን ታቀርባላችሁ።

ዳሩ ያንን ያህል ምጥቀት ግን በጣም እያሰለሰ የሚገኝ ነው፡፡ ሰዎች ግትሮች እና ደደቦች ናቸው:: ወዲያውኑ ነው አፀፋ የሚሰጡት፡፡

ወደ ላይ ከማንሰራራት እና የቡድሐን (የነቃውን ሰው) ጫፍ ፈተና በመውሰድ ፋንታ ዳግም ማሸለብ ይችሉ እና ጣፋጭ ህልሞች ተብዬዋቻቸውን ያልሙ ዘንድ ቡድሐን፣ ኢየሱስን የመሰሉ ሰዎችን ያጠፏቸዋል፡፡

ለዚያ ነው ከእኔ ጋርም በተቃርኖ ውስጥ የሆኑት፡፡ እኔ የሆንኩኝ ረብሻ ዓይነት ነገር ነኝ፡፡ የእኔ መገኘት ችላ ሊባል አይችልም፡፡ አንድም ከእኔ ጋር መሆን አለባችሁ አልያም ደግሞ ከእኔ በተቃርኖ ውስጥ መሆን ይኖርባችኋል፡፡ የአንድን ሰው አሁናዊነት (መገኘት) ችላ ማለት ሣትችሉ ስትቀሩ መምረጥ ይኖርባችኋል፤ ታላቅ ትርምስም በፍጥረታችሁ ውስጥ የሚኖር ይሆናል - ምክንያቱም የትኛውም መምረጥ ቀላል አይደለም፡፡ መምረጥ ማለት ደግሞ መቀየር ማለት ነው::

ለሃምሣ ዓመታት በተወሰነ መንገድ ኖራችኋል እንበል፡- በነዚያ ዓመታት ውስጥ እነዚያ ልምዶች ሰምረዋል፡፡ አሁን በድንገት እኔ እዚህ ሆኜ እውነተኛ ህይወት ብላችሁ ታምኑበት ከነበረው መቃብራችሁ እየጠራኋችሁ ነው:: እኔ እዚህ ስትኖሩላቸው የነበሩት ሁሉንም ነገሮች፣ ሁሉም እሤቶቻችሁን፣ ግብረ - ገባዊነት ተብዬዎቻችሁ፣ ሁሉም ዕውቀቶቻችሁን፣ እየኮነንኩኝ ነው፡፡ በጣም ደፋር ሰዎች፣ በጣም የተመረጡ ሰዎች ብቻ ና፥ቸው በሁኔታው ማንሰራራት የሚችሉት እና ያላቸውን ሁሉንም ነገር ሊታይ ለማይችል ግን ዕምነትን ሊያሣድሩበት ለሚችል ነገር አደጋው ውስጥ ሊከቱ የሚችሉት፡፡ አሁን ይህ ለተራው መንጋ (ህዝብ) አስቸጋሪ ነው፡፡ ተራው መንጋ መወሰን የሚችለው ለታወቀ ነገር ነው፡፡ ኢየሱስ አንድ ያልታወቀ ነገር ነው፤ ቡድሐ ከባሻገሩ ያለ አንድ የሆነ ነገር ነው:: አሁን ጥያቄው አንድም የታወቀውን፣ አስተማማኙን፣ ምቹውን መምረጥ አልያም ይህንን ጅብዱ መምረጥ እና ካርታ ላይ ወዳልሰፈረው፣ ፈፅሞ እርግጠኛ ሊሆኑበት ወደማይችሉት መሆኑ አልያም አለመሆኑ ወደማይታወቅበት አንድ የሆነ ነገር
ውሥጥ ከቡድሐ ጋር መሄድ ይሆናል፡

ምናልባት ቡድሐ ራሱ ተሸውዶ ይሆናል ወይም ደግሞ ቡድሐ አታላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንኛው፣ ያንኛው የሚል ምልዑ የሆነ እርግጠኛ የሆነ ምንም መንገድ የለም፡፡ አንድ ሰው በጥልቅ ማመንታቱ፣ በጥልቅ ግራ መጋባቱ፣ በጥልቅ መንገዳገዱ ከቡድሐ (ከነቃው ሰው) ጋር መሄድ ይኖርበታል፡፡ እስካሁንም ወጣቶች የሆኑቱ ፣ አዕምሯቸው አቧራዎችን ያልሰበሰበው፣ የተደሞ ብቃት ያላቸው፣ የህይወት አክብሮት ስሜት ያላቸው፣ ፍፁም ያልተዘጉ፣ ከህይወት ጋር ያላቸውን ጉዳይ ገና ያልጨረሱ፣ እስካሁንም ድረስ ያልሞቱ ...እነዚህ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው ከእኔ ጋር፣ ከኢየሱስ እና ከቡድሐ ጋር መሄድ የሚችሉት፡፡ ሌሎቹ ከእኔ፣ ከኢየሱስ እና ከቡድሐ ጋር በተቃርኖ ውስጥ ሊሆኑ ግድ ነው::

በተጨማሪም ሌሎች ምክንያቶች አሉ ሰዎች የቡድኖች አባል መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ቡድን አባል መሆን አንድ የሆነ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነኝ የሚል መፅናናትን እና እርካታን ዓይነት ነገር ይሠጣል፡፡

እውነት በመንጋው ተቀባይነት ልታገኝ አትችልም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ መንጋው የሚኖረው በውሸቶች ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ እናም እነርሱ እነዚያ ውሸቶች ውሸቶች እስከማይመስሉ ድረስ ለረዥም ጊዜ ስለኖሩባቸው ውሸቶቹን የምር ያምኑባቸዋል፡፡ ከእነርሱ እምነቶች የተለየ ነገርን ስትናገሩ ግራ ይጋባሉ እናም ማንም ደግሞ ግራ እንዲገባው አይፈልግም፡፡ ውስጣዊ መነጋነግን ፣ ግራ መጋባትን በውስጣችሁ ትፈጥራላችሁ እናም ማንም ደግሞ በጥርጣሬ ውስጥ መሆንን አይፈልግም፡፡ እዚያ ግን ጥርጣሬ አለ፡፡ እውነትን አውቀው በነበር ምንም ፍርሃት አይኖርም ነበር፡፡ እነርሱ እውነትን አያውቁም፡፡ ብቻ ያምናሉ፡፡ በጥልቁ ነፍሣቸው ውስጥ ጥርጣሬ አለ፡፡ ስለዚህ ከእነርሱ በተቃርኖ የሚሄድ አንድ የሆነ በምትናገሩበት ጊዜ ጥርጣሬ ማንሰራራት ይጀምር እና ከላይ ቦታውን መያዝ ይጀምራል፡፡ እናም እነርሱ ደግሞ በጥርጣሬ ውስጥ መሆንን ይፈራሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው እርግጠኝነትን ይፈልጋል፡፡ ለምን? ምክንያቱም እርግጠኝነት በራስ መተማመንን ይሠጣችኋል፡፡ ጥርጣሬ እንድትንቀጠቀጡ ያደርጋችኋል፡፡

እናም እኔ ደግሞ ብዙ ጥርጣሬን በውስጣችሁ እየፈጠርኩኝ ነው - ምክንያቱም በራዕዬ ውስጥ ጥርጣሬ ውሸት የሆኑ እርግጠኝነቶቻችሁን ካላወደው በስተቀር እውነተኛውን እርግጠኝነት የመቀዳጀቱ ዕድል አይኖርም፡፡ እውነተኛው እርግጠኝነት ከዕምነት አይመነጭም፡፡ እርግጠኝነት የሚመጣው ከልምድ ነው ፤እርግጠኝነት የሚመነጨው በራሣችሁ ማወቅ ነው::

@Zephilosophy
@Zephilosophy
932 views16:34
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-02 04:36:21 ስልጣን የሌለው አንድም ሰው
የለም!

ምንጭ ፦ ህያውነት ፫ (ኦሾ)
ትርጉም ፦ ሀብታሙ ተስፋዬ
               ተስፋሁን ምትኩ

ስልጣን እንደሚያባልግ በሎርድ አክተን የተነገረውን ዝነኛ አባባል ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ አባባሉ እውነት አይደለም፡፡ በተወሰነ መልኩ ሰውየው የታዘቡት ነገር ትክክል ቢሆንም እውነት አይደለም። ስልጣን በፍፁም ማንንም ሰው አያባልግም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሎርድ አክተን ትክክል ናቸው - ምክንያቱም ሁልጊዜም ሰዎች በስልጣን ሲባልጉ እናያለን፡፡ ስልጣን እንዴት ሰዎችን ሊያባልግ ይችላል?

በሌላ መልኩ ካየነው እንዲያውም የባለጉ ሰዎች ስልጣንን ማግኘት ይሻሉ፡፡ በእርግጥ ስልጣን በሌላቸው ጊዜ ብልግናቸውን በይፋ መግለፅ አይችሉም፡፡ ስልጣን ካላቸው ግን ነፃ ናቸው፡፡ የዚያን ጊዜ ከስልጣናቸው ጋር ስለሚንቀሳቀሱ አይጨነቁም፡፡ የዚያን ጊዜ እውነተኛ ማንነታቸው ፀሃይ ይሞቃል፤ እውነተኛ ገፅታቸውንም ያሳያሉ፡፡

ስልጣን በፍፁም ማንንም ሰው አያባልግም፡፡ ነገር ግን ባለጌ ሰዎች ወደ ስልጣን ይሳባሉ፡፡ እናም ስልጣን ሲኖራቸው ስልጣናቸውን በእርግጥም ፍላጐቶቻቸውን እና ጥልቅ ስሜቶቻቸውን ለማሟላት ይጠቀሙበታል፡፡

የዚህ አይነቱ ነገር ያለ ነው፡፡ አንድ ሰው በጣም ትሁት ሊሆን ይችላል የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት ሲፈልግ በጣም ትሁት ሊሆን ይችላል ታውቁትም ይሆናል - በመላው የህይወት ዘመኑ በጣም ጥሩና ትሁት ሰው እንደነበር ታውቁ ይሆናል፤ እናም ትመርጡታላችሁ፡፡ ስልጣን የያዘ ጊዜ ግን ለውጥ ይኖራል፤ ከዚያ በኋላ የድሮው አይነት ሰው አይደለም፡፡ በዚህ ለውጥ ሰዎች በጣም ይገረማሉ- እንዴት ስልጣን ያባልጋል?

በእርግጥ የሰውየው ትህትና የውሽት፣ የማሳሳቻ ነበር፡፡ ትሁት የነበረው ደካማ ስለነበረ ነው፤ ትሁት የነበረው ስልጣን ስላልነበረው ነው፤ በሌሎች ሀይለኛ ስዎች እንዳይደፈጠጥ ስጋት ስለነበረበት ነው ትሁት የነበረው፡፡ ትህትናው የፖለቲካ መሳሪያው ፖሊሲው ነበር። አሁን ግን መስጋት አያስፈልገውም፤ አሁን ማንም ሊደፈጥጠው ስለማይችል መፍራት አያስፈልገውም፡፡ ስለሆነም አሁን ወደ እውነተኛ ተፈጥሮው መምጣት አለበት፣ አሁን እውነተኛውን የገዛ ራሱን ማንነት መግለፅ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የባለገ መስሎ ይታያል።

በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ስልጣናቸውን በአግባቡ መጠቀም ይቸግራቸዋል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣናቸውን አላግባብ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ናቸው ስልጣን ላይ ዝንባሌ የሚያድርባቸው፡፡ ትንሽ ስልጣን ካላችሁ እራሳችሁን ታዘቡ፡፡ አሁን መንገድ ዳር የምትቆሙ ተራ ደንብ አስከባሪዎች ልትሆኑ ትችላላችሁ። ነገር ግን አጋጣሚውን ካገኛችሁ ስልጣናችሁን አላግባብ ትጠቀሙበታላችሁ፤ ማንነታችሁን ታሳያላችሁ፡፡

ሙሳ ናስረዲን ደንብ አስከባሪ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ እናም አንዲትን ሴት መኪና እየነዳች አያለ ይይዛታል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ሴትና መኪና በፍፁም አብረው አይሄዱም የሚል ሀሳብ ነበረ፡፡ ሴትየዋም ታዲያ ስህተት ፈፅማ ነበር፡፡ ሙላ ማስታወሻ ደብተሩን አወጣና መፃፍ ሲጀምር፣ ሴቲቱ «ቆይ! ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስለማውቃቸው አትጨነቅ» አለችው፡፡ ሙላ ግን መፃፉን ቀጠለ፡፡ ምንም አይነት ከበሬታ አላሳያትም፡፡ «ሀገረ ገዢውንም ጭምር እንደማውቃቸው ታውቃለህ ወይ?» አለችው ሴቲቱ፡፡ ሙላ ግን አሁንም መፃፉን ቀጠለ፡፡

«ስማ ምን እያደረግህ ነው? ፕሬዝዳንቱንም እኮ አውቃቸዋስሁ!» አለችው ሴትየዋ፡፡

በዚህ ጊዜ ሙላ «የኔ እመቤት ትሰሚያለሽ? ሙላ ናስረዲንንስ ታውቂዋለሽ?» ብሎ ጠየቃት፡፡

‹‹ኧረ በፍፁም ስለ እሱ ሰምቼ አላውቅም፡፡»

«አንግዲያውስ ሙላ ናስረዲንን ካላወቅሽ ችግር ላይ ነሽ፡፡»

ስልጣን ሲኖራችሁ ... ነገሮች ቀላል አይሆኑም - አይደለም እንዴ? ዙሪያ ገባውን መታዘብ ትችላላችሁ፡፡ በአንድ የባቡር ጣቢያ ትኬት መሸጫ መስኮት ፊት ለፊት ቆማችሁ ሳለ፣ ትኬት ቆራጩ አንድ የሆነ ነገር ማድረጉን ይቀጥላል
ምንም የሚሰራው ነገር እንደሌለ
ብታውቁም፣ እሱ ግን ወረቀት ከወዲያ ወዲህ ማገላበጥ ይይዛል፡፡ ሊያዘገያችሁ ይፈልጋል፤ አሁን ስልጣን እንዳለው ሊያሳያችሁ ይፈልጋል፡፡ «ቆይ!» ይላችኋል፡፡ እናንተን እምቢ ለማለት ይህን
አጋጣሚ መጠቀም አለበት፡፡

ይህንን ነገር በገዛ ራሳችሁ ውስጥም አስተውሉት፡፡ ልጃችሁ ይመጣና «አባዬ ውጪ ወጥቼ ከነ አቡሽ ጋር ኳስ መጫወት «እችላለሁ ወይ?» ብሎ ይጠይቃል፡፡ «አይሆንም!› ትሉታላችሁ፡፡ ልጃችሁም ሆነ እናንተ የኋላ፣ ኋላ እንደምትፈቅዱለት ታውቃላችሁ፡፡ ከዚያ ልጁ መበጥበጥ፣ መዝለል፣ መጮህ ይጀምራል፡፡ «ሄጄ መጫወት እፈልጋለሁ» እያለ ይነተርካችኋል፡፡ በመጨረሻ «እሺ በቃ ሂድ» ትሉታላችሁ፡፡ ይህንን አስቀድማችሁ በደንብ ታውቁታላችሁ፤ ከዚህ በፊት የዚህ አይነቱ ነገር አጋጥሟችኋል፡፡ ደግሞም ውጪ ወጥቶ ኳስ መጫወት ችግር እንደሌለበት ታውቃላችሁ፡፡ ታዲያ ለምን እምቢ ትሉታላችሁ?

ስልጣን ካላችሁ ስልጣናችሁን ለማሳየት ትፈልጋላችሁ፡፡ ልጃችሁም የራሱ ስልጣን ስላለው መዝለል ይጀምራል፤ ሁከት ይፈጥራል ምክንያቱም ረብሻ እንደሚፈጥር እና ጐረቤቶቻችሁም ሰምተው በመጥፎ ሁኔታ እናንተን ሊያዩዋችሁ እንደማትፈልጉ ያውቃል፡፡ ስለዚህ <እሺ> ትሉታላችሁ፡፡

በሁሉም የሰው ልጅ ገጠመኝ ውስጥ ይሄ ነገር በተደጋጋሚ ሲፈጠር ታያላችሁ ሰዎች በየቦታው ስልጣናቸውን እያሳዩ ነው፤ ሰዎችን ያበሻቅጣሉ፣ ወይም በሌሎች ይበሻቀጣሉ፡፡ አንድ ሰው ካበሻቀጣችሁ እናንተም ወዲያውኑ የሆነ ቦታ ላይ የደረሰባችሁን በደል ለመበቀል ደካማ ሰዎችን ታገኙና በተራችሁ ታበሻቅጣላችሁ::

በመስሪያ ቤታችሁ ውስጥ አለቃችሁ ካበሻቀጣችሁ ቤታችሁ መጥታችሁ ሚስታችሁን ታበሻቅጣላችሁ፤ ሚስታችሁም የሴቶች መብት ታጋይ ካልሆነች ልጇ ከትምህርት ቤት እስኪመጣ ድረስ ጠብቃ ታበሻቅጠዋለች፡፡ ልጇም ቢሆን ዘመናዊ ከሆነ፣ አሜሪካዊ ከሆነ መኝታ ክፍሉ ይሄድና መጫወቻዎቹን ይሰባብራል ምክንያቱም እሱ ማበሻቀጥ የሚችለው መጫወቻዎቹን ብቻ ነው፡፡ እሱም ስልጣኑን መጫወቻዎች ላይ መግለፅ ይችላል፡፡ ሁኔታው በዚህ መልኩ ይቀጥላል። እንግዲህ ጨዋታው ይህንን ይመስላል፡፡ እውነተኛው ፖለቲካም ይኸው ነው...

ደግሞም ሁሉም ሰው ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ስልጣን አለው᎓᎓ ስልጣን የሌለው አንድም ሰው አታገኙም፤ እስከ መጨረሻው ድረስ ብትሄዱ ስልጣን የሌለው ሰው ማግኘት አትችሉም፡፡ አንድ ሰው አንድ የሆነ ስልጣን ይኖረዋል፤ ቢያንስ ውሻውን በእርግጫ ነርቶ ስልጣኑን ይገልፃል፡፡ ሁሉም ሰው አንድ የሆነ ቦታ ላይ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ፖለቲካ ውስጥ ይኖራል፡፡ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አትሆኑ ይሆናል፤ ይሄ ማለት ግን ፖለቲካዊ አይደላችሁም እንደማለት ተደርጉ አይታይም፡፡ ስልጣናችሁን በአግባቡ ካልተጠቀማችሁ ፖለቲከኞች ናችሁ፡፡ ስልጣናችሁን በአግባቡ የምትጠቀሙ ከሆናችሁ ግን ፖለቲከኛ አይደላችሁም፡፡

ስልጣናችሁን አላግባብ አለመጠቀማችሁን እወቁ፡፡ ይህን ከተገነዘባችሁ ይህንን በማድረጋችሁ አዲስ ብርሃን ታያላችሁ፤ እንዴት እንደምትንቀሳቀሱም ታያላችሁ - የዚያኔ በጣም እርጋታ የተላበሳችሁ እና አስተዋዮች ትሆናላችሁ፡፡ የአእምሮ ሰላምና ፀጥታን ታገኛላችሁ።

@Zephilosophy
@Zephilosophy
1.4K views01:36
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-30 07:05:17
707 views04:05
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-29 07:53:31 ኑሮና ጣዕም

ሙያዬን ታውቃለህ፣ ማጀቴን ታያለህ፤
“እንጀራሽ እንክርዳድ፣ገበታሽ ጣዕም አልባ!”
ለምን ትለኛለህ?

በል ዝም ብለህ ብላ!!
ቸርቻሪ መንግስታት፣
ሰነፍ ገበሬዎች፣
በዝባዥ ነጋዴዎች፣ በበዙባት ዓለም፤
ጠንካራ ጥርስ እንጂ ቀማሽ ምላስ የለም!

በረከት በላይነህ
@Zephilosophy
966 viewsedited  04:53
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-28 20:08:42 የነቃ ሲመክር

ውዶቼ!
ተነሱ! ተነሱ! ተነሱ!
በጠያቂ አቅም ነው የሚሰራው መልሱ፡፡

ከኮከቦች ርቀት፣
ከባህሮች ስፋት፣
ከአውሎ ንፋስ ጉልበት የተጠነሰሰ፤
የመገለጥ ወይን ከልቤ ፈሰሰ።
ከከፍታዎቼ፣ ከአደባባዮቼ ወስዶ ላይመልሰኝ፤
ከነፍሴ ተማክሮ ክንፌ ቀሰቀሰኝ።

ሰረገላው አይቆም፣ ነጂውም አይተኛ፤
ጥያቄም፣ ይቅርታም፣
ፀፀትም፣ ትዝብትም - ይልካል ወደእኛ፤
“ተጓዦቼን ሁሉ ምንድን አስተኛቸው?
እኔ መቆም አላውቅ -
           ወይኔ ረበሽኳቸው!” ይላል።

ዕረፍት የማያውቀው - ፈጣን ሰረገላ፣
መንቃት በማያውቁ- ተጓዦች ሲሞላ፤
የመገለጥ ወይን በአፍጢሙ ተደፋ፤
“ወራጅ አለ!” የሚል ተሳፋሪ ጠፋ።


ውዶቼ!
ተነሱ! ተነሱ! ተነሱ!
ግለጡ፣ ኀስሱ፣
ከጥያቄ ጅረት በጥራት ፍሰሱ፤
ሰፊ ጊዜ ስጡ ክንፍ ከነፍስያ እንዲወሳወሱ።
ጎዳናው፣ ሸለቆው፣
ጋራው፣ ሸንተረሩ - አዲስ ፊት እንዲያዩ፤
“ወራጅ አለ!” በሉ በየአደባባዩ።

ምንጭ -የመንፈስ ከፍታ
ደራሲ-ሩሚ
በረከት በላይነህ እንደተረጎመው!!

@Zephilosophy
@Zephilosophy
1.0K viewsedited  17:08
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-22 19:17:33 ያልተረዳነው!!

"... ሰው ሲታመም የምንጠይቀው ከቋጠሮ ሰሐን ጋር ነው... ሰው ሲታሰር ' እግዚአብሔር ያውጣህ ' የምንለው ከፍትፍት አገልግል ጋር ነው ....አራስ የምትጠይቀው ከፔርሙዝ አጥሚት ጋር ነው ... የክርስትና አባታችን ለፋሲካ አክፋዩን የሚጠብቀው ድፎ ዳቦ እና አረቄ ነው ...እዝንተኛ የምናስተዛዝነው ሰባት እንጀራ ከአንድ ሰሐን ወጥ ጋር ነው ...ሟችን የምንሸኘው ከገንቦ ጠላና ከለምለም እንጀራ ጋር ነው ...የቅዱሳንና የመልአክታት ተራዳኢነት የሚጎበኘን በስማቸው ከዘከርን ነው... ስዕለታችን በሬ ወይም በግ ነው ... ሰርጋችን፣ ልደታችን፣ እርቃችን፣ ሹመታችን፣ አምልኳችን፣ የሚበላ ነገርን ሙጥኝ ያሉ ናቸው ...

....ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ተምሮ ሲመረቅ ይዘን የምንሄደለት ስጦታ ብዕር ወይንም መጽሐፍ አይደለም ፤ ኬክ ፣ ብርቱካን ፣ ሙዝ ...ነው ። በሽተኛ ስትጠይቅ ከብርቱካንና ከሙዝ ይልቅ መጽሐፍ መውሰድ እንደማላገጥ ይቆጠራል። ጊዜውን ይገፋበት ዘንድ መጽሐፍ ማበርከት በሽተኛው እንዳይድን ከመመኘት እኩል ነው።

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን መጻሕፍት ከባዶ ገበታችን በስተዚያ የተቀመጡ ትርፍ ነገሮች ናቸው ። መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ገበታችን ሞልቶ ከገነፈለ በኋላ ነው ብለን በይነናል። ገበታችንም አይሞላ ፤ መጻሕፍቱም አይነሱም። ያልተረዳነው ቢኖር ለገበታ መትረፍረፍ ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ መጻሕፍት አቋራጭ መንገድ መሆናቸውን ነው።

እንዴት ታዲያ ማንበብ መብላትን ይቅደም ? መቼ ይሆን ከምንኮራባቸው ባህሎቻችን በላይ ማንበብ ባህላችን ሆኖ የምንታወቅበት ና የምንኮራበት?......''

(ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ)

@Zephilosophy
@Zephilosophy
1.1K viewsedited  16:17
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 22:59:43 ...... ካለፈው የቀጠለ

"ናርሲዝም".......3

ፀሐፊዋ ‹‹ሂክማንበኢየሩሳሌም›› (Eichmann in Jerusalem) በማለት ይኸን የናዚ ወንጀለኛ ስትገልፀው ‹‹ግለሰቡ በወህኒ ቤት ህይወቱ እንኳን ለአንድም ቀን በፈፀመው ድርጊት የመፀፀት ነገር አለማሳየት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም እሱን ዘወትር የሚያስጨንቀውና የሚቆጨው የሆድ ድርቀት ሕመሙ እንጂ ሌላ አልነበረም››:: ሂክማን በራሱ ነገር ብቻ የተዋጠና የታዘዘውን በመፈፀም ታማኝነቱን በማሳየት ብቻ የሚደሰት ወታደር ነበር:: ‹‹ሂክማን አይሁድን የሚጠላ ሰው አልነበረም፣ ነገር ግን ይኸ ደግሞ በራሱ የሰውዬውን የባህርይ ማንነት የባሰ የከፋ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም በሰው ልጅ ዘንድ መልካምም ይሁን በጎ ነገርን የማመዛዘንን ስሜት ከማጣትስ በላይ ምን የከፋ ነገር ይኖራል?›› ትላለች አና::

ለሂክማን ከእሱ ትዕዛዝ ባሻገር፣ ከራሱ ደህንነት በላይ፣ እንዲሁም ከሥራና ኃላፊነቱ በቀር ሌላው ነገር ሁሉ ዋጋ ቢስ ነበር:: በአረን አገላለፅ ‹‹እንዲህ አይነት የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ የተላበሱ ሰዎች ክፉና ጨካኝ ብለን ከምንጠራቸው ሰዎች የላቀ ጥፋትና ክፋት የምናገኝባቸው በመሆናቸው ከምድር ሊወገዱ ይገባል::››

የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ድርጊት የከፋ ሆኖ የሚታሰበን ደግሞ ምግባራቸው በራስ መውደድና ፍቅር የተያዘ ከመሆኑ ላይ ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑም ድርጊታቸውን አውቀውና አምነውበት የመፈፀማቸውም ነገር ነው:: በተለይም እንዲህ ዓይነቱ ስለሌላው ግድ የለሽ የመሆንና ያለማሰብ ነገር ከራስ ዘር፣ ባህልና እምነት ውጪ የሆነውን ሰው ዝቅ አድርጎና አሳንሶ ከመመልከት የሚመነጭ መሆኑ ነው:: ይህ ደግሞ የ‹‹ናርሲዝም››ን ባህርይ ወደከፋ ደረጃ የሚያደርሰው ይሆናል::

የስነ-ልቦና ሊቁ ኤርክ ፍሮም ይህንኑ የናርሲዝም ሦስተኛ ደረጃ የሆነውን ግዴለሽነትን ሲገልጠው፡- ‹‹የግድየለሽነት መገለጫው ከራስ ዘርና ባህል ወይም ከመሰል ውጭ የሚገኘውን ሰው እንደ ዕቃ መቁጠር ነው›› ይላል::

በመጨረሻና አራተኛ ደረጃ ላይ የምናገኘው የ<<ናርሲዝም›› ባህርይ መገለጫ ደግሞ ‹<የታነቀ (የታግተ) ዕድገት›› (Arrest- ed development) መታየቱ ነው:: ማንኛውም ሰው በሞራል ላይ የተመሰረተ ምግባርን ከቤተሰቡመ ከማሕበረሰቡ፣ ከትምህርት ቤት ከንባብ...ወዘተ እያሳደገውና ራሱንም እየለወጠበት የሚመጣ ሲሆን የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ የተላበሰ ግን ምግባርን አስመልክቶ በዙሪያው የሚያልፍባቸውን ልምምዶች ሁሉ ከራሱ ፍላጎትና ደስታ ውጭ መመንዘር አይሻም:: የሰው ልጅ ከአንድ የዕድሜ ክልል ወደ ሌላው ሲሻገር አስተሳሰቡ ምክንያታዊ እየሆነ፣ በሕግና በኃላፊነት እየተገዛ ለሌሎች መብትና ፍላጎትም ርኅራኄ እየተሰማው የመሄዱ ነገር የሰውነቱ አንድ የምግባር መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ ነገር ግን የ‹‹ናርሲዝም›› ባሀርይ እነዚህን የዕድገት ደረጃዎች የማያልፍባቸውና በራስ ፍላጎትና ስሜት ብቻ ተይዞ የቆመ (የታሰረ) ነው::

በዚህ ደረጃ የሚገኘውን የናርሲዝምን ባህሪይ በጥሩ ሁኔታ እንዳስቀመጠው የሚታመንለት ኒኮሎ ማኪያቬሊ ‹‹The Prince›› ውስጥ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአንድ ገዢ የመጀመሪያ ሃሳቡ ሊሆን የሚገባው ሥልጣኑን በሚገባ መያዙና ይኸንኑ ሥልጣኑንም ሊደሰትበት መቻሉ ነው:: ይኸን ግብ ለመጨበጥ ደግሞ ገዢ የሆነ ሰው ማንኛውንም ድርጊት ለመፈፀም ፈቃደኛ መሆን አለበት::›› ይኸ ምን ማለት ይሆን?

ስለሌላው የማሰብና ለሌላው የመኖርን ነገር ማስቀደም እንደሚገባ የምግባር አስተሳሰብ ቢያስቀምጥም የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ ግን የሥልጣንንም ሆነ የኃላፊነትን ግብ በራሱ የፍላጎት ደረጃ የሚገታ ነው፡፡ ከሌሎች ጥቅምና ፍላጎትም ይልቅ የግል ጥቅምና ፍላጎትን በሥልጣን ላይ የመቆየት ምክንያት የሚያደርግ ነው:: ለዚህም ይመስላል ማኪያቬሊ ‹‹ናርሲስት ማለት በምርጫውና በባህርዩ ከራሱ ጥላ ነጻ መውጣት ያልቻለና የማይፈልግ ሰው ነው›› በማለት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የሚገልፀው:: የእኛም የናርሲዝም ጉዞ ማሰሪያችን የሚሆነው፡-በራሱ ጥላ ሥር የሚኖር ሰው የሌላው ብርሃን አይታየውም›› የሚለው ይሆናል::

@Zephilosophy
@Zephilosophy
872 viewsedited  19:59
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 22:45:55 ...ካለፈው የቀጠለ

"ናርሲዝም".......2

የስነ-አእምሮ ሊቃውንቱ ደግሞ ‹‹ናርሲዝም›› በየሰው ልጅ ባህርይ ውስጥ የሚገኝና ዋነኛ መገለጫው ደግሞ ‹‹ለራስ የሚሰጥን ከፍተኛ የተፈላጊነት ስሜት (self importance) እንዲሁም ራስን ከሌላው ሰው በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የተለየ (unique) አድርጎ የማመን አስተሳሰብ ነው›› ይላሉ:: በተለይም ‹‹ናርሲዝም›› በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጥባቸው ሰዎች የራሳቸውን መንገድ ብቻ መሄድን (መከተልን) የሚሹና ክብርና ሀብትንም አጥብቀው የሚፈልጉ ናቸው:: እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ታዲያ ከሌላው ሰው ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ የተበላሸና ብዙ ርቀትም የማይጓዝ ነው:: ለሌሎች የሚያሳዩት ምግባርም ሆነ ርኅራኄ ከሞራላዊ አስተሳሰብ የሚፈልቅና የሚመነጭ ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎትና ግብ በመጨበጥ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ይሆናል:: ለዚህም ነው ምግባር በሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚኖራት ሰፊ ስፍራ ሲፈተሸ የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይን በወጉ ማየትና መመርመር ተገቢ የሚሆነው፡፡ የናርሲዝም ባህሪያት መገለጫዎች እንደሚከተለው ሰፍረውልን ስናገኝ እያንዳንዱ የሰው ልጅ የራሱን ምግባር ከዚህ አንጻር ሊፈትሽ እንደሚገባም ሊቃውንቱ ይነግሩናል::

የ‹‹ናርሲዝም›› ባህሪይ የተላበሰ ሰው በዋነኛነት ቀጣዩን ባህሪያት በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ኑሮው ውስጥ ያንፀባርቃል፡- በራሱ ነገር የተዋጠ ነው፤ የራሱን ዋጋ ከሌሎች አልቆ ወይም በማጋነን ዘወትር ይናገራል፤ ለሌሎች ርኅራኄን አያሳይም፤ ከሌሎች ይልቅ ራሱን ለሕይወት ከፍታ የተገባ አድርጎ ይቆጥራል፤ ዘወትር የሌሎችን አትኩሮት ይሻል፤ ትችትን (ሂስ) አይቀበልም፤ መደነቅ ይወዳል፤ ከሌሎች ልዩ እንክብካቤ ዘወትር ይፈልጋል፤ ፈጣሪን መቆጣጠር (የፍላጎቱ ፈፃሚ አድርጎ መቁጠር) ይሻል፤ የትኛውም ሕግና ደንብ እሱን እንደሚመለከት አያስብም፤ ሌሎችን መሸንገል ይወዳል፤ እንዲሁም ለሚደረግለት መልካም ነገር ምስጋናን አያውቅም::

ምንም እንኳን የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ የተላበሰ ሰው ከላይ የተዘረዘሩት ዋነኛ መገለጫዎቹ ተደርገው ይወሰዱ እንጂ በአንፃሩ የሰው ልጅ በምድር ለመኖር የቻለው እነዚህን ባህርያት በመያዙ ነው የሚሉ ተከራካሪዎች ደግሞ አልታጡም:: ለምሳሌ የስነ-ልቦና ሊቅ የሆነው ሮበርት ራይት ሲናገር፡- ‹‹የሠው ልጅ ሞራላዊ እንሰሳ ነው የምንልበት ምክንያት እኮ ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማሰቡና ተፈጥሮንም በዚሁ ችሎታው በነቃ ፍተሻ ሊረዳት በመቻሉ ነው›› ይላል፡፡ ለራይት የሰው ልጅ አእምሮ በሦስት የተከፈለ ሲሆን ማሰብና ቋንቋን ከመናገር አእምሮአዊ ብቃት ባሻገር እንደሰው ዘር በቀጣይነት ረዥም ዘመን በምድር ለመኖር (ሳንጠፋ) ያስቻለን የተለያየ አስተሳሰብ መያዛችን መሆኑ ደግሞ መዘንጋት የለበትም:: በቀላል አገላለፅ በምድር ላይ ለመኖር ቀዳሚው ነገር የራስን ፍላጎትና ስሜት መፈፀም ነው፤ ይኽ ደግሞ የመኖር ጥበብ ይባላል:: ለዚህም ነው ራይት ‹‹ናርሲዝም›› የሰው ልጅ ብቻ ባህርይ ሳይሆን በማንኛውም እንሰሳ ውስጥ የሚገኝ ‹<የመኖር ትግል›› ተደርጎ መወሰድ ያለበት የሚለን::

እንደአለመታደል ሆኖ ግን ይኸ የሰው ልጅ የመኖር ትግል በውስጡ ከመኖር ፍላጎት አልፎ በመሄድ የራስን ደስታና ክብር ብቻ ወደመሻት ደረጃ ላይ መድረሱን መመልከት አለብን ይላሉ የላይኛው አስተሳሰብ ተቃዋሚ ሊቃውንት፡፡ ሊቃውንቱ ‹‹የሰው ልጅ የደስታና ፍላጎቱ መገለጫ ከዓለም በሚቀበለው ላይ የተወሰነ እስከሆነ ድረስ በራሱ ከመያዝና ራሱንም ከማገልገል በቀር የሚያስበው ሌላ ነገር ሊኖር አይችልም:: ናርሲስቶች ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ ሳይሆን በእነሱ ዙሪያ የምትሽከረከር አድርገው ማሰብን የሚመርጡትም ለዚህ ነው::

የታሪክ ምሁሩ ክርስቶፈር ላች ዝናን ባተረፈለት ‹‹The culture of narcissism›› በተሰኘ መፅሐፉ የዛሬው የአሜሪካ ትውልድ የተያዘበትን የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ ሲገልፀው፡- ‹ለራስ ብቻ እንጂ ለዘመኑ ተጋሪዎች ወይም ለተከታዩ ትውልድ የማያስብ፤ የወላጅ፤ የጎረቤትና የዜጋን ማኅበራዊ ሚና የዘነጋ (የጣለ) ሲሆን የዚህም ምክንያቱ የራሱን ደስታና ክብር አጥብቆ የሚሻ ከመሆኑ በመነጨ ነው›› ይለዋል::

እንግዲህ ናርሲዝም›› የራስን ጥላ ብቻ የመከተልና ለሌላው ማሰብን የነፈገ አስተሳሰብ የመሆኑ ነገር በሊቃውንቱ ዘንድ ሚዛን የደፋ ሆኖ በምናገኝበት በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነቱን ባህርይ የተላበሰ ሰው ከዚህ ማንነቱ አገኘዋለሁ ወይም እጨብጠዋለሁ ብሎ የሚያምንበትስ ጉዳይ ምን ይሆን? ብለን ስንጠይቅ አራት አውነታዎችን መምዘዝ እንችላለን::
የመጀመሪያው የናርሲስቶች መሻት የተንጠለጠለው ‹‹ቅፅበታዊ ደስታን›› (They desire instant gratification) ከማግኘት ላይ ነው:: የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ የተላበሰ ሰው ያለፈው ዘመንም ሆነ መጪው ጊዜ አያሳስበውም:: ያለፈው ዘመን አልፏል፣ ለዛሬው ማንነት የሚያበረክተውም አንዳች ፋይዳ የለም:: የዛሬ ድርጊቱም ቢሆን ለነገ የሚያስቀምጠው ስንቅ ወይም የሚጠብቀው ዘር አይደለም:: በአጭሩ ማንኛውም ድርጊቱ አሁንና በቅፅበት የሚያስገኝለትን ደስታና የሚሰጠውንም ትርፍ ብቻ በማስላት የተጠመደ ነው:: ምንም እንኳን እውነታ (reality) የሚባለው አሁን (now) የተከናወነ ነገር ቢሆንም ከትናንት የመጣና ወደነገ ደግሞ የሚወስደን መሆኑን ግን አይቀበሉትም:: እናም ናርሲስቶች ዛሬንና አሁንን መኖር ብቻ ሳይሆኑ ምርኮኛውም ናቸው::

በሁለተኛ ደረጃ የናርሲዝም ባህርይ የተላበሱ ሰዎች ‹‹የሞራል ምናብ ይጎድላቸዋል›› (They lack moral imagination)። ናርሲዝም የራስን ፍላጎት፤ መሻትና ስሜት ከመፈፀም ወይም ለመፈፀም ከመትጋት ባሻገር ድርጊታቸው በሌላው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ወይም ያልተጠበቀ ውጤት የሚመለከቱበት ምናብ የላቸውም:: ይኸ በተራ አገላለፅ ሲቀመጥ ከሌላው የሰው ልጅ ጋር በሚኖራቸው ማኅበራዊ ግንኙነት ዋነኛ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት የራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም ብቻ ነው:: ሞራላዊ ምናብ (moral imagination) ይኖር ዘንድ ርኅራኄ የግድ ያስፈልገናል:: ለዚህም ነው እንደፓትሪሺያ ዌርሀን አይነቶቹ የዘመናችን ፈላስፎች አባባል ሞራላዊ አስተሳሰብም ሆነ ምግባር ዛሬ ከሰው ልጅ ዘንድ እንዲጠፋ ያስገደደው ምክንያት ይኸው ከራስ ጥላ ተላቅቆ በሌላው ሕይወት ውስጥ ራስን የመመልከት ነገር መጥፋቱ ነው:: ሌላው የሰው ልጅ ከእኛ እኩል የመኖር ፣ ፍላጎቱን የመጨበጥ፣ ደስታውን የመሸመት፣ እንዲሁም ግዴታውን የመፈፀም እምነት በውስጣችን ሊኖር የግድ ነውና:: ምግባርም ከዚህ የተለየ ሞራላዊ መገለጫ አይኖራትም::

በሦስተኛ ደረጃ የ‹‹ናርሲዝም›› ባህርይ መገለጫ ሆኖ የምናገኘው ደግሞ ‹‹ግዴለሽነትና ልማድ›› ነው:: አንዳንድ ጊዜ ‹‹ናርሲዝም›› ራስን መውደድና ማፍቀር ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የሚናገሩት አሳባውያኑ በተለይም ‹‹ስለሌላው ደህንነት ግድ የለሽ መሆንና አለማሰብም እንዲሁ መገለጫው ነው›› ይላሉ:: ለዚህ እንደማሳያ የሚጠቀሰው በ1963 እ.ኤ.አ አና አረን በፃፈችውና የናዚ መሪዎችን የፍርድ ሂደት በዘገበችበት መፅሀፏ ሚሊየን አይሁዶችን በካምኘ እያጎረ የፈጀውን አዶልፍ ሂክማን የገለፀችበት አባባል ነው።

           ይቀጥላል

@Zephilosophy
@Zephilosophy
797 viewsedited  19:45
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-19 22:09:32 ‹‹በራሱ ጥላ ስር የሚኖር ሰው የሌላው ብርሃን አይታየውም››

"ናርሲዝም"...........1

ምንጭ ፦ ተዓምራትና ጣኦታት
ፀሀፊ ፦ ሀይለጊዮርጊስ ማሞ (ጲላጦስ)

በምግባር ዙሪያ ካሉ ፍልስፍናዎች መካከል ‹‹ናርሲዝምን›› (Narcissism) የምንመለከት ይሆናል:: ምናልባትም የሞራልን ነገር አንስተን ይኸን የሰው ልጅ ባህርይ አንዱና አስቸጋሪው መገለጫ የሆነውን ‹‹ናርሲዝምን›› ሳንመረምር ብናልፍ ትልቅ ስህተት ይሆናል:: እንግዲህ በምግባር ዙሪያ ሰፊ ምርምርና ሃሳቦችን ያራመዱ በርካታ አሳብያንና ፈላስፎች እንዲሁም ምሁራን ዋነኛ ቁምነገር አድርገው የያዙት “የሰውን ልጅ ከራሱ ጥላ ነፃ የማውጣት” ጉዳይ ነው:: በሌላ አገላለፅ ይህ ጥላ በራስ ፍላጎትና ስሜት ተውጠንና በተፈጥሮአዊው ግፊት ተወስደን ከሌሎች ጋር ከሚኖረን ግንኙነት የተነሳ የሚወድቅብን ተፅዕኖ ሆኖ ይገለፃል::

የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንሰሳ የመሆኑ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ ይኸ ማኅበራዊ ሕይወቱ ግን ዘወትር በሌሎች ፍላጎትና ለራሳችን ባለን ፍቅር መካከል የሚጎተት ጭንቀት ነው:: ስለሌሎች ግድ ይለን ዘንድ የድርጊታችን መመዘኛና መስፈሪያ ከእኔነት ስሜት ተላቆ ተፈጥሮአዊ መልካምነትን ወይም ርኅራኄን (Empathy) መላበሱ የግድ ይሆናል:: ነገር ግን ተፈጥሮም ብትሆን የሰውን ልጅ ምግባር ከራስ ፍቅር ባሻገር በሌላ መመዘኛ ለመመልከት አስቸጋሪ አድርጋዋለች:: መልካም ምግባር ማለት ግን በብዙዎቹ ዘንድ የሚታመንበትን አብዛኛውን ድርጊት ‹‹መልካም›› ብሎ መቀበል አይመስለንም:: ምክንያቱም አብዛኛው ሰው የድርጊቱ ትክክለኛነት መመዘኛ አድርጎ በቅድሚያ የሚያሰላው ከራሱ ፍላጎትና ስሜት እንዲሁም እምነት ጋር የመቆራኘቱና በዚያም የሚያገኘውን ሥጋዊም ይሁን መንፈሳዊ ጥቅም ነው:: ይኸ ደግሞ መገለጫው ‹‹ናርሲዝም›› (ከራስ ጋር በፍቅር መውደቅና በራስ ጥላ መመራት) ይባላል:: ናርሲዝም በአጭሩ ሲቀመጥም ‹‹እኔ፣ለእኔ እና በእኔ›› ይሆናል::

በግሪክ አፈታሪክ ‹‹ናርሲሰስ›› በተለያየ መንገድ ሲተርክ የኖረ ቢሆንም ተረኪዎቹ በመጨረሻ የሚደርሱበት ሞራላዊ መልዕክት ግን አንድና ተመሳሳይ ነው:- ‹‹በራስ ወዳድነት መጠመድ››፡፡

ናርሲሰስ ከህፃንነቱ ጀምሮ እጅግ የተዋበና ቆንጆ ሲሆን ከዚህም የተነሣ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም በፍቅሩ የሚወድቁለትና ከእሱ ጋር ጊዜያቸውን ለማሳለፍ አጥብቀው የሚሹና የሚደክሙ ነበሩ:: ሴት መንፈስ (Nymph) የነበረችው ኤኮ (echo) እንኳን በናርሲሰስ ፍቅር ተይዛ ስንትከራተት በተራሮችና አለቶች መካከል ጠፍታ ዛሬ በሌሎች ሰዎች ድምፅ ውስጥ ብቻ የምታስተጋባ ‹‹የገደል ማሚቶ›› ሆና ቀርታለች:: ‹‹ናርሲሰስ›› ከራሱ በቀር ለማንም ፍቅር ደንታ የሌለውና በራሱ ፍቅር የተያዘ ከመሆኑ የተነሣ የትኛውንም የፍቅር ጥያቄ አይቀበልም ነበር:: ይልቁኑም የእሱ ደስታ የሆነው ሄሊኮን በተሰኘው ተራራ ሥር የረጋ ውሃ (ኩሬ) ወደሚገኝበት ሥፍራ በመሄድ፤ በውሃው የራሱን መልክ እየተመለከተ በደስታ መሞላት ነበር::

በራሱ መልክና ቁንጅና ያበደው ናርሲሰስ ከዚያ ውሃ አጠገብ መለየትም ሆነ መራቅ አልተቻለውም:: ዕለት ዕለት፣ በየሠዓቱና በየደቂቃው ከዚያ ውሃ አጠገብ ቆሞ ቁልቁል የሚመለከተውን የራሱን ፊት እየተመለከተ በከፍተኛ ደስታ ይሞላ ነበር:: ናርሲሰስ በራሱ ውበት ተሸንፎ ፍቅር የተያዘ ከመሆኑ የተነሣ ምግብ ለመመገብም ሆነ ውሃ ለመጠጣት ትዝ የማይለውና ስለየትኛውም ሰው የፍቅር ጥያቄና ጭንቀት ግድ የማይሰጠው ነበር::

ናርሲሰስ በግሪክ አፈታሪክ ሰፍሮ የምናገኝበትን መንገድ ቀንጭበን መመልከቱ ምን ያህል በራሱ ፍቅር የተያዘ ብቻ ሳይሆን ያበደም እንደነበር ማረጋገጫ ይሆናል::

ናርሲሰስ የራሱን መልክ ነፀብራቅ በውሃው ውስጥ እየተመለከተ ‹‹ለምን አንተ እጅግ የተዋብክ ፍጡር ዝም ትለኛለህ? እርግጥ ነው የእኔ መልክ የአንተን ውበት ማሸነፍ አይችልም፤ ሴት መናፍስት ሳይቀሩ በፍቅሬ ወድቀዋል፤ አንተ ግን በእኔ ውስጥ የተለየ መስለህ አትታይም:: እጆቼን ወደአንተ ስዘረጋ አንተም እንዲሁ ታደርጋለህ፤ በፈገግታህ ዘወትር ትመለከተኛለህ፤ ድርጊቴንም በተመሳሳይ ድርጊት ትመልሳለህ:: እባክህን ከእኔ አትለይ፤ እኔም እንከባከብሀለሁ:: ቢያንስ በእጆቼ መንካት የማልችለውን ውበትህን በአይኖቼ እየጎበኘሁ ልደሰትበት::››

‹‹ናርሲሰስ›› ለአፍታም ከውሃው ዳር መለየት አልሆነለትም:: ይሁንና በፍቅር የወደቀለትና በውሃው ውስጥ የሚመለከው ውበት ደግሞ ምላሽ የሚሰጠው (እንደእሱ ፍላጎት) አልሆነም:: እናም ከፍተኛ ሀዘን ወደቀበት:: እንዲህም አለ፡- ‹‹እነሆ! አሁን አወቅሁ፤ ሌሎች በእኔ ፍቅር እንዴት ይሰቃዩ እንደነበር የተረዳሁት አኔ በአንተ ፍቅር ሥር ወድቄ ራሴን ስመለከተው ነው›› አለው::

ናርሲሰስ ሐዘንና ለቅሶው የቱንም ያህል ከንቱና ምንም የማያተርፍለት ቢሆን እንኳን የተሸነፈበት የራሱ ፍቅር ከፍተኛ ነበርና ሊቋቋመው ከማይችለው በላይ ሆነ:: በመጨረሻም ራሱን ስቶ ከውሃው ዳር ወደቀ:: ታሪኩ የሚያበቃው አማልክቱ ሳይቀሩ ለ‹‹ናርሲሰስ›› ሲያዝኑና ገላውን ወደአዲስ ዓይነትና እጅግ የሚያምር አበባ ሲቀይሩት ነው:: ይኸ በውሃ ዳር የበቀለው እጅግ የተዋበ አበባ ታዲያ እስከዛሬ ድረስ ‹‹ናርሲሰስ›› ተብሎ ይጠራል::

እንግዲህ የሰው ልጅ በራሱ ፍቅር የወደቀና የተያዘ ይኸም ተፈጥሮአዊ መገለጫው አድርገው የሚመለከቱት አሳብያንና ምሁራን ይኸን ባህርይውን የሚገልፁበት ቃል ‹‹ናርሲዝም›› ሆኖ እንደቀጠለ እንረዳለን::

ሰው የቱንም ያህል ሞራላዊ ፍጡርና ለሌላው ግድ የሚለው ወይም ርኅራኄን የሚያሳይ ቢሆን እንኳን ከራሱ በላይ የሚያፈቅረውም ሆነ የሚያስብለት መሰል ፍጡር ግን ሊኖር አይችልም:: ከዚህ አንጻር አንዳንድ አሳብያን በብዙዎች የሚታመንበትንና ከራስ አስበልጦ ልጅን የማፍቀርን ባህርይ እንኳን መመልከት የሚገባን ከደመ ነፍሳዊ ስሜት ጋር በተያያዘ እንጂ ከሞራላዊ አስተሳሰብ ጋር በተገናኘ ሊሆን አይገባም ይላሉ:: የቱንም ያህል መልካም ነገራችን የሚደርሰው ፍጡር (ልጅንም ጨምሮ) ከራስ ደስታና ስሜት ጋር በተገናኘ መሆኑን ከተቀበልን የድርጊታችን ምንጩ ዞሮ ዞሮ ከራስ ፍላጎትና ስሜት ላይ የሚወድቅ ይሆናል:: እናም ‹‹ናርሲዝም›› ደረጃው የቱንም ያህል የተለያየ ይሁን እንጂ በሰዎች ሞራላዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሰፊውን ሥፍራ ይዞ እንደሚገኝ መካድ አይቻልም::

ታላቁ የስነ-ልቦና ሊቅ ሲግመን ፍሮይድ በሥራው ውስጥ አልፎ አልፎ ይኸንኑ ‹‹ናርሲዝም›› የተጠቀመበት ሲሆን በቀጥተኛ ትርጓሙም ‹‹በራስ መወሰድ (መስመጥ)›› አድርጎ ይወስደው ነበር:: ይሁንና በሌላ ሥፍራ ደግሞ ለፍሮይድ ‹‹ናርሲዝም›› ማለት የስነ- አእምሮ መረበሽ አንዱ ደረጃና አልፎም የአእምሮአዊ መናጋት (mind disorder) መገለጫ ነው:: ለምሳሌ አንድ ሰው የራሱን ገላ የወሲብ ስሜት እርካታ ማግኛ አድርጎ የሚጠቀምበት ከሆነ ወይም ደግሞ ሰው ከአንድ የዕድሜ ክልል ወደቀጣዩ (ለምሳሌ ከልጅነት ወደ ወጣትነት) ሲሸጋገር ራስን የመውደድ ወይም የተፈላጊነት ስሜት የሚያድርበት ከሆነ የዚሁ የ‹‹ናርሲዝም›› መገለጫ ተድርጎ ይወሰዳል::

               ይቀጥላል

@Zephilosophy
@Zephilosophy
1.1K views19:09
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-11-12 19:40:36 የመንፈስ ነፃነት
ከኦሾ ድንቅ መፅሀፍ ከሆነው ከፓንታጃሊ የዮጋ ጥበብ  የተወሰደ

@Zephilosophy
@Zephilosophy
1.5K viewsedited  16:40
ክፈት / አስተያየት ይስጡ