2022-10-14 22:18:08
.... ካለፈው የቀጠለ
የፆታ ፍልስፍና ......3
ይሄንን አተያይ ለመቀንጠስ ይላሉ እነዚህ አሳቢያን <ለሴቶችም ልክ እንደ ወንዶች ሁሉ ዕድልን መስጠት ያስፈልጋል። ሴቶቹ አይችሉም ብሎ ከመከልከል ይልቅ ወንዶች በሚሰለፉበት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ ተቋም ውስጥ ሴቶችም ተመሳሳይ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ችግሩን ይፈታዋል። ይህን ማድረግ ከተቻለ እንደ ፕሌቶና አርስቶትል
ያሉት ፈላስፎች ያስቀመጧቸው <<ሁሉም ሴቶች የማይለወጥ የማይናወጥ የዝቅተኝነት እጣ ፈንታ አለባቸው›› የሚለውን ደምሳሽ ዕይታ መቀየር
ይቻላል ይላሉ።
የሃይማኖት፣ የማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ተቋማትን በማደስ (Reform) ትውልዱ በአመለካከቱ የተሻለ ግራ ቀኙን ማገናዘብ የሚችል ሴትን ከወንድ እኩል መመልከት የሚችል ማድረግ ይቻላል የሚለው የአሳቢያኑ ዕይታ ነው። “ስቱዋርት ሚል” እና “ዊልስቶን ክራፍት” ይሄንን ለማለት ያስቻላቸው “ሴቶች የበታች ናቸው።” የሚለው አመለካከት “ተፈጥሯዊ ያልሆነ ሰው ሠራሽና በመፈጠር የመጣ ሳይሆን በመፍጠር የመጣ ነው” ከሚል መነሻ ነው። በእነዚህ ሰዎች ዕይታ ነባሩን ማኅበረ-ፖለቲካዊ መዋቅር እንደገና ማደራጀት በራሱ ለሴት ጨቋኝ የሆነውን እሳቤ ከሥር ለመመንገል ያስችላል።
“Vindication of the rights for women” በሚለው ዝነኛ መጽሐፏ ዊልስቶን ክራፍት እንዲህ ትላለች፤ “ሴቶች በተፈጥሯቸው ሆደ ቡቡ ደካማ፣ አልቃሻ፣ ስሜታዊ እና እኑስ ሆነው አልተፈጠሩም። ይልቁንም በማኅበረሰቡ እንዲህ እንዲሆኑ ተደርገው ይሠራሉ እንጂ.. ሴቶች በተፈጥሮ ከተፈጠሩት በላይ ማኅበረሰቡ እንዲሆኑ ወደ ሚመኝላቸው ደካማነት እንዲጓዙ የሚደረግባቸው ጫና ይበዛል።”
በዊልስቶን ክራፍት እሳቤ ሴቶችን ልፍስፍስ፣ አልቃሻና ጥገኛ አድርጎ የሠራቸው መፈጠር (Nature) ሳይሆን ማኅበረሰቡ (Nurture) ነው። የእዚህ ሁሉ መሠረት ደግሞ አሁን ያለው የትምህርት ሥርዓት ነው” ትላለች። በየሀገሪቱ ያለውን የተንሸዋረረ የትምህርት ሥርዓት ስትተችም እንዲህ ትላለች። .... “Like the flowers which are planted in too rich a soil, strength and usefulness are sacrificed to beauty –(1792:7)
እንዲህም ትላለች ክራፍት ... “በዚህ የተነሣ ሴቶች አመክንዮ የመጠቀም ብልሃታቸውን ለማዳበር እንዳይችሉ ተደርገዋል። ትምህርቱም የሰውን ልጅ ወደ ፍጽምና የሚወስድ መሆኑ ቀርቶ ሰዎች ኑሯቸውን ብቻ እንዲኖሩ የሚያስተምር ሆነ።”
ሰዎች የሚኖሩት ኑሮ ደግሞ የሴት እና የወንድን ዕጣ ፈንታ ቀድሞ የበየነ ነው። እየተሰጠ ያለው ትምህርት ሴቶች እንዴት ሰጥ ቀጥ ለጥ ብለው መኖር እንዳለባቸው (አንገትን ደፍቶ መኖርን) ሲያስተምር ወንዶች ደግሞ እንዴት አለቃ፣ አዛዥና ጉልበተኛ መሆን እንዳለባቸው የሚያስተምር ሆኗል።
ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በአካል ጠንካራ እና ሁሉን ቻይ ተደርገው ስለተሠሩ ሴቶችን እንደ ጥቅም የለሽ ወይም እንደ መገልገያ ቁስ ለመጠቀም ምክንያት መሆን የለበትም።
በሌላ በኩል “ስቱዋርት ሚል” ተፈጥሮ (Nature) የሚለውን እሳቤ አምርሮ ይቃወማል። “the subjection of women” በሚለው ሥራው ውስጥ «በሚኖረን የዕለት ከዕለት ግብብነትና ቅርርብ እየተገነዘብናት እንሄዳለን እንጂ፣ የትኛዋንም ሴት ቢሆን ስለተፈጥሮዋና አንደኛዋ ፤ ስለአንደኛዋ ስላላት ልዩነት ልናውቅ አንችልም። በመሆኑም በተለምዶ ወይም ቀድሞ ባለው ፍልስፍና ውስጥ የሴቶች ተፈጥሮ እየተባለ የሚወራው ነገር ውኃ የማይቋጥር ተልካሻ ሙግት ነው” ይላል። ይሄ ተልካሻ ሙግት የወንዶችን የበላይነት ለማስረጽ ከማሰብ የዘለለም አይደለም ይላል ስቱዋርት ሚል
አባታዊ የሆነው የእዚህ ዓለም አተያይ “ወንዶች በተፈጥሮ አገኙት። የሚባለውን ነገር ሴቶች እንዳላገኙት (እንደማያገኙት) ያስመስላል። ይሄ አባዊ (Androcentric) ሥርዓት በሴቶቹ ላይ የራሱን ፍላጎት እና መላምት ከጫነ በኋላ ይሄ የሴቶች ተፈጥሮ ነው ብሉ ይደመድማል።
በመሆኑም ከዚህ ዓይነቱ የቅጥፈት አተያይ ለመውጣት ወንዶችና ሴቶች ማንነታቸውን የሚያጎለብቱባቸው መንገዶች ለሁሉም የሰው ልጅ (ለሁሉም ፆታ) በእኩል ሊሰጡ ይገባል። ወንዶች ብቻ የሚችሉት እየተባለ ሴቶች ሊከለከሉ የሚችሉበት መንገድ መዘጋት አለበት።
አሁን አክራሪ የሆነውን ምላሽ እንመልከት። ከላይ የተመለከትናቸው ሁለትቶ ፈላስፋዎች ዕይታቸው ለዘብተኛ ነው፤ “ተቋማዊ አሠራርን በማስተካከል ዓለም ስለ ሴቶች ያለውን የተንሸዋረረ ዕይታ ማስታረቅ ይችላል» የሚል ሐሳብ ያላቸው ናቸው። ፈረንሳያዊቷ ኢግዚስቴንሻሊስት "ሲሞን ዲቦቨር” ደግሞ የቀደመውን ፍልስፍና ከመሠረቱ ትንደዋለች።
ፕሌቶ እና አርስቶትል “ነገሮችን ነገር የሚያደርግ የራሳቸው የሆነ የማይለወጥ የማይናወጥ ማንነት (Essence) ሥሪት ናቸው።” በማለት የሞገቱበትን ፍልስፍና ውድቅ ታደርጋለች - “ኢሰንስ” የሚባል ነገር “ኢሴንሻሊዝም” የሚባል ፍልስፍና አይረባም ስትል።
የዲቦቨር መከራከሪያ የነገሩ መገለጫ ከሆነው “ኢሰንስ” ይልቅ የነገሩ ኅልውና (Existence) ይቀድማል። የአንድ ነገር ዕጣ ፈንታውን ለመወሰን መገለጫው ምንነቱ ላይ ሳይሆን መኖር አለመኖር (ጎልዮው) ላይ ነው ማነጣጠር ያለብን” ትላለች። የዲቦቮር ፍልስፍና (Existentialism) በእዚህ የተነሣ ዕጣ ፈንታ ላይ ሳይሆን ነጻነት ላይ ያተኩራል።
“ስለሆነም መገለጫዎችን እያነሡ የሴቶች ዕጣፈንታ ከማለት ይልቅ ሴቶች በራሳቸው ኅልዮአዊ መሆናቸውን ተቀብሎ ፈቃድ እንዳላቸው ማመኑ ነው ትክክለኛ መንገድ” -ትላለች ዲቦቮር።
The second sex”” በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፏ “የትኛው አካላዊ፣ ሥነ-ልቡናዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ እውነታ ሴቶች በተፈጥሮ ያላቸውን ምንነት ሊወስን አይችልም” ትላለች። “one is not born, but rather, become a woman” (1976፡267) “ሴታዊነት” ወይም «የሴት” ተብለው የተለዩ ሁሉ ለሴቶች እየተሰጡ ያሉ መገለጫዎች
ናቸው።
ይሄ “የሴት” እየተባለ የሚሰጥ መገለጫ ደግሞ ሴቶችን “ሌሎች” እንዲሰኙ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ወንድነት እንደ አንደኛ ደረጃ ፆታ ሴትነት እንደ ሁለተኛ ደረጃ ፆታ ተቆጠረ።
ወንዶች ሴቶች “እነርሱ” ሲሉ ዝቅ የሚያደርጓቸውን ያህል ሴቶችም ወንዶችን “እነርሱ” እያሉ ሌላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ አድርገው እንዲቀበሉ ተገደዱ።
ወንዶች “እኔ” ሲሉ ሴቶችንም “እርሷ” ሲሉ ራሳቸውን ባለቤት አዛዥ የበላይ ሴቶች ደግሞ የበታች መገልገያ ቁስ ያደርጓቸዋል። ከልጅነት ጀምሮ ወንዱ ወንድነት ሴት ሴትነት እየተላበሱ እንዲያድጉ ይደረጋል።
ለወንዱ ጎረድራዳነት፣ ድምቡጭነት፣ ውፍረት ወይም ክሳት መሥፈርት አይሆንም። የወንድ መልክ ለውድድር አይቀርብምና። ወንድ አያለቅስም፤ ወንድ ደረቱን ነፋ ማድረግ አለበት። በአንጻሩ ሴት መኳኳል አለባት፤ ኣካሏን ካልጠበቀች የሚነካት (የሚመኛት) እንደሌለ ይነገራታል። ረጅም ሰዓቷን መስታወት ፊት እንድትቆም ትደርጋለች።
ለዲቦቮር የትኩረት ነጥቧ የሴት ገላ ሳይሆን “ሴት” ራሱ ፆታው ነው። ወንድ ሲነሣ ስለ አካላዊነቱ አይነገርም ይልቁንም ሰለ ወንድነቱ ይነሣል። እንዲያ ከሆነ ሴት ደግሞ ራሱን ችሎ ማንነት ነው፤ “ኅልዮነቱ የተረጋገጠ” ትላለች። በሴት ላይ ያሉ ፈተናዎችም እነዚህ ናቸው ትላለች። በራስ ውበት ፍቅር መውደቅ (ውበት አምላኪነት)፣ ፍቅር (ጥገኝነት) እና ሃይማኖት (ተገዥነት)።
@Zephilosophy
@Zephilosophy
5.1K views19:18