2022-09-02 19:54:20
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች ነገ ያስመርቃል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርኃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ5 ሺህ 540 በላይ ተማሪዎችን በነገው እለት እንደሚያስመርቅ አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደገለጹት፣ ተመራቂዎቹ በመጀመሪያ፣በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ የስልጠና መስኮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው 31 ተማሪዎችን በ3ተኛ ዲግሪ እንደሚያስመርቅና ይህም ቁጥር በታሪኩ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አስራት "ከጠቅላላ ምሩቃን መካከል 1 ሺህ 856ቱ ሴቶች ናቸው" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ማኅበረሰብ አቀፍና ሀገር ተኮር የሆኑ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪ መርኃ ግብሮችን በሂደት እየቀነሰና የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርኃ ግብሮችን እያሰፋ ለመሄድ የሚያስችለውን መርኃ ግብር ነድፎ እየሠራ ነው።
"ተቋሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በቀጣይ በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩ ከተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆኑ ከ2015 ጀምሮ ወደተግባር ለመግባት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ነው" ብለዋል።
ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተማሪዎችን ለመሳብ የሚያስችሉ አሠራሮችን ዩኒቨርሲቲው እየዘረጋ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አስራት፣በአሁኑ ወቅትም 50 ዓለም አቀፍ ተማሪዎች እንዳሉት ገልጸዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ፣በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም በስፔሻሊቲና በሰብ ስፔሻሊቲ የትምህርት መርኃግብሮች ከ48 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
አሚኮ
206 viewsedited 16:54