Get Mystery Box with random crypto!

ራስህን ካልሆንክ በተኮረጀ ሕይወት ዘመንንህን ትጨርሳለህ! (እ.ብ.ይ.) ዘመኑ የግልቦች ነው፡፡ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ራስህን ካልሆንክ በተኮረጀ ሕይወት ዘመንንህን ትጨርሳለህ!
(እ.ብ.ይ.)

ዘመኑ የግልቦች ነው፡፡ ቁምነገር የሌለው ትውልድ እየተመረተ ነው፡፡ ለጥበብ የሚንጋጋ ዕውቀት ቆፋሪ፣ እውነት መርማሪ እያነሰ ነው፡፡ ሩጫው ገንዘብ ወዳለበት ነው፡፡ እሽቅድምድሙ ቁሳዊ ነው፡፡ ፉክክሩ አለባበስና አበላል ላይ ነው፡፡ የዘንድሮ ቢዝነስ እውነት፣ እምነትና ሃቅ የለበትም፡፡ ሃይማኖቱም፣ ፖለቲካውም፣ ሙያውም፣ ንግዱም፣ ትምህርቱም፣ ፍቅሩም፣ ትዳሩም፣ ወዳጅነቱም፣ ዝምድናውም፣  ወዘተውም እየተሸቀበ ነው፡፡ መንጋው የሚንጋጋው ለራሱም ለሐገሩም የማይጠቅም ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ረጋ ብሎ የሚያስብ፣ ከመንጋው ተለይቶ መንጋውን የሚመልስ ጠፍቷል፡፡ መሪውም ተመሪ፤ ተመሪውም ደንባሪ ሆኗል፡፡ ሁሉም እየተምዘገዘገ ያለው ወደገደሉ ነው፡፡ “ሐሰተኛው በእምነት ስም” መፅሐፍ ገፅ 61 ላይ ‹‹ከኋላ የሚከተል መምሕር፣ ከፊት የሚቀድም ደቀመዝሙር፤ ሁኔታው ሁሉ የተምታታ ነው›› እንዳለው እርስበርሱ የተምታታ ሐገር ባለቤት ሆነናል፡፡!

የሐሽማል ደራሲ፡-

‹‹አሁን ዘመኑ የጠቢባን ሳይሆን የግልቦች ነው!›› ይለናል፡፡

እውነትነት አለው! አዎ እምነቱ ግልብ ነው፤ እውቀቱ ግልብ ነው፤ ስርዓቱ ግልብ ነው፣ አመራሩ ግልብ ነው፤ ግልብነት የዘመናችን ምልክት ሆኗል፡፡ ዛሬ ዶክተር ምህረትአብ ደበበ በ‹‹ሌላሰው›› መፅሐፉ እንደሚገልፀው ‹‹ማድረግም አለማድረግም›› ኪሳራ ሆኗል፡፡ በብዙ ነገር ረፍዶብናል፡፡ የያዘን አዚም በቀላሉ የሚለቀን አይደለም፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› መፅሐፉ ገፅ 81 ላይ፡

‹‹የማትችለውን ዓለም በሰልፍ የምትኳኳነው፤ የምትችለውን ዓለም ባለመገንባትህ ነው፡፡›› ይላል፡፡

ልክ ነው! አዎ ዓለማችንን ተሰርቀናል፡፡ የእኛ ባልሆነ ዓለም ውስጥ ነው እየተንገላታን ያለነው፡፡ ሌሎች ባዋቀሩት የዓለም ስርዓት ውሰጥ ስለምንኖር ነው ኑሯችን የማይመች፣ ሕይወታችን መከራ ብቻ የሆነው፡፡ በልካችን የተሰፋ ርዕዮት ዓለም ስለሌለን ገልብጠን ያመጣነው ስትራተጂና ፖሊሲ ሱሪ ባንገት ሆኖብናል፡፡ ለህዝባችን የሚሆን፣ እንደሐገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊያዋጣን የሚችል ስርዓት የለንም፡፡ መልካሙን የአባቶቻችንን ጥበብ ጥለነዋል፡፡ እኛነታችንን ንቀነዋል፡፡ የእኛ ባልሆነው የባዕድ ጌጣጌጥ ተማርከናል፡፡ በሰው ጥበብ ለማጌጥ እላይ ታች እንላለን፡፡ ምክንያቱም አሳቢ ሰው አጥተናል፡፡  ተመራምሮ አዲስ መንገድ የሚያሳየን ለራሱም ለወገኑም የሚተርፍ ዜጋ ተቸግረናል፡፡ ተማርኩኝ የሚለውም ለሆዱ ብቻ እንጂ ለገዛ ራሱ ነፍስ እንኳን አልተረፈም፤ እውቀቱ ከአንገት በታች ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ.... ንጉስ ሰለሞን ‹‹ልጄ ሆይ...... ከሕዝብ ጋር አትሂድ!›› የሚልህ ከህዝብህ ተለይተህ ጥፋ ለማለት ሳይሆን ለሕዝብህ የሚሆን መፍትሄ ታበጅ ዘንድ ከመንጋው ተለይተህ አስብ እያለህ ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ሙሉ ጊዜህን የምታጠፋ ከሆነ የምታስብበት ጊዜ አይኖርህም፡፡ ህዝብ በተፈጥሮው በወል ነው የሚያስበው፡፡ አይመረምርም፣ አይፈትንም፣ የተቀበለውን መስጠት እንጂ አዲስ የሕይወት መንገድ አይቀርፅም፡፡ ህዝብን የምትከተል ከሆነ ለራስህም፣ ለሐገርህም አትሆንም፡፡ ማሰላሰያ፣ ማገናዘቢያ፣ ራስህንም ዓለሙንም ማንበቢያ ጊዜ ከሌለህ ራስህን ዘንግተህ ያንተ ባልሆነው የሌሎች ዓለም ስደተኛ ነው የምትሆነው፡፡ መንጋው ያንጋጋሃል!

ወዳጄ ሆይ.. ወዳጅነት መልካም ነው፤ ዝምድና አይከፋም፣ አብሮአደግነት ደግ ነገር ነው፤ ባልንጀርነት ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን የማሰቢያህን ጊዜ የሚሻማ ማንኛውም የማህበራዊ ግንኙነት ሁሉ ዘለቄታዊ ጥቅም አይሰጥህም፡፡ ሰዎች በዘልማድ ባሰመሩት የአኗኗር መስመር ብቻ መሄድ የሚያስገኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ የብዙዎቻችን ሕይወት አሰልቺ እየሆነ የመጣው በድግግሞሽ ህይወት ውስጥ ስለምንመላለስ ነው፡፡ ኑሯችን አዙሪት የሆነው በሰጡን ርዕዮት ዓለም፣ ባቀበሉን የአኗኗር ዘይቤ ስለምንጓዝ ነው፡፡ የራሳችን መንገድ የሌለን የማሰቢያ ጊዜ ስላጣን ነው፡፡ የተወጠርንበትና የተጠመድንበት ነገር ሁሉ የሚያለማን ሳይሆን የሚያጠፋን ነው፡፡ በራሳችን መንገድ ካላሰብን የትም አንደርስም፡፡ እንዲሁ የኋሊት እንምዘገዘጋለን፡፡ ህዝብነት አያተርፍም፤ መንጋነት በራስህ እንዳትተማመን ያደርግሃል፡፡ ለህዝብ መቆም እንጂ ከህዝብ ጋር መሄድ የተለየ ውጤት አያስገኝም፡፡ ለህዝብህ ጠብ የሚል መፍትሄ አምጠህ የምትወልደው ከመንጋው ተነጥለህ ማሰብ ስትችል ብቻ ነው፡፡ መነጠልህ እስመጨረሻው የሚለይህ ሳይሆን ህዝብህን መልሶ እንዲጠቅም የሚያደርግ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ.... ምርጫዎችህን ለመምረጥ፣ የሕይወት መንገድህን ለመቀየስ፣ መነሻህን አሳምረህ ፍጻሜህን ለማስዋብ አንተ አንተን ሆነህ መገኘት አለብህ፡፡ ለራስህ የማታውቅ ከሆነ ሌሎች ባወቁትና በቀረፁት መንገድ ትከተላለህ እንጂ ራስህን አትመራም፡፡ ስታስብ፣ ስትመረምር፣ ስታሰላስል፣ ስታስተውል፣ አዲስ ሃሳብ ስትፈጥር ግን ችግሮችህን ትቀርፋለህ፣ መሰናክሎችህን ትሻገራለህ፣ ስልጣኔን ታመጣለህ፡፡ ራስህን ከሌሎች ባርነት ነፃ ታወጣለህ፡፡ አልያ ግን በመንጋው ተጠልፈህ በራስህ መንገድ ትመላለስ ዘንድ እንዳትችል አቅም ታጣለህ፡፡ ተከታይነት በራስህ ፀንተህ ለመቆም ሃይል እንዳይኖርህ ያደርግሃል፡፡ ተጎታች እንጂ መሪ አትሆንም፤ ጠባቂ እንጂ ሰጪ ትሆን ዘንድ አትችልም፡፡ የሰው ዓለም መፃተኛ እንጂ የራስህ ዓለም ሰሪ ለመሆን አይቻልህም፡፡ በተኮረጀ ሕይወት ዘመንንህን ትጨርሳለህ፡፡

ባለመድሐኒት ሆይ....
ራስህን አድን!
ራስህን


ል!
አንተነትህን
ቀ-ጥ-ል፣
እስትንፋስህን ቀ-ጣ-ጥ-ል፡፡

ቸር ቅጥ’ለት! ደግ ንጥ’ለት!

እሸቱ ብሩ ይትባረክ

@Zephilosophy
@Zephilosophy