2023-01-26 21:23:28
ከ2014 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የማለፊያ ውጤት ያመጡት ሦስት በመቶ ብቻ ናቸው
ኩረጃን ለማስቀረትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚል፣ በልዩ ሁኔታ ከተሰጠው የ2014 የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት (የማለፊያ ነጥብ) ያገኙ ተማሪዎች 28 ሺሕ ብቻ መሆናቸውን ታውቋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲ በተሰጠው ፈተና ከ980 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፣ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች 28 ሺሕ ገደማ መሆናቸው ከትምህርት ሚኒስቴር ምንጮች ለማወቅ ተችሏል።፡
ከፍተኛ ጥያቄ የሚነሳበትን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል እና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ላይ የሚስተዋለውን ኩረጃ ለማስቀረት ወሳኝ ነው የተባለለት ፈተና በጥብቅ ቁጥጠር ከ50 በሚበልጡ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ይታወቃል፡፡
የፈተና ውጤቱ ከዛሬ እኩለ ሌሊት ጀምሮ በበይነመረብ ይፋ እንደሚደረግ፣ ተማሪዎችም በተሰጣቸው የመለያ ቁጥር ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በውጤቱ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር በነገው ዕለት መግለጫ እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር፣ ዩኒቨርስቲዎች ካላቸው የመቀበል አቅም ጋር በፍፁም እንደማይጣጣም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች 130 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንዳላቸው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ካላቸው የቅበላ አቅም የ2014 ተፈታኞች የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት ከዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበል አቅም ከ20 በመቶ የማይበልጥ ነው ማለት ነው፡፡
ከፍተኛ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ማጋጠሙን የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሰሙ ሲሆን፣ ያጋጠመውን የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምን ይደረግ በሚለው ላይ ምክክር እየተደረገበት ነው፡፡ በውይይቱ የዩኒቨርስቲዎች መቀበል የሚችሉት አቅም ጋር የሚጣጣም ተማሪ፣ ወደ ዩኒቨርስቲ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንን ተከትሎ፣ ዩኒቨርስቲዎች በመቀበል አቅማቸው ልክ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ አማራጭ እየተፈለገ ነው፡፡ በዚህም በልዩ ሁኔታ ለማለፊያ የቀረበ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን የማጠናከሪያ ትምህርት ወስደው ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ይደረግ የሚለው አንዱ አማራጭ ሆኖ በመንግሥት በኩል እየታዬ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተማሪዎቹ ውጤት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲያውቁት የተደረገ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡
የ2014 የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ፣ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለውን ስብራት ለማከም እንደ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ ተወስዷል፡፡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግበራዊ የተደረገው የፈተና ስርዓት፣ በዩኒቨርስቲ መምሀራን አማካኝነት፣ ተማሪዎችም ከተማሩበት አካባቢ ርቀው በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢዎች ውስጥ የተሰጠ ነበር፡፡
423 views18:23