2023-04-28 12:07:35
“በጎነትነትን አደርግልሃለሁ” (ኦሪት ዘፍጥረት 32:9)
አባቶቻችን ‘በጎ ማድረግ ለራስ ነው’ ይላሉ፤ ይህን አባባል በአንድም ይሁን በሌላ ሰምተነው ሊሆን ይችላል፤ ግን ስንቶቻችን እንሆን አስተውለን የቃሉን ትርጉም የመረመርነው? ስንቶቻችንስ ነን ፍቺውን ተረድተን በሕይወታችን የተገበርነው?
በሕይወታችን ውስጥ በርካታ ሰዎችን ልናውቅ እንችላለን፤ ከሁሉም በበለጠ በልባችን ትልቅ ስፍራ ያላቸው ወላጆቻችን፣ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን እንዲሁም ዘመድ አዝማዶቻችን እና ባልንጀሮቻችን እንደራሳችን የምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ በጎ ልናደርግላቸውም የተገባ ነው፤ ለእነርሱ ዘወትር መልካም ማድረግን ቸል ልንል አይገባም፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር መልካምነትን የሚወድ አባት መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ክፍል ኦሪት ዘፍጥረት ላይ በተደጋጋሚ ተገልጾ እናገኘዋለን፤ ሰውን የፈጠረውም ለመልካም መሆኑን ተገልጿል፤ ፈጣሪያችን ነገርን ሁሉ ለበጎ እንዳደረገው በሥነ ፍጥረቱ መግለጹን እዚህ ላይ እንመለከታለን፡፡ (ዘፍ.፪፥፩-፯)
ቅዱስ ያዕቆብ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበት ስፍራ ተመለስ፤ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለባሪያህ በአደረግኸው በምሕረትህና በእውነትህም ሁሉ በጎውን አድርግልኝ” በማለት በጎነትን የሚያደርግ አምላክ እንዳለን አመልክቶናል፡፡ (ዘፍ.፴፪፥፱)
የበጎነቱ ተምሳሌትም በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረን እኛ ሰዎች በክርስቲያናዊ ሕይወታችን የምንተገብረው ምግባር እንደሆነ በቅዱሳን መላእክት፣ በነቢያትና በሐዋርያት ላይ አድሮ በቅዱስ ቃሉ አስተምሮናል፡፡
ሰው ለመልካም ተፈጥሮ መልካም ማድረግን ገንዘቡ ሊያደርግ እንደሚገባ በሥነ ፍጥረት ትምህርት የምንረዳው ነው፤ አምላካችን መልካም እንደሆነ እኛም ሰዎች መልካም መሆን፣ አምላካችን ለፍጥረታቱ መልካም እንዳደረገ እኛም ለሰዎች መልካም ማድረግ የተገባን ነን፡፡
በጎነት ሰው ላይ ክፋት ካለማሰብ ይጀምራል፤ ያም ለሰው መልካም መመኘትን ያመጣል፤ ወንድማችን፣ እኅታችንና ወዳጆቻችን ጥረው ግረው ስኬታማ ሲሆኑ ማየትን፣ መልካም ትዳር ሲይዙ መደሰትን እንዲሁም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሲበረቱ ምስክር ለመሆን መብቃትን ያስከትላል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም! ለዚህ ሁሉ ስኬት ለሚወስዱት እርምጃና ለሚያከናውኑት ተግባር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማድረግና መርዳት ለሰው በጎ መሆን ነው፡፡
በወተትና በፍትፍቱ መግበው ያሳደጉንን አባት እናቶታችንን መጦር፣ የታላላቆቻችንን ውለታ መክፈል፣ አያቶቻችንን መንከባከብ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶቻችን ምክርና ትእዛዝ በመተግበር እነርሱን ማገልገል ይገባል፡፡ በተጓዳኝም በሕይወታቸው ለሚያጋጥማቸው ማንኛውም ችግር መድረስና የተቻለንን ርዳት ማድረግ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በጎ ማድረግ ለሰዎች መልካም መሆን ብቻ ሳይሆን በውስጣችንም የሚፈጥረው መልካም ስሜት ይኖረዋል፤ ለሌሎች በጎ ነገር ባደረግን ቁጥርም መልካምነት በውስጣችን ከመስረጹም ባሻገር አምላክችን ደስ ስለሚሰኝብን መንፈስ ቅዱስ ያድርብናል፡፡ ይህም ዘወትር መልካም ሰው እንድንሆን ይረዳናል፤ አባቶቻችን “በጎ ማድረግ ለራስ እንዲሉ ያደረጋቸውም ይህ ነው!
አምላካችን እግዚአብሔር በበጎ ምግባር የታነጽን መልካም ሰዎች እንድንሆን ይርዳን!
4.2K views09:07