2022-06-20 11:27:44
“የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ እንዲታገድ እየሰራሁ ነው” - የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ እንዲታገድ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከታዲጊዎች እና ወጣቶች ስብዕና ግንባታ እንዲሁም በተለያየ መንገድ ከሚያስከትላቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች አንጻር ዘርፉ ሊታገድ ይገባል በሚል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ በሚኒስቴሩ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ አበበ ሃይማኖት መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የስፖርት ውርርድ ለማስቆም የተለያዩ የንቅናቄና የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው ሲካሄዱ መቆየታቸውን የገለፁት ኃላፊው፤ አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች መሰል የምክክር መድረኮች በበቂ መጠን እየተካሄዱ እንደማይገኝ ተናግረዋል።
በተለያየ ጊዜ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተዘጋጁ የዳሰሳ ጥናቶች የስፖርት ውርርድ ለወጣቱና ለታዳጊው ዘርፈ ብዙ አደጋ የደቀነ መሆኑን ያመላከቱ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ዘርፉ በተጨባጭ ችግር የሚፈጥር መሆኑን ገምገመናል ብለዋል።
የስፖርት ውርርድ ቁማር ነው ብለን እንቅስቃሴ ጀምረናል፤ ቁማር የሚባለው ነገር ደግሞ በራሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያስከትል ጉዳይ ነው ብለዋል።
ቁማር ታዳጊዎችንም ይሁን አዋቂ ሰዎችን ወዳልተፈለገ መንገድ ሊወስድ የሚችል ማህበራዊ ቀውስ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ማንኛውም ሰው ሰርቶ የመለወጥ እሳቤውን የሚያቀጭጭ፣ ቤተሰብን ጭምር ወደ መበተን ሊያደርስ የሚችል ጉዳይ እንደሆነም ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ወጣቶች እና ታዲጊዎች ለቤቲንግ ውርርድ ሲሉ ያላቸውን ነገር በሙሉ እስከማውጣት እንደሚደርሱ ጠቅሰው፤ ወጣቶች ስራን ከመስራት ይልቅ በአቋራጭ መክበር እንዲያስቡ በማድረግ ምርት እና ምርታማነትን የሚቀንስ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ዘርፉ በስነልቦና ረገድም ለጭንቀት፣ ለድብርት ብሎም እራስን እስከማጥፋት የሚዳርግ ችግር የሚያስከትል በመሆኑም የሚመለከተው አካል በጊዜ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰል የስራ ዘርፎች እንደስራ መታየት እንደሌለባቸው እና ከደቀኑት ፈርጀ ብዙ አደጋ አንጻር ሊታገዱ ይገባል በሚል ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።
ተቋሙ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት መድረኮችን በማዘጋጀት ፍቃድ ለሚሰጡት የንግድ ሚኒስቴር እና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተቋማት አስፈላጊውን የግንዛቤ እና የማሳወቅ ስራ መሰራቱን የገለፁት ኃላፊው፤ እነዚህ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አለማድረጋቸው ለውሳኔው መዘግየት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን መግለጻቸውን የኢብኮ ዘገባ ያስረዳል።
@tikvahethmagazine @tikvahmagbot
22.5K viewsedited 08:27