2023-02-22 08:09:20
የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ12 ርእሰ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ማድረጋቸው ተገለጸ።
በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል ለሁለተኛ ጊዜ የሁለትዮሽ ውይይት ከየካቲት 4 ቀን እስከ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሩሲያ ሞስኮ መደረጉ ይታወሳል።
በጉባኤው በኢትዮጵያ በኩል በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት በሩሲያ በኩል በብፁዕ አቡነ ሊዮኒድ በአፍሪካ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ተከናውኗል።
በውይይቱ ላይ ከአራት ዓመታት በፊት በተካሔደው በመጀመሪያው የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ወቅት በጋራ ይተገበራሉ ተብለው በተስማሙባቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ ግምገማ ተደርጓል።
እንዲሁም ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ክርስትና እና ክርስቲያኖችን መከላከል፣ በዘመናዊው ዓለም ክርስቲያናዊ ዕሴቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ በሚዲያ አማካኝነት የልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ በትምህርት ዘርፍ መደጋገፍን ጨምሮ በ12 ርእሰ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ፈጽመዋል።
የመነኮሳት ልዑካን ወደ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት እንዲሔዱና በሁለቱም በኩል ያለውን የገዳማውያን ሕይወት እንዲመለከቱም ዕቅድ ይዘዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሞስኮ የነገረ መለኮት አካዳሚ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ በትብብር እንዲሠሩ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ልዑክ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲንና ሌሎች የኢትዮጵያ ቦታዎችን እንደሚጎበኝም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ያሉ ቅዱሳን ቦታዎችን መጎብኘት እንዲችሉ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል። መረጃው የተሚማ ነው።
2.0K views05:09