2023-01-12 22:34:52
ለመጀመሪያ ጊዜ ቡርቧክሶች ቀየ ዘለኩ ….
ሙዚቃ ሳይንስ ነው፡፡ ሙዚቃ ሀይማኖት ነው፡፡ ሙዚቃ ፖለቲካ ነው፡፡ በቃ ሙዚቃ የሁለንታ (Universe) ወኪል ነው፡፡
“ዳዊት በበገናው፣እዝራም በማሲንቆው የእግዚአብሔርን እናት ቅድስት
ድንግል ማሪያምን አመስግነው ሞትን ሳይቀር እንደ እንቅልፍ
አቅለውታል፡፡
የመፅሃፍ ቅዱሱን እዝራ የመሰንቆ ውርስ ለማግኘት ጎንደር ዙሪያ ማክሰኝት ከተማ ቡርቧክስ መንደር ላይ በመሰንቆ ድምፅ ከትመናል፡፡ ቡርቧክስ የአዝማሪዎች መንደር ናት፡፡ እነ ኤሊያስ ተባባል፣ እነ የሺ እመቤት ዱባለ--- ርቄ ሳልጓዝ ወንድሜ ወረታው እህቴ ሀረግም ሰፈራቸው እዚሁ ነው፡፡ ቡርቧክስ!!!
አበው ስለብርቧክስ ሲናገሩ መነሻቸው ነገስታቱ ናቸው ጎንደርን አፄ ፋሲለደስ በዝግ ፖሊሲ አረጋግተው እስከ ተከታዮቻቸው ለሁለት መቶ ዓመታት በሰላማዊ ሁኔታ መርተዋል፡፡ ሌላው ጊዜ የደርቡሽ ፣የመሳፍንቱ እና የሌላው የጦርነት ጊዜ ነበር፡፡ በደርቡሽ( በሱዳን)ጦርነቱ ጎንደር ማክሰኝት አካባቢ ከብቶች አለቁ፡፡ የጦር መሳሪያዎች ወደሙ፡፡ የትሬዛ ብር ወደመ፡፡ ብር እንደኳስ ተጠለዘ፡፡ ብር ኳስ ሆነ፡፡ ቡርቧክስ መነሻው ይሄው ነው፡፡ በተኮላተፈ አማርኛ ብር እንደ ኳስ ማለት ነው፡፡
ቡርቧክስ የአዝማሪዎች መንደር ነው፡፡ የቡርቧክስ ተወላጅ ከወላጁ የሚወርሰው ከፈረስ ጭራ እና ከወይራ እንጨት የተሰራ መሰንቆ እና የሰም ለበስ ቅኔ ግጥምን ነው፡፡ መሰንቆ በአንድ ክር የትኛውንም የሙዚቃ ምት የሚያወጣ ነባር የሙዚቃ መሳሪያ ነው፡፡ አዝማሪም፣ መሰንቆን ከመዘወር ጀምሮ ሰም ለበስ ግጥምን እስከ መቀኘት የመጠቀ ምናብ ያለው የጥበብ ሸራ ነው፡፡
መቸሞ በኛ ሀገር ታሪክ ፈረስ ና መሰንቆ የተጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ አዝማሪ ጣዲቋን ብቻ እናስታውስ፡፡ ፡በአድዋ ጦርነት ብዛት ያለው መሰንቆ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡አዝማሪ ጣዲቋም በመሰንቆዋ ቅኝት ወታደሩን በወኔ በማጋል፣ጠላትን በማደናበር የአድዋ ተራሮችን ተቀኝታባቸዋለች፡፡
አዝማሪ ከግዕዝ ወደ አማርኛ ሲተረጎም አመሰገነ ማለት ነው፡፡ እዝራ በመሰንቆ አምላኩን አመስግኗል፡፡ የኛ ሀገር አዝማሪዎች ጀግናን አመስግነው፣ፈሪን ነቅፈዋል፡፡ ተችተዋል፡፡
አዝማሪ፣ፊት ለፊት ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን፣የህዝብ ብሶት መተንፈሻ አባሪ እስትንፋስ ነው፡፡ለዚህም ነው ጃንሆይ ( ቀኃስ) በአዝማሪዎች አጥኝ እየላኩ የማህበረሰባቸውን ስሜት ያዳምጡ
የነበረው፡፡ህዝብን እስከ ፍላጎቱ ከአዝማሪዎች አንደበት ይገኝ ነበርና፡፡
በኃላ ግን ከደርግ ዘመነ መንግስት ጀምሮ መንግስትን አዝማሪዎች እንዳይተቹ ሲባል አዝማሪነትን ማናናቅ፣ማዋረድ፣ማንቋሸሽ ተጀመረ-የደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ በኛ ና አብዮቱ በተሰኘው መፅሃፋቸው እንደመሰከሩት፡፡
የጎንደር የቡርቧክስ አዝማሪዎች ግን መሰንቆቸውን ከትክሻቸው ሳያወርዱ ያባቶቻቸውን የጥበብ ገፀ በረከት አስከትለዋል፡፡ ዛሬም በዚህ ሰፈር ፖለቲካ፣ሃይማኖት፣ ፍቅር...... በመሰንቆ
ይወራል፡፡ ይመሰጠራል፡፡ ባህል ና ስነ ልቦና በቡርቧክስ አዝማሪዎች አንደበት ይተነተናል፡፡ከዚህች ሰፈር የጎንደር ስሜት፣የአማራ ስነልቦና ፣የኢትዮጲያዊነት መዳረሻ. .......በመሰንቆ ይገለፃል፡፡ እነሆ መሰንቆ እና ግጥም በአዝማሪዎች ደጃፍ፣
"""" ""''
አዝማሪው ይዘፍናል ማሲንቆ በዜማ እየከረከረ
የፈረስን ጭራ የፍየልን ቆዳ ባንድ እያናገረ
ግጥሙ ግን ከንቱ ነው ፍፁም ሀሳብ የለሽ
‹‹አልማዝ እንደምን ነሽ እናናየ እንዴት ነሽ››
ኤዲያልኝ አዝማሪ ኤዲያልኝ ማሲንቆ
ድምፅ ብቻ መስማት ሀሳብ ተደብቆ
ተቀበል አዝማሪ ተቀበለኝ ግጥም
ህይወቴን ዝፈነው ቅኝትህ እንዲጥም
‹‹እህህን እህህ…ዋሆየ ዋሆየ››
‹‹ጭራ ሆኜ ቀረሁ አንቺን ከፊት ብየ››
ተቀበል አዝማሪ ኑሮየን ተቀኘው
የመንከራተቴን ውሎየን ዝፈነው
ሀያ አመታት ሙሉ አገር ለጠበቀ
ላገሩ ዳር ድንበር የትም ለወደቀ
አስር አለቃ ነው የተሰጠው ማረግ
እያየህ ዝምያልከው እንዳይሆን ሲደረግ
ኧረ ተው ፈጣሪ ኧረ ተው ኧረ ተው
ግፌን ደበቁህ ወይ አንተንም እንደሰው
******ተቀበል አዝማሪ ብሶቴን አዚመው
የማሲንቆህ ዜማ ጩኸቴን ይልቀቀው
‹‹እትብቴ ከወዲያ መቃብሬ ወዲህ››
‹‹በተወለድኩበት አልኖርኩም ከንግዲህ››
ሞኝነት ነበር ወይ ምሽግ ላይ ማርጀቴ
ሰው ኪሱን ሲሞላ ሀገሬን ማለቴ
ጅልነት ነበር ወይ ላገር መዘመሬ
ጦቢያ በሚሉት ቃል ሌት ተቀን መስከሬ
በጨርቅ ሱሪ ላይ ከስክስ ጫማ አድርጌ
ጉራማይሌ መልኬን ከሰዎች ሸሽጌ
ስራ ማስታወቂያ ከሚለጠፍበት
አየሁ ለኔ ሚሆን ግሩም የስራ አይነት
የስራ መደቡ የስራው መጠሪያ
ዘበኝነት ይላል የጥበቃ ሙያ
የስራ ልምዱ ላይ እዛ ሚፈለገው
በውትድርና የስራ ልምድ ያለው
እይልኝ እጣዮን ያገሬን ብሽቅነት
የሹመቴን ቦታ ርስትና ጉልት
እይልኝ አገሬን የገልቱነቷን ጥግ
ቀርፍታ ስትጥለው ህይወቴን እንደምርግ
******እንዲህ ብለህ ዝፈን እንባየን ተውሰህ
እናናየ እንዴት ነሽ ስትል እንዳልሰማህ የኔን እምባ ትተህ
‹‹ምንድን ነው ውዳሴ ከንግዲህ ለጠላ››
‹‹የደረቡት ሁሉ ከሆነ ነጠላ››
‹‹ጠበቃሽ ማን ይሆን ዋስሽስ ማን ይሆን››
‹‹ነበረኝ ያልሽው ሰው እንዳልነበር ሲሆን››
አድሮ ጥጃ ነው ወይ ከቶ የኔ ሹመት
ካደባባይ ጓዳ ከእልፍኝ ወደ ማጀት
******እንዲህ ብለህ ዝፈን ተቀበል አዝማሪ
ለዚች መናኛ አገር በቁሜ ቀባሪ
ወጥቶ ላደረ ሰው እድሜውን በሙሉ ጋራ ሲሰነጥቅ
አይጠብበትም ወይ ስርቻ መንደር ውስጥ ደጃፍን መጠበቅ፡፡
….. አቤት የግጥማቸው ለዛ የስንኝ አጣጣሉ ዛሬ እኔ ብያለሁ
የገጣሚው ግጥም ሀረጉ ስንኙ
ዘንድሮስ ያስብላል አይ ገጣሚ ሞኙ
ብቻ የሆነ ሆነና ዛሬ ስጓጓላት የነበረችውን የብርቧክሶችን የዋርካ ዛፍ አገኘኃት ብዙ ጥያቄዎችን ጠየኳት ምን ትሺ ይሆን አልኳት መልሳ ብዙ ጥያቄ ጠየቀችኝ በጣም ብዙ ጥያቄ ብቻ ብዙ ብዙ የቤት ስራ አለብን ክብር ለመሰንቆ እመለስበታለሁ
ቅዳሜ በጎንደር ከተማ ታላቅ የአዝማሪዎች ፌስቲባል በክብር ተጋብዛችኃል፡፡
90 viewsNa le Tofek, 19:34