2023-02-23 17:15:54
ከዚህ ልጅ ምን እንማር ይሆን
ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል ቆሜ አላያትም ብሎ መስቀሉን ጨብጦ የተቃጠለዉ የጎጃም ወጣት የህይወት ታሪክ
+++++++#የቻለ_ለሌሎች_ያጋራ+++++++
ጉዳዩ እንዲህ ነዉ፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን በደጀን ወረዳ የሚገኘው ደብረ መድኃኒት ሰብሸንጎ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በ1267 ዓ.ም መሆኑ ይነገርለታል።
ታቦቱ ተአምረኛ፣ ጠበሉ ፈዋሽ ነው። የደብሩ ነዋሪዎች ከሆኑት መካከልአቶ ጌታቸው እጅጉና እናቱ ወ/ሮ ውዳላት ያየህይራድ የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች በ1981 ዓ.ም የሚያምር ወንድ ልጅ ሲወልዱ ይርመዴ በማለት ስም አወጡለት።
ዓይኑ ቀለም መለየት፣ አንደበቱ ፊደል መጥራት ሲጀምር የትመን አቦ በሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ 6ኛ ክፍል ተማረ። ከዚያም አራት ዓይናው ሊቅ አለቃ ውብሸት ወንበር ዘርግተው ባስተማሩበት አጠገብ በተሠራው ብቸና ከተማ በሚገኘው በላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዐሥራ አንደኛ ክፍል ቢማርም ትምህርቱን ለመቀጠል የማያስችል ችግር ገጠመው። ተምሮ እስከምጨርስ የቤተሰቦቹ ችግር ጊዜ የማይሰጥ ሆነበት።
ትምህርቱን አቋርጦ ቤተሰቦቹን በመደገፍ ሕይወታቸውን ለመቀየር የወሰነው በደብሩ አጠገብ የሚያልፈውን ሙጋ የተባለውን ወንዝ በመጥለፍ ለልማት ነበር። ለአምስት ዓመታት ቀን ከሌት በመሥራት አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የቤተሰቦቹ ሕይወት ከቀየረ በኋላ ዓይኑ ያረፈባትን ሐና አየለ የተባለችውን ወጣት አግብቶ አንዲት ሴት ልጅ ወለደ። ትዳሩ ባይዘልቅም እርሱ ግን ልብስ ስፌት ሠልጥኖ በዚያ መተዳደር ጀመረ።
ልብስ ሰፍቶ ከሚያገኘውን ገንዘብ የዕለት ጉርሱን፣ የዓመት ልብሱን በማስቀረት ለቤተ ክርስቲያንና ለችግረኞች መርዳቱን ገንዘቡ አደረገ። ርኅራኄው አምሳያ እንዳልነበረው የሚያውቁት የሚመሰክሩለት ምነው እንደ እርሱ በመሆን የሚል መንፈሳዊ ቅንዓት እያደረባቸው ነው። ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለተቸገረ በማይሰስተው እጁ መመጽወት የሚወደው ይርመዴ ዐመታዊ የታቦት ንግሥ የማያመልጠው ሲሆን ሲሔድም ባዶውን የማይሔድ አንድ ጊዜ ከሦስት ሺህ ብር በላይ ሰጥቶ የሚመለስ ክርስቲያን ነበር።
ይርመዴ “አልባሳት የምሰፋው ትርፍ ለማግበስበስ አይደለም” የሚል ፈሊጥ ነበረው። ገዝቶ በሣጥን ያስቀመጠውን ልብስ ለታረዘ ሰጥቶ ሲጨርስ ብትን ጨርቅ ገዝቶ ሰፍቶ ያለብስ ነበር። የማስቀድመው መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ምክንያት የሚሆኑኝን ነው በማለት ንሰሓን አባቱ ሁለት ጊዜ ሰፍቶ አልብሷል። የተቸገረ ሰው አይቶ ማለፍ የማይሆንለት ይርመዴ ስንቅና የትራንስፖርት ላለቀባቸው ጠበልተኞች ገንዘብ በመስጠት ሀገራቸው እንዲገቡ ያደርግ ነበር።
ገንዘብ መመጽወቱና የተቸገረ መርዳቱ አላረካው ያለው ይርመዴ የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ክርስትና የተነሣበት ደብረ መድኃኒት ሰብ ሸንጐ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ መሆኑን ሲሰማ ቤተ ክርስቲያኑ ከተቃጠለማ አብሬ እቃጠላለሁ እንጂ ሲቃጠል በፍጹም ቆሜ አይሆንልኝም በማለት በፍጥነት ወደ እሳቱ ሄደ። ለቃሉ ታማኝ፣ ለእምነቱ ሟች የነበረው ይርመዴ ጌታቸው ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር መቃጠንል መርጦ እሳቱ ከተነሣበት ጉልላት ላይ ሊወጣ ሲሞክር ጓደኞቹ ሊከለክሉት ቢሞክሩም አልቻሉም።
በፍጥነት ወጥቶ አማትቦ ወደ እሳት የተቀየረውን የቤተ ክርስቲያን ጉልላት ያቀፈው ተነፋፍቆ የከረመ ወዳጁን ያገኘ ያህል ነበር። ይርመዴና የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት እንደ ተቃቀፉ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ተያይዘው ጣራው ላይ ወደቁ።
ላለመላቀቅ ቃለ ማሐላ የፈጸሙ የሚመስሉት ይርመዴና የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ጣራው ሲደረመስ ተያይዘው ወደ ቤተ ልሔም ወረዱ። በቦታው የደረሱ ክርስቲያኖች ይርመዴን በውስጥ፣ መስቀሉን በላይ ተናንቀው አገኟቸው።
ቤተ ክርስቲያንን ከራሱ አስበልጦ የሚወደው ወጣቱ ክርስቲያን ራሱን እንደ ሻማ በማቅለጥ ሰማዕትን የተቀበለው በእንዲህ ያለ ጥብዓት ነው። በዚህ ዘመን ለምንኖር ክርስቲያኖች አምላካችን እንዲህ ያለውን ጥብዓት ያድለን።
2.9K views14:15