2023-05-29 09:57:52
ትዳርና ኃላፊነት
ትዳር ፍቅር ብቻ አይደለም። ትዳር ኃላፊነትም ነው።
በትዳር ውስጥ ብዙ የሚገመቱም የማይገመቱም ጉዳዮች ሊያጋጥሙ ይችላል። ያልጠበቃችሁት እና የሚያናድዳችሁ ጉዳይ ቢያጋጥማችሁ እንዴት ታስተናግዱታላችሁ? ትቆጣላችሁ? ትጣላላችሁ? ታግሳችሁ በዝምታ ታልፋላችሁ? በይቅርታ እና እርቅ ታልፋላችሁ? ወይንስ ወደ ፍቺ ትሄዳላችሁ?
በትንሽ በትልቁ ወደ ፍቺ የሚሮጡ ባለትዳሮች በመንፈስና በአስተሳሰብ ያልበለጸጉና ራስ ወዳዶች ናቸው። አንዳንዶች ተጋብተው አንድ ዓመት እንኳ ሳይቆዩ ወደ ፍቺ ይሄዳሉ። ይሄ ልዩነትን መሸከም አለመቻል ነው፣ አለመብሰል ነው። ልዩነትን ማስተናገድ ሳትችሉ ወደ ጋብቻ አትሩጡ።
ትዳር ስትመሰርቱ ኃላፊነት ያለው አኗኗር ውስጥ መግባታችሁን አስቡ። ትዳር የራሳችሁን ፍላጎት ለሌላው ማስገዛት መሆኑን እወቁ። ትዳር በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር ራስን ለማስገዛት መፍቀድ መሆኑን ተረዱ። ትዳር ውስጥ ስትገቡ ነጻነታችሁን በተወሰነ ደረጃ እንደምትተዉ እመኑ።
ትዳር ውስጥ ልጆች ይመጣሉ። ልጆች በነጻነትና በደስታ እንዲያድጉ የራስን ስሜት መግዛትና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁንልኝ ከማለት ራስን ማቀብ ያስፈልጋል፣ልጅ ወልዶ የራሱ ጉዳይ ብሎ በትኖ የሚሄድ ከእንሰሳም ያነሰ ሰብዕና ያለው ነው። ፍሬ ለማፍራት ስንዴዋ እንኳ ራሷ እንዴት እንደምትፈርስ አታዩምን? ታድያ ከስንዴ እንኳ ታንሳላችሁ?
ኃላፊነትን ለመቀበል ካልተዘጋጃችሁ ወደ ትዳር አትግቡ፣ ትዳርን ቸኩሎ ኃላፊነትን ለመሸከም ብቁ ሳይሆኑ መያዝ አይገባም። ትዳር የዕቃ ዕቃ ጨዋታ አይደለም። ትዳር የፉክክር ቤትም አይደለም ፣ ትዳር ራስን አሳልፎ መስጠት ቢጠይቅም፣ በጥበብ ከተያዘ ደግሞ ፈተናዎች ሁሉ ቀላል ናቸው።
ትዳር በህይወት የሚከሰቱ ለውጦችን የማስተናገድ አቅም ይጠይቃል። ህመም፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ እስር ጥጋብ፣ ውስልትና፣ ንዴት፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ ሹመት፣ ማግኘት፣ ማጣት፣... ትዳርን ይፈትናሉ። ግን ላወቁበት፣ ለበሳሎችና ኃላፊነት ለሚሰማቸው ትዳር ለማፍረስ ምክንያት አይሆኑም።
ትዳር ለመያዝ ማናችንም የመጀመሪያም ይሁን የመጨረሻም ሰዎች አይደለንም። ትዳር ውስጥ ያለ አለመግባባትም ያለና የነበረ የሚኖርም ነው። እናንተ ያጋጠማችሁ በሌሎችም የደረሰ እንጂ አዲስ አለመሆኑን እወቁ። ቁም-ነገሩ ችግርን መፍታት እንጂ ችግርን ማውራት አለመሆኑን ተገንዘቡ። ችግርን ታግሳችሁ ፍቱ።
ከትዳር በፊት ሁለት ዓይናችሁን፣ ከቻላችሁም ሦስተኛውን ከፍታችሁ በደንብ እዩ፣ ፈትሹ፣ በአእምሮ ተዘጋጁ፣ ለኃላፊነት ተዘጋጁ። ትዳር ውስጥ ከገባችሁ በኋላ ግን አንድ ዓይን ብቻ ይበቃችኋል። ትዳር ውስጥ ሁሉን ካልሰማሁ ሁሉን ካላወቅሁ አትበሉ። ሁሉን ማወቅ አይጠቅማችሁም።
መጀመሪያ አይታችሁና አምናችሁ ለኃላፊነት ተዘጋጅታችሁ አግቡ። እንደተጋባችሁ ለመውለድ አትቸኩሉ። ምንም ምንም ምንም ቢሆን ግን ወልዳችሁ አትፋቱ፣ ከፀሓይ በታች አዲስ ነገር የለም! ወልዶ የሚፋታ ግለሰብ ፣ ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን አገር ያፈርሳል።
ውብ ምሽት
4.2K viewsAddisu, 06:57