2023-03-25 10:59:05
ፖሊስ ምን አለ? ካህኑን ማን ገደላቸው ?" ኃይሌ ጋርመንት " የሁርሲሳ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቀዳሽ ካህን ቀሲስ ዐባይ መለስ " ማንነታቸው አልታወቀም " በተባሉ አካላት በተፈፀመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።
ካህኑን የሚያውቋቸው አገልጋዮች /ምዕመናን ስለነበረው ሁኔታ / ስለጥቃቱ ምን አሉ ?
(ለማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ከተናገሩት የተወሰደ)
ቃላቸውን የሰጡ ምዕመን አንድ ፦
" ትላንት/መጋቢት 14 ቅዳሴ ቀድሰው በአጋጣሚ እኔ በውጪ አስቀድሼ ነበር ፤ ወደ ደጀሰላም ገባን ምግብ ተመግበን ተለያይተን ነው እነሱ ወደ ኃላ ነበሩ ከምግብ በኃላ እኛ እዚህ አካባቢ ነበርን ተሻግረው ቤታቸው ቆይተው የሌላ (ቄስ አሰፋ ይባላሉ) የእሳቸው ቤት ነው የፈረሰው የእሳቸው ቤት ፈርሶ ሊሻገሩ ገና ከቤታቸው ወጥተው ትንሽ እራመድ እንዳሉ ነው ተመቱ የሚባል ወሬ ሰማን።
ተደወለና ባጃጅ አምጡ ተብለን እስከቤታቸው ድረስ እንደምንም ተቋቁመውት ሄደዋል ከቤታቸው በኃላ አንድ ካህን አብረው ይዘዋቸው መጡ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲደርሱ ተሸነፉ ወደቁ ፤ እኔ ለማናገር ሞከርኩኝ ምንድነው ? ምን ሆነው ነው ? ምንድነው የተፈጠረው ? ስላቸው ምንም ሊመልሱልኝ አልቻሉም ወዲያው ተናነቃቸው ባጃጅ ላይ አስገባናቸው ወደ ክሊኒክ ወሰድናቸው እዛሪ ሪፈር ተባለ ወደ ጥሩነሽ (ሆስፒታል) ወስደው ሌሊት አረፉ የሚለውን ሰማሁ በጣም አዝኛለሁ። "
ቃላቸውን የሰጡ አገልጋይ ሁለት ፦
" ዘጠኝ ሰዓት ከለሊቱ አረፉ ይሉኛል የደብሩ ዋና ፀሀፊ ፤ እንዴት ? አልኳቸው ፈረሳ ነበረና እዛ ፈረሳ እኔ መጠምጠሜን አልያዝኩም፣ ጋቢም አልያዝኩም ማንም ያወቀኝ ሰው የለም ካህንም ልሁን ምዕመንም ልሁን አሉ፤ እሳቸው ግን ጋቢያቸውን ቆባቸውን አድርገው መጥተው እዛ ነው የደበደቧቸው አሉኝ። ቅዳሴ ውለዋል ቀድሰው እዛ ማዶ ፈረሳ አለ ሲባል ግን የኛ የማርያም አገልጋዮችም የፈረሰባቸው ነበረና እዛ ሄጄ አብሬም ልቀላቀል ፤ ባለኝ አቅም ልርዳቸው ብለው ነው ተነስተው የሄዱት፤ እጂ ቀድሰው ውለው ነው የሄዱት። "
ቃላቸውን የሰጡ ምዕመን ሶስት ፦
" የአሟሟታቸውን ሁኔታ ሲነግሩኝ በዕለቱ በ14 ማለት ነው ፤ ቅዳሴ ቀድሰው ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለው አቀብለው ወጣ እንዳሉ ነው ያልታወቁ ሰዎች መንገድ ላይ አደጋ ያደረሱባቸው የሚል ነው የተሰጠኝ መረጃ።
ቤት የላቸውም ፤ ስለቤቴ ብለው የተከራከሩትም ነገር የለም መንገድ ላይ እየሄዱ ነው የሌላ ሰው ቤት ፈርሶ ወደዚያ ለማስተዛዘን ሲሄዱ ነው ጥቃት የደረሰባቸው ብለው ነው የነገሩኝ አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች። "
ቃላቸው የሰጡ ምዕመን አራት፦
" ባጃጅ ላይ ስናስገባቸው አንድ ነገር ብቻ ነው የተናገሩት ' እባካችሁ እዚሁ ቤተክርስቲያን አድርጉኝ አትውሰዱኝ ' ሲሉ ተነፈሱ ከዚያ መናገርም አልቻሉም ፤ ውሃም ስንሰጣቸው መቀበል አልቻሉም እዛም ስንወስዳቸው መረጃ ሊነግሩን አልቻሉም "
የካህኑ ልጅ ፦
" ቤት ሲመጣ ደም ደምቶ እራሱ ላይ ነጠላ አድርጎ ነው የመጣው ከዚያ በኃላ ምን ሆነህ ነው ስለው መተውኝ ነው ያለው ሌላ ቄስ ነበሩ መጡና ሃኪምቤት ወሰዱት።
ሃዘን ናፍቆት ነው የሚሰማኝ አባ አባቴ ስለው በጣም ነው የምወደው ስለዚህ ካለሱ ማንም የሚያሳድገኝ የለም። "
ቀሲስ ዐባይ መለሰ በምዕመኑ እጅግ የሚወደዱ፣ የሚከበሩ፣ ሰርተው የሚያሰሩ ያላቸውን ሁሉም አቅም ለቤተክርስቲያኗ የሚሰጡ ትልቅ አባት እንደነበሩ ምዕመናኑ ገልጸዋል።
ካህናት በአካባቢው ላይ የተፈፀመው ድርጊት ፍርሃት ላይ እንደጣላቸው የተገለፀ ሲሆን በእሳቸው ህልፈት ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ እንዳሉ ተጠቁሟል።
ፖሊስ ስለጉዳዩ ምን አለ ? ከታች ያለውን ያንብቡ
የአዲስ አበባ ፖሊስ የቀሲስ ዐባይ መለሰን ግድያ በተመለከተ " መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ/ም አገልግሎታቸውን ጨርሰው ወደ የሚኖሩበት ሸገር ከተማ ልዩ ቦታው ኤርቱ ሞጆ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ በተፈጠረ ፀብ ጉዳት ደርሶባቸው በጡሩነሽ ቤጁንግ ሆሰፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በትላንትናው ዕለት መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ/ም ህይወታቸው አልፏል፡፡ " ብሏል።
" ወንጀሉ በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የተፈፀመ እንደሆነና ጉዳዩ ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲሰጠው ለማስመሰል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተሰራጩ የሚገኙት መረጃዎች ትክክለኛ አይደሉም " ሲል ገልጿል።
የቀሲስ ዐባይ አስክሬን ለተጨማሪ ምርመራ አቤት ሆስፒታል መላኩን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ቀሪ የፖሊስ ምርመራ እየተካሔደ መሆኑን በሽገር ከተማ አሰተዳደር የፉሪ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ዳንኤል ኃ/ማርያም ገልፀዋል ብሏል።
1.3K views07:59