2022-12-21 14:51:05
የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በጥብቅ ድስፕሊን እንዲመሩ ትዕዛዝ ተሰጠ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ መሰቀልና መዝሙር መዘመር ጋር በተገናኘ፣ በት/ት ቤቶች ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች በጥብቅ ድስፕሊን እንዲመሩ መመሪያ መሰጠቱ ተሰማ፡፡
ትምህርት ቤቶች በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲመሩ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሲሆን፤ በጥብቅ ይፈጸም የተባለው አሰራር በተማሪዎች እና በመምህራን ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ያዛል ተብሏል፡፡
#አዲስ_ማለዳ በትምህርት ቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ ተፈርሞ፣ ለኹሉም ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የተላለፈውን ደብዳቤ መመልከቷን ዘግባለች፡፡
በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው፤ ትምህርት ቤቶች አንድ ቀን ላረፈደ ተማሪና አንድ ቀን ለቀረ ተማሪ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ ታዘዋል፡፡
እንዲሁም ኹለት ቀን ያረፈደና የቀረ ተማሪ በወላጅ ፊት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ዘላለም በፈረሙበት ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል፡፡ ከኹለት ቀን በላይ ያረፈደና የቀረ ተማሪ በመመሪያው መሰረት ተፈጻሚ የሚሆን እርምጃ እንደሚወሰድበትም ተመላክቷል፡፡
በትምህርት ቤቶች በር ላይ ጥብቅ ፍተሻ እንዲደርግ የሚያዘው ደብባቤው፣ ተማሪዎች ስልክ፣ ርችትና ፊኛ የመሳሰሉ ቁሶችን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዳይሄዱ ገደብ ጥሏል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የተከለከሉ መገልገያዎችን፣ ይዞ የተገኘ ተማሪ የድስፕሊን እርምጃ እንዲወስዱ ትምህርት ቤቶች መታዘዛቸውም ተነግሯል፡፡
የትምህርት አመራር፣ መምህራንና ሰራተኞች በሙሉ የሥራ ሰዓታቸውን አክብረው፣ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጥብቅ ትዕዛዝ የተሰጣቸውም ሲሆን፤ በዚህም ማርፈድ፣ መቅረትና የሥራ ሰዓት ሳያልቅ ከትምህርት ቤት ግቢ መውጣት የተከለከለ ነው ተብሏል፡፡
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ትዕዛዝ ባስተላለፉበት ደብዳቤ፣ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ የማያስፈጽም በየደረጃው የተቀመጠ የትምህርት ቤት አመራርም ተጠያቂ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም ኃላፊው ለክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች፣ ባስተላለፉት ትዕዛዝ “ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ቦታ ናቸው” ያሉ ሲሆን፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያደናቅፍ ተግባራ የሚፈጽም ማንኛውም አመራር፣ መምህር፣ ሰራተኛና ተማሪ ላይ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድና ሪፖርት እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ ማለዳ
የትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ የተረጋገጡ ዜናዎችን ለ ጓደኛዎ ያጋሩ https://t.me/Temhert_Minister
https://t.me/Temhert_Minister
2.8K viewsedited 11:51