2022-12-13 23:27:22
መረጃን ማጥለል፤ መጭመቅ እና በቀላል ጥረት መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ጊዜ ገንዘብ እና ጤናቸውን እንዲጠብቁ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት።
መግቢያ
ማህበራዊ ሚዲያ እንዴት ጉልበት ያለው መሳሪያ እንደሆነ ለማየት መቸም በ2016ቱ የአሜሪካን ምርጫ ውጤት ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ማስታወስ በራሱ በቂ ነው። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ለመምጣት ትዊተርን የተጠቀሙበትን መንገድ ስናስተዋል ሶሻል ሚዲያ ለፓለቲካዊ ዘመቻዎች እና የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ቁልፍ ሚና በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። ባልተጠበቀ እና ብዙሃንን ባስገረመ መልኩ ወደ ዋይት ሀውሰ ለመግባት ትራምፕ ከተከታይ ደጋፊዎች ጋር በፍጥነት እና በስፋት ለመገናኘት ከየትኛውም የመገናኛ መሳሪያ በላይ ማህበራዊ ሚዲያ አቅም እንዳለው ተረድተዋል። ይህንን በውጤታማነት መተግበር ችለዋል። አገራችንን ጨምሮ በሌሎች የአለማችን ሀገራትም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት እንዴት ጦርነት ፤ ህዝባዊ አመጽ ፤ ህዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ /የቡድን ድርጊቶች ሊመሩ እንዲሁም ሊቀጣጠሉ እና ሊሳለጡ እንደሚችሉ ከበቂ በላይ አብነቶች አሉ።
የማህበራዊ ሚዲያን ትልቅ ተጽእኖ ፈጣሪነት እና የዘመኑ ፖለቲካ ቁልፍ ማንቀሳቀሻ መሳሪያነት የማይካድ ሀቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተጽእኖው ከቁጥጥር እየወጣ ለግለሰብ ዜጎችም ሆነ ለአገራት መሪዎች አስቸጋሪ ሀይል ወደ መሆን እያቆጠቆጠ የመጣ ይመስላል።
በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚተላለፉ ማለቂያ የሌላቸዉ የሚመስሉ የፖለቲካ መረጃዎች ሱሰኛ የሆናቸሁ ትኩረታችሁን መሰብሰብ የተቸገራችሁ ይመስላችኋል? የኢንተርኔት ኮኔክሽን እንዳገኛችሁ በመጀመሪያ የምትገቡት ወደ ትዊተር ፤ ፌስቡክ ፤ ኢንስታግራም ፤ ዩቲዩብ ወዘተ ነው? ብዙ ጊዜ ለማግኘት የምትፈልጉት መረጃሰ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው? ማህበራዊ ሚዲያን ፍሪያማ በሆነ መንገድ መጠቀም መላ እየፈለጋችሁ ከሆነ ?
መርህ በሌለው እና በማስረጃ ባልተመሰረተ ኦንላይን ላይ በሚካሄድ የፓለቲካ ውይይት አጠቃላይ የግል ደህንነታዎን እና ጤናዎ ላይ ተጻእኖ እንዳደረገብዎት ካሰቡ እና ፈቱን መፍትሄ እየፈለጉ ከሆነ? በዚች አጭር ፅሁፍ እነዚህን እና መሰል ጉዳዩች ላይ ሀሳብ ለማንሸራሸር እሞክራለሁ።
ማህበራዊ ሚዲያ ሰንል?
በኢንተርኔት አሳላጭነት በድረ ገጽ መተግበሪያ /አፕ/ ወይም ድረ ገጽ የሚከናወን ለመረጃ ዝውውር እና መልዕክት ርስበርስ ለመለዋወጥ የሚያስችል መድረክ ብሎ በቀላሉ ብያኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ፌስቡክ ፤ ዩቱዩብ ፤ ዋትስአፕ ፤ ቲዊተር ፤ ኢንስታግራም ከዋናወቹ እና ብዙ ተጠቃሚ ካላቸዉ የሶሻል ሚዲያዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ርስበርስ ለመነጋገር፤ ለመተባበር፤ ርስበርስ ግንኙነት ለመፍጠር እና ግንኙነቶችን ለማስቀጠል ለማህበራዊም ሆነ ለቢዚነስ አላማ ሊውል የሚችል መሳሪያ ነው።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙዎቻችን ዋና የህይወታችን አንዱ ክፍል እንደመሆኑ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ውይይቶችም የየለት ህይወታችን ገጽታ እንደመሆናቸው በኑሮዋችን ላይ እያመጡት ስላሉት አንድምታ ልናስብ /ልናሰላስል ይገባል ብየ አስባለው።
ላልተጣራ ፤ ለተጋነነ፤ በማስረጃ ላልተመሰረተ የበዛ የፓለቲካ መረጃ በየለቱ መጋለጥ ምን ምን ችግሮች ያመጣል ?
የመረጃ ይዘቱን /ኮንተንቱን/ ትተነው እንዲሁ ለሰፊ መረጃ ላይ በራሱ የተለያዩ እክሎች አሉት፡፡ ጽንፍ የወጡ ፤ መርዛማ ፤ መርህ-ቢስ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ ደግሞ የባሰ ጠንቀኛ መሆኑን መገመት ይቻላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዱም ስክሮሊንግ ወይም ዱም ሰርፊንግ የተሰኘ ቃል አለ ትርጉሙም ያልተጣራን፤ ገንቢ ያልሆነን ዜናን መቃረም ፤ ከኢንተርኔት ላይ መረጃ ለረጅም ሰአት ማጋበስ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ከቀልቡ ሳይሆን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጊዜ የሚያባክንበትን ይህን ሁኔታ የሚገልጽ የአማርኛ አቻውን አላገኘውትም፡፡ እናንተ የሚቀራረብ ብላችሁ የምታስቡትን አስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ ብታሰፍሩ በጣም ደስ ይለኛል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚደረጉ የፖለቲካ ውይይቶች ውስንነት ዋና ምንጩ እንደ የገፅ-ለገፅ ንግግሮች እና ተግባቦቶች ሁሉ የአካል እና የፊት ለውይይት የሚረዱ እንቅስቃሴዎች ባለመኖራቸዉ የሚፈጠረው ለመግባባት ማዳገት እና ሰዎች የሚረዱን በምንጽፈው ጽሁፍ /ቴክስት / ብቻ ከመሆኑ ጋር ይተሳሰራል፡፡፡ ይህ ደግሞ በአካል ለአካል ግንኙነት ካለው በበለጠ እና በባሰ መልኩ ሰዎች ከኛ ጋር ያላቸውን የሀሳብ አለመጣጣም እንዲሁም የአስተያየት ልዩነት ያሰፋዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ ሌላዉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚከናወኑ ፖለቲካዊ ውይይቶች እና ማህበራዊ ግንኙነቶች አንዱ ሌላ አብይ ችግር ደግሞ በርቀቱ ሰበብ ወዲያው በንግግሩ ተሳታፊዎች ላይ የሚመጣ እርምጃ ባለመኖሩ በግድ የለሽነት ስሜት እና ያለምንም የሀላፊነት መንፈስ የሚደረጉ ንግግሮች መኖራቸዉ ነዉ።
መነሻ እና መድረሻቸው በማይታወቁ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የፓለቲካ ክርክር -ውይይቶች ሰንጠመድ የስራ ውጤታማነታችንን፤ የፈጠራ ክህሎታችንን፤ ውሳኔ አሰጣጣችንን፤ በኑሮ ደስተነኝነታችንን ይጎዳል። ለዚህም በቂ ጥናቶች አሉ።
ከውይይቱ ብዙ ሳናተርፍ ግን ብዙ ጊዜ ማባከናችን በራሱ ለገንዘበ ብክነት በዚሁ ሰበብም ለጭንቀት ሊዳርገን ይችላል።
ሶሻል ሚዲያ ላይ ባገኘነው የተሳሳተ መረጃ ተመስርተን የተሳሳተ ውሳኔም ልናሳልፍ እንችላለን ወዘተ።
ስለዚህ በሶሻል ሚዲያ ሰለምናከናውናቸዉ የፖለቲካ ዉይይቶች ምን መላ እንምታ ?
በመጀመሪያ ስለ አጠቃላይ አጠቃቀማችንን ባህሪ ራሳችንን መታዘብ ይቀድማል፡፡ በየቀኑ የምናጠፋውን ጊዜ እና በገንዘብም ስናሰላው ያለውን ወጭ ማሰብ ያስፈልጋል። ከዚህ በመቀጠል ሌሎች ለየግል ለእያንዳንዳችን የሚሰሩ ስልቶችን በመጠቀም ጉዳቱን በመቀነስ ጥቅሙን መጨመር እንችላለን ፡፡
ለምሳሌ በቀን ውስጥ ለማህበራዊ ሚዲያ የምንበጅተው ውሱን ሰዓት ማበጀት ከበዛ ፤ወጥነት ከጎደላቸዉ የፖለቲካ ውይይቶች ባጠቃላይ ከፍተኛ ከሆነ የመረጃ ፍሰት ሊታደገን ይችላል። [ ይህ ጊዜ ምናልባት በስራ እረፍት መሃል ሊሆን ይችላል ወይም ታክሲ ባስ ውስጥም ሊሆን ይችላል….ብቻ የተወሰነ ጊዜ መወሰን እና በዚሁ በመደብነው ሰዓት ብቻ መጠቀም።
ሁሉንም አይነት የፖለቲካ መረጃ አለመቃረም፡፡ ከመረጃዎች ውስጥ በማሰረጃ ከጎለበተዉ በጠራ መረጃ ላይ በተመረኮዘው ብቻ ማተኮር ፡፡ ይህም በሁሉም የፓለቲካ ርእዩት ልውውጥ ውሰጥ በመጠመድ እና ንቁ ያልሆነ ተሳታፊነት [ሶሻል ሚዲያ ለርከር’ነት] ከሚመጣ የአዕምሮ መዛል እንዲሁም የጊዜ ብክነት ሊታደገን ይችላል::
የፖለቲካ ነክ መረጃዎች ሱስ እንደመሆናቸው የተለያዩ ወገኖች የራሳቸውን ፈላጎት ለማስረጽ የሚፈልጉበትም መስክም በመሆኑ በተጨማሪ ሌሎች አባሪ ምንጮች ለማዳባር መጣር ያስፈልጋል። በዚህም አንዳንዴ በቀላሉ እና ያላንዳች በቂ የሚባል ጥረት የፖለቲካ መረጃን ከኢንተርኔት ላይ ከምናገኝ ይልቅ ደከመን እና ለፍተን ሲሆን የተሻለ ነው:: በዚሀ ረገድ ሜንስትሪም ሚዲያ /mainstream media/ ጊዜ ተወስደዉ በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዩች የሚሰናዱ በበቂ ዝግጅት እና በላቀ የሀላፊነት ስሜት ስለሚዘጋጁ የተወሰነውን የፖለቲካ መረጃ ከዚህ ምንጮች ለማግኘት መሞከር።
የፖለቲካ አቁዋም ስንይዝም ከጥልቅ ምርምር እና ጥንቃቄ በሁዋላ መሆን አለበት፡፡
37 viewsNa le Tofek, 20:27